“ከአቡበከር እና ሽመልስ ውጪ ግብፅን ያሸነፈውን ቡድን መግጠማችን ለእኛ ትልቅ ነገር ነው” ሚቾ

አመሻሽ ላይ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ያከናወነው የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ሰርዲዮቪች ሚሉቲን ተከታዩን የድህረ-ጨዋታ አስተያየት ሰጥተዋል።

ጨዋታው እንዴት ነበር?

“በመጀመሪያ የዛሬውን እና የእሁዱን ጨዋታ እንድናደርግ ቀድመው ሀሳቡን ያመጡትን አቶ ኢሳይያስ ጂራ እና ውበቱ አባተን ማመስገን እፈልጋለው። ይሄ ለእኛ ብዙ ማለት ነው። እኔ በግሌ የማስበው በእግር ኳስ ወይ ታሸንፋለህ አልያም ትምህርት ወስደህ ትወጣለህ ብዬ ነው። እኛ ዛሬ ትምህር ወስደን ነው ከሜዳ የወጣነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በጣም ጥሩ ቡድን ነው። ለዚህም የቡድኑን አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ማመስገን እፈልጋለው። ቡድኑ ፕሬሲንግ መቋቋም ይችላል ፤ በተጨማሪም በኳስ ቁጥጥር ጨዋታውን ለመቆጣጠር የሚጥር ነው። ይህ ደግሞ በጨዋታው በደንብ እንድንማር አድርጎናል። እኔ ከ14 የልምምድ መርሐ-ግብሮች አንድ ጨዋታ የተሻለ ምስል ይሰጣል ባይ ነኝ። በተለይ በልምምድ ላይ የተሻሉ ሆነው ጨዋታዎች ላይ ጥሩ ያልሆኑ ተጫዋቾችን ለማየት ይጠቅማል። በእንደዚህ አይነት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች ላይ ሙከራዎችን ነው የምታደርገው። በነጥብ ጨዋታዎች ብቻ ነው በደንብ ለመፎካከር የምትጥረው። በአጠቃላይ የዛሬው እና የእሁዱ ጨዋታ ለቀጣዩ ወሳኝ ጨዋታችን ጥቅም አለው። በዚህም አጋጣሚ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን እንኳን ደስ አላችሁ ማለት ነው። በጨዋታዎች ላይ ባለቀ ሰዓት ነጥብ መጣል ደስ አይልም ግን ጥሩ የእግርኳስ ባህል ያለው ሀገር መጥተን ጨዋታ በማድረጋችን ደስተኛ ነን። ኢትዮጵያ ሁለተኛ ሀገሬ ነች። ስለዚህ በመምጣቴ ደስተኛ ነኝ ፤ ከጨዋታውም ባገኘነው ትምህርት ደስተኛ ነኝ።”

ውጤቱ ፍትሀዊ ነው?

“ስለውጤቱ ማውራት አልፈልግም። በእግርኳስ ጨዋታዎች ማግኘት የሚገባህን ነገር ላታገኝ ትችላለህ ፤ ማግኘት ያለብህን ነው የምትቀበለው። ጨዋታውን ተሸንፈናል። እንደዛ ባይሆን ጥሩ ነበር። ግን ለነጥብ ጨዋታ በዚህን ያክል ደረጃ መዘጋጀታችን ጥሩ ነው። በተለይ ከአቡበከር እና ሽመልው ውጪ ግብፅን ያሸነፈውን ቡድን መግጠማችን ትልቅ ነገር ነው። ይህ ስለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደረጃ እና ብቃት የሚነግረን ነገር አለ። ከዚህም ቡድን ትምህርት ለመማር በመምጣታችን ደስተኞች ነን።”