የፌዴሬሽኑ ዋና ፀሀፊ መግለጫ ሰጥተዋል

በቀጣይ ሁለት ቀናት የሚደረገውን የምርጫ ጠቅላላ ጉባዔ የተመለከተ መግለጫ ተሰጥቷል።

መጪውን አራት ዓመታት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት እና ሥራ አስፈፃሚ የሚሆኑ ግለሰቦችን ለመለየት የሚደረገው የምርጫ ጠቅላላ ጉባዔ ነገ እና ከነገ በስትያ በኢሲኤ አዳራሽ ይከናወናል። የዚህን የምርጫ ሂደት በተመለከተ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፅህፈት ቤት የከወናቸውን ተግባራት አስመልክቶም ዋና ፀሀፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን ዛሬ በፌዴሬሽኑ ቢሮ መግለጫ ሰጥተዋል።

ዋና ፀሀፊው የሁለቱ ቀናት ጠቅላላ ጉባዔ በቅድሚያ ሪፖርት ቀርቦበት በቀጣይ ወደ ምርጫ የሚሄድበትን ሁናቴ በቀጣይ ጊዜያት በአንድ ቀን እንዲጠናቀቅ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን በማብራራት መግለጫቸውን ጀምረዋል። በመቀጠል ለምርጫ አስፈፃሚው እና ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው አስፈላጊ ግብዓቶችን ማሟላት እና ማገዝ እንዲሁም ቁሳቁሶችን የሟሟላት ሥራ ሲከወን መቆየቱን የተናገሩ ሲሆን ከደህንነት አንፃር በዕለቱ ብቻ መድረስ ያለባቸው የህትመት ወረቀቶችንም በጊዜው እንደሚያደርሱተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ ለተሳታፊዎች ጥሪ ማድረግ ፣
ለክለብ እና ክልሎች ተወካዮችን ቨሪፋይ የማድረግ ፣ የኢሲኤን አዳራሽ ለጉባኤው ማድረስ እንዲሁም መጪው አስተዳደር ሥራውን ከምንም እንዳይጀምር ለማገዝ ሌጋሲ ዶክመንት በማዘጋጀት መቆየታቸውን አስረድተዋል። ታዛቢዎችን በተመለከተ ዋና ፀሀፊው እንዳሉት አራት የፊፋ ተወካዮች የሚኖሩ ሲሆን ከሪጅናል ኦፊስ ሁለት ፣ የአፍሪካን ጉዳዮች የሚመለከት ከፈረንሳይ ፣ ከዙሪክ ደግሞ የገቨርናንስ ባለሙያ ዛሬ ማታ እና ነገ ጠዋት አዲስ አበባ እንደሚገቡ ይጠበቃል። በተጨማሪ የካፍ ተወካይ አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን የሴካፋ ፕሬዘዳንት ደግሞ እሁድ እንደሚደርሱ ተጠቁሟል።

በመቀጠል ዋና ፀሀፊው ከጋዜጠኞች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡ ሲሆን ዋና ትኩረት የተደረገባቸው ጥያቄዎች እነዚህ ነበሩ።

ከፕሬዘዳንት ዕጩነት ውጪ የሆኑት አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ያቀረቡትን አቤቱታ ተከትሎ CAS (Court of Arbitration for Sport
) ከፌዴሬሽኑ ስለጠየቀው ማብራሪያ…

“CAS የላከው ደብዳቤ ደርሶናል። ማብራሪያ እንድንሰጥ የጠየቀባቸው ጉዳዮች ነበሩ። እንደ ኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ምላሽ ሰጥተናል። ዝርዝሩን ባልሄድበትም ግን ይሄንን ያመለከቱት አካል ለCAS ያቀረቧቸው ጥያቄዎች ነበሩ። እኛም ጉዳዩ ለCAS ግልፅ እንዲሆን ማብራሪያ ሰጥተናል። ትናንት ማታ የተላከ እና ዛሬ ስድስት ሰዓት ድረስ ላኩ የሚል እና በአጭር የጊዜ ገደብ የተላከ ነው። አጭር ጊዜ ነው የተሰጠን። ጉባዔውን የተሳካ ከማድረግ አንፃር ብዙ ሥራዎችን እየሰራን ነው። እዛ ላይ ነው ጊዜያችንን እያጠፋን ያለነው በቶሎ ባናየው እና ዛሬ ቢያልፍ ከባድ ውጤት ይኖረው ነበር። CAS ለእኛ ነው የላከው። ምላሹን ስንሰጥ ግን ለፊፋም ጭምር ነው። ከዚህ ቀደም ለፊፋ ጥያቄዎች ቀርበዋል ይባላል ፤ ፊፋ በይፋ የጠየቀን ነገር የለም። በዚህ ጉዳይ ላይ መደበኛ ያልሆኑ ውይይቶች ግን አሉ። (ስለክሱ) እንጂ በይፋ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በዚህ ጉዳይ ማብራሪያ ይስጥበት ብሎ ፊፋ የላከው ነገር አልነበረም ፤ ካፍም በተመሳሳይ። የበላይ የሆነው CAS ላቀረበው ጥያቄ ደግሞ ምላሽ ሰጥተናል።”

