ሲዳማ ቡና ናይጄሪያዊ አጥቂ አስፈርሟል

በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ሲዳማ ቡና ሦስተኛ የውጪ ዜጋ ተጫዋች ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል።

ጊዜያዊ አሠልጣኙ ወንድማገኝ ተሾመን በዋናው መንበር ከሾመ በኋላ በዝውውር መስኮቱ የነቃ ተሳትፎ ያደረገው ሲዳማ ቡና በዛሬው ዕለት 8ኛ ፈራሚውን አግኝቷል። ቡድኑን የተቀላቀለው ተጫዋች ናይጄሪያዊው ጎድዊን ኦባጅ ነው።

የ26 ዓመቱ የአጥቂ መስመር ተጫዋች ጎድዊን ዊኪ ቱሪስትስ፣ ፕሌትዩ ዩናይትድ እና አባያ ዋሪየርስ ለተባሉ የሀገሩ ክለቦች የተጫወተ ሲሆን ወደ ቱኒዚያ አምርቶም ኤስ ኬይሩዋንን ተቀላቅሎም ግልጋሎት ሰጥቷል። በተጫወተባቸው ክለቦች ለከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ሲፎካከር የነበረው ጎድዊን አሁን ደግሞ ሲዳማ ቡናን በቀጣዩ ዓመት ለማገልገል የአንድ ዓመት ውል ፈርሟል።

ሲዳማ ቡና እስካሁን ፀጋዬ አበራ፣ አንተነህ ተስፋዬ፣ አቤል እንዳለ፣ እንዳለ ከበደ፣ ሙሉቀን አዲሱ፣ ፍሊፕ ኦቮኖ እና ቡልቻ ሹራ በአዲስ መልክ ወደ ስብስቡ መቀላቀሉ ይታወቃል።