ሠራተኞቹ የሦስት ተጫዋቾችን ዝውውር አገባደዋል

በአሠልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ የሚመራው ወልቂጤ ከተማ የግብ ዘብ፣ አጥቂ እና ተከላካይ ማስፈረሙ ታውቋል።

በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት 8ኛ ደረጃን ይዞ የቀጠናቀቀው ወልቂጤ ከተማ ዘግየት ብሎም ቢሆን በዝውውር ገበያው እየተሳተፈ የቀጣይ ዓመት ስብስቡን እያጠናከረ ይገኛል። በዛሬው ዕለትም የሦስት ተጫዋቾችን ዝውውር መፈፀሙን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ቡድኑን የተቀላቀለው የመጀመሪያው ተጫዋች አቤል ነጋሽ ነው። ከመከላከያ ወጣት ቡድን የተገኘው ይህ አጥቂ በዋናው ቡድን ዓምና እና ዘንድሮ ግልጋሎት የሰጠ ሲሆን ግማሽ ዓመት ላይ ግን በስምምነት ከክለቡ ጋር ተለያይቶ አዲስ አበባ ከተማን ተቀላቅሎ ነበር። ተጫዋቹ ከቀናት በፊት አዲስ አዳጊውን ክለብ ለገጣፎ ለገዳዲን ለመቀላቀል ቅድመ ስምምነት ፈፅሞ የነበረ ቢሆንም መዳረሻው ሠራተኞቹ ቤት ሆኗል።

ሁለተኛው ተጫዋች ደግሞ ሳሙኤል አስፈሪ ነው። የቀድሞ የአረካ ከተማ፣ ዱራሜ ከተማ እና የካ ክፍለ ከተማ ተጫዋች አዲስ አበባ ከተማን ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊግ አሳድጎ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በሊጉ ቆይታን አድርጎ ነበር። ከክለቡ ጋር ያለው ውል መጠናቀቁን ተከትሎ የቡድን አጋሩን ተከትሎ ወልቂጤን ተቀላቅሏል።

የዛሬው የቡድኑ ሦስተኛ ፈራሚ የሆነው ተጫዋች ግብ ጠባቂው ፋሪስ አላዊ ነው። ቁመታሙ የግብ ዘብ ፋሪስ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ቤንች ማጂ ቡና ቆይታን ያደረገ ሲሆን በፕሪምየር ሊጉ የመጀመሪያ ዓመቱን በወልቂጤ ለማሳለፍ ፊርማውን አኑሯል።