ሲዳማ ቡና የቅድመ ውድድር ዝግጅት የሚጀምርበት ቀን ታውቋል

ከአሰልጣኝ ወንድማገኝ ተሾመ ይፋዊ ሹመት በኋላ በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን የቀላቀለው ሲዳማ ቡና የ2015 የውድድር ዘመን ዝግጅቱን መቼ እንደሚጀምር ተገልጿል፡፡

ከአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ጋር በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት አጋማሽ ከተለያየ በኋላ ረዳት አሰልጣኙ ወንድማገኝ ተሾመን በጊዜያዊ አሰልጣኝነት የሾመው ሲዳማ ቡና ከቀናት በፊት ደግሞ ወንድማገኝን በዋና መንበሩ ላይ ሾሞ ለ2015 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተጠናክሮ ለመቅረብ ይጠቅሙኛል ያላቸውን አዳዲስ ተጫዋቾች ሲቀላቅል ሰንብቷል፡፡

ይህንን ዘገባ እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ ቡልቻ ሹራ ፣ ሙሉቀን አዲሱ ፣ እንዳለ ከበደ ፣ አበባየው ዮሃንስ ፣ ፀጋዬ አበራ ፣ አንተነህ ተስፋዬ ፣ አቤል እንዳለ እና ፊሊፕ ኦቮኖን በአዲስ መልክ ያስፈረመ ሲሆን ውላቸው የተጠናቀቁ ተጫዋቾችንም ቆይታ እያደሰ ከቆየ በኋላ የቅድመ ውድድር ዝግጅት የሚያደርግበት ቀን አሁን አሳውቋል።

ቡድኑ በሀዋሳ ከተማ ነገ ቅዳሜ ሐምሌ 30 ለተጫዋቾቹ የህክምና ምርመራን ከፈፀመ በኋላ ከሰኞ ነሀሴ 2 – 2014 ጀምሮ በይፋ ዝግጅት ማድረግ ይጀምራል፡፡