ፈረሰኞቹ ከመስመር አጥቂያቸው ጋር በስምምነት ተለያይተዋል

በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ፈረሰኞቹን የተቀላቀለው የመስመር አጥቂው ከክለቡ ጋር በስምምነት ተለያይቷል።

የወቅቱ የሊጉ ባለድል ቅዱስ ጊዮርጊስ ሦስት ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ በመቀላቀል ውላቸው የተጠናቀቀባቸውን ተጫዋቾች ደግሞ የኮንትራት ዘመናቸውን በማራዘም እያቆየ ይገኛል። አሁን እንዳገኘነው መረጃ ከሆነ ከሰበታ ከተማ ዘንድሮ ፈረሰኞቹን የተቀላቀለው ቡልቻ ሹራ ከፈረሰኞቹ ጋር በስምምነት መለያየቱን ተጫዋቹ ገልፆልናል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ ቀሪ የአንድ ዓመት ኮንትራት ያለው የመስመር አጥቂው ከክለቡ አመራሮች ጋር በመነጋገር በስምምነት በመለያየት መልቀቂያውን መውሰዱን አረጋግጠናል። ቡልቻ ከፈረሰኞቹ ጋር የሊጉን ዋንጫ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ያነሳ ሲሆን በቅርብ ጊዜ ወደ ሌላ ክለብ እንደሚያመራም ይጠበቃል።