ለጠቅላላ ጉባዔው የሚቀርበው ሪፖርት ከምርጫው በኋላ ቢደረግ የተሻለ የሆን እንደነበር…

“ይሄን የተለመደውን አካሄድ ወደ ፊት ማስተካከል ይኖርብናል። ያ ማለት ግን ተሳስተናል ማለት አይደለም። የሚመጣው ሥራ አስፈፃሚ እና ፕሬዘዳንት በዚህ ዓመት ውስጥ ምን ተሰራ የሚለውን ጥንቅቅ አድርጎ ሪፖርት ያገኛል። ተቋሙ አይሞትም ፤ ሥራ አስፈፃሚ ሊሄድ ይችላል የተመረጠ አካል ይሄዳል ፤ ሌላ ይመጣል ፤ ተቋሙ ግን ሁሌም ያቅዳል ሪፖርት ያደርጋል። የሚመጣው አካል ደግሞ ዕቅዱን አይቶ ይሄ ዕቅድ አልተመቸኝም ቢል ዕቅድ መከለስ ስለሚችል በዛ አንፃር ነው እንደፌዴሬሽን ሪፖርት ቀርቦ ወደ ምርጫ የምንሄደው። ከዛ የዘለለ ምንም ዕንድምታ የለውም።”

ስለጉባዔው መካሄጃ ከተማ ለውጥ ከፊፋ የመጣ ደብዳቤ ስለመኖሩ…

“የጉባዔ ቦታን የመወሰን ሥልጣን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ነው። ፊፋ ካፍ ሲባል የሚደነግጥ አካል አለ ብሎ ከማሰብ ነው እንጂ ፊፋም ካፍም ቦታ ለምን ቀየራችሁ ብሎ በዚህ ጉዳይ ጣልቃ አይገባም ፤ ምክንያቱም ሥልጣኑ የሥራ አስፈፃሚው ኮሚቴ ነው።”

ፅህፈት ቤቱ እንደስጋት የሚያው ነገር ስለመኖሩ…

“እንደስጋት የሚነሳ ነገር የለም ለCASም ለተጠየቅነው ነገር ምላሽ ሰጥተናል። ስጋት ከተባለም ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ የምንሰማቸው እና ተጨባጭ መረጃ ያላቸው ነገሮች ናቸው። ቶሚ ሆቴል ላይ ትናንትና ድራማ እንደነበር ይታወቃል። የሚዲያ አካላትም የምታውቁት ይመስለኛል። የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ነው አልጋ የያዘላችሁ ተብለው ቶሚ ሆቴል የተወሰኑ ሰዎች ከደቡብ ክልል እንዲያርፉ ተደርገዋል። ያንን ማን እንዳደርገ አናውቅም። ግን በረፈደ ሰዓት የምርጫ ድራማዎች ይሰማሉ። መጨረሻ ላይ ሁሉም ለኢትዮጵያ እግርኳስ የሚጠቅም አካልን አመዛዝኖ የሚመርጥበት ሁኔታ ነው የሚኖረው። ቦታው ላይ በኢትዮጵያ እግርኳስ ትልልቅ ስም ያላቸው ሰዎችም ታይተዋል ተብሏል። ይሄ ነው ምንአልባት ስጋት ሊሆን የሚችለው። ምርጫውን በዚህ መንገድ በገንዘብ ለማድረግ የሚኬዱ መንገዶች ለኢትዮጵያ እግርኳስ ውድቀት ይሆናሉ ብዬ አስባለሁ።”

ከላይ ከተነሳው ሀሳብ አንፃር ከፌዴሬሽኑ መረጃዎች ስለሚወጣበት መንገድ…

“ሰራተኞች ፕሮፌሽናል ሆነው እንዲሰሩ ያስፈልጋል። ማንም ወደ ሥልጣን ይምጣ አይምጣ ፕሮፌሽናል አካሄድ መኖር አለበት። ነገር ግን የተለያዩ መረጃዎችን በማሹለክ ለአንዱ በመስጠት አለ። በቤቱ ገንዘብ እየተከፈላቸው ፤ ገንዘብ እያገኙ ነዳጅ እየተሞላላቸው የቤቱን መኪና እየተጠቆሙ የማይሆኑ ተግባራት ላይ የተሰማሩ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ከውስጥም ከውጪም ፈተና ሆነውብን ቆይተዋል። እኛም እርምት የወሰድንባቸው ጉዳዮች አሉ። መረጃዎችን አለማግኘት ሲኖር ደግሞ በተለያየ አቅጣጫ ለመቅረብ ሲሞከር እንደነበር ይታወቃል።”