የአሠልጣኝ ውበቱ የድህረ-ጨዋታ አስተያየት

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ቡድናቸው ከዩጋንዳ አቻው ጋር በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ካደረጉት የወዳጅነት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ በስፍራው ለተገኙ የመገናኛ ብዙሀን አባላት ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።

ስለጨዋታው

“ከ7 የልምምድ ቀናት በኋላ ያደረግነው ጨዋታ ነበር። ቡድናችን በምን ደረጃ እንደሚገኝ የተመለከትንበት እንዲሁም በዛሬው ጨዋታ ከ3 ተጫዋቾች ውጭ ያሉንን በሙሉ የተመለከተንበት ነበር ፤ በምንፈልገው የጨዋታ መንገድ ለመጫወት ግን እንደተመለከታችሁት ሜዳው ትንሽ አስቸጋሪ ነበር። በተጨማሪም ተጋጣሚ ይዞት የመጣው ትንሽ ሀይል የቀላቀለ አጨዋወት ነገሮችን ፈታኝ አድርጎብን የነበረ ቢሆንም እንደአጠቃላይ ግን ጥሩ ነበር።”

በጨዋታው ቡድናቸውን እንዴት ገመገሙት

“እያንዳንዱ ጨዋታ የራሱ መልክ አለው ፤ ሩዋንዳ የመጀመሪያውን ዙር ሳትጫወት በነበራት ደረጃ ላይ ሆና ነው እኛን የምትጠብቀው ፤ እኛ ደግም ከዚህ ጨዋታ አስቀድመን በቀጠናው ጠንካራ የሆነውን የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን መግጠማችን ይረዳናል።ይህ ማለት ግን ዩጋንዳ እና ሩዋንዳ ተመሳሳይ ናቸው ማለት አይደለም። ይህ የወዳጅነት ጨዋታ እንደመሆኑ በርካታ ተጫዋቾችን ትቀይራለህ ፤ ያኛው የተወሰኑ ተጫዋቾችን ትቀይራለህ በዚህኛው ራስን ለማየት ነው የምትጫወተው ያኛው ደግሞ የግድ ለማሸነፍ ስለዚህ ጫና ፣ ፍላጎት እና ሌሎች ብዙ የሚለይበት ነገር አለ ነገርግን እንደመዘጋጃ ጨዋታ ለእኛ ጥቅም አለው።”

በእሁዱ ጨዋታ መሻሻል ስለሚገባቸው ጉዳዮች

“በማጥቃት ሲሶው ላይ ተደጋጋሚ እድሎችን መፍጠር ይኖርብናል። በተጨማሪም ወደ ራሳቸው ሜዳ ሸሽተው በሚጫወቱበት ወቅት በትዕግሥት ለማስከፈት የምናደርገው ጥረት መሻሻል ይኖርብናል።”

በጨዋታው ስላደረጉት የተጫዋቾች እና የአጨዋወት ለውጥ

“ሁሉንም ተጫዋቾች ለመጠቀም ሞክረናል። መጨረሻ ላይ በረከትን ስናወጣ ሜዳ ላይ ሊኖረን የሚችለው ነገር መቀየር ነበረብን። ስለዚህ ሁለት አጥቂዎችን ይዘህ ሜዳ ላይ አንድ አማካይ ወደ ውጭ አውጥተህ ከመጫወት በሦስት የመሀል ተከላካዮች ፣ በአምስት አማካዮች እና በሁለት አጥቂ መጫወት ነው። እንደ ጨዋታው በተለያዩ አደራደሮች መጫወት መጥፎ አይደለም። ዋናው ነገር የምንጫወትበትን መንገድ አለመልቀቃችን ነው። ከጨዋታ መንገድ አንፃር ብዙ ለውጥ አልነበረም ፤ በቅርፅ ረገድ ከ4-3-3/4-2-3-1 ከሚመስል አደራደር ወደ 3-5-2 መጥተን ነበር። በዚህም እድሎችን መፍጠር ችለን ነበር። በጥቅሉ ግን ከለውጡ በኋላ የተመለከትነው ነገር መጥፎ አልነበረም።”

ተጫዋቾች ከዕረፍት መምጣታቸው ስለፈጠረባቸው ተፅዕኖ

“በተለይ በመከላከል ሽግግራችን ወቅት መጠነኛ ችግሮች አይቻለሁ። በማጥቃቱ ግን በረከት የፈጠረው አጋጣሚ ላይ አብረውት ሌሎች ተጫዋቾች ደርሰው ተመልክቻለሁ ፤ በመከላከል ሽግግር ወቅት የነበረን ክፍተት ከአካል ብቃት ጋር የተያያዘ ነበር። ይህን በ7 ቀን ልምምድ ምንም ማድረግ አንችልም። በጣም ለአጭር ጊዜ እንደመገናኘታችን ተጫዋቾች ወይ ከውድድር አልያም ከጠንካራ ዝግጅት ላይ አለማግኘታችን ተፅዕኖ ፈጥሯል።”