የክለቦች የውድድር ዘመን ዳሰሳ | ድሬዳዋ ከተማ

ያለፉትን የውድድር ዓመታት በደረጃ ሰንጠረዡ የታችኛው ፉክክር ራሱን ሲያገኝ የነበረው ድሬዳዋ ከተማ የዘንድሮውን የሊግ ውድድር ሊቀርብ ያሰበበትን መንገድ እና ዝግጅት አስመልክቶ ተከታዩን ዳሰሳ አሰናድተናል።

1975 ላይ የተመሰረተው ድሬዳዋ ከተማ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በአዲስ መልክ 1990 ላይ ከተጀመረ በኋላ ለ10ኛ ጊዜያት ተሳትፏል። እርግጥ ክለቡ በእነዚህ ዓመታት በአብዛኞቹ ላለመውረድ በሚደረገው ፉክክር እራሱን እያገኘ በመጨረሻዎቹ የጨዋታ ሳምንታት መትረፉን ሲያረጋግጥ እንደከረመም ይታወቃል። ዓምናም ይሁ አባዜ ቡድኑን ተጠናውቶ በመጨረሻው ጨዋታ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በተፈጠሩ አወዛጋቢ ትዕይንቶች ለከርሞ በሊጉ መኖሩን አረጋግጧል።

ድሬዳዋ ከተማ በ2014 የውድድር ዓመት በብዙ መስፈርቶች የተረጋጋ አልነበረም። የውድድር ዓመቱ ሲጀምር በአሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ እየተመራ ሊጉን ቢቀርብም ክለቡ ለአሰልጣኙ ከዘጠኝ የጨዋታ ሳምንታት በላይ ዕድል ሳይሰጥ ፊቱን ወደ ሌላ አሰልጣኝ አዙሯል። በምትካጨውም የክለቡን የቴክኒክ ዳይሬክተር ፎዐድ የሱፍ በመንበሩ ሾሞ በመቀመጫ ከተማው በተደረጉትን ጨዋታዎች ለመነቃቃት ቢያስብም ውጥኑ ሳይሰምር ከ6 ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው 18 ነጥቦች 5ቱን ብቻ በማሳካት ዳግም ሌላ አሰልጣኝ ለማግኘት ማማተር ይዟል። በዚህም አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ ቡድኑን ተረክበው ከባዱን ያለመውረድ ትንቅንቅ ተጋፍጠው በመግቢያችን እንደገለፅነው በመጨረሻው ጨዋታ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሊግ እርከን ውድድር ለ7ኛ ተከታታይ ዓመት መሳተፉን አረጋግጧል።

በውድድር ዓመቱ ከተደረጉት 30 ጨዋታዎች 8ቱን በማሸነፍ 9ኙን አቻ ወጥቶ በቀሪዎቹ 13 ፍልሚያዎች ተረቶ አጠቃላይ 33 ነጥቦችን በመያዝ ከወራጅ ቀጠናው በአንድ ነጥብ እና አንድ ደረጃ ብቻ ከፍ ብሎ ያጠናቀቀው ድሬዳዋ ከተማ ዘንድሮ ካለፉት ዓመታት የታችኛው የደረጃ ፉክክር ለመውጣት ቆርጦ የመጣ ይመስላል። ክለቡ በዝውውር መስኮቱ ትንሽ ዘግየት ብሎ መሳተፍ የጀመረ ቢመስልም አህጉራዊ ወድድር ከሌለባቸው ክለቦች ቀድሞ የ2015 የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ጀምሯል።

ድሬዳዋ ከተማ ለአዲሱ የውድድር ዓመት ያለፉትን ሁለት ዓመታት በመከላከያ (በአሁኑ ስሙ መቻል) የአሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ምክትል የነበሩትን አሰልጣኝ ዮርዳኖስ አባይን ሐምሌ 7 በዋና አሠልጣኝነት መንበር ሾሟል። አሠልጣኝ ዮርዳኖስ አባይም በረዳትነት ሽመልስ አበበ እና መሐመድ ጀማልን አምጥቶ ከስድስት ወራት በፊት ከተቀጠሩት ዓለምሰገድ ወልደማርያም ጋር በማቀናጀት የአሠልጣኝ ቡድን አባላቱን እንደ አዲስ አደራጅቶ በዝውውር መስኮቱ ላይ መሳተፍ ጀምሯል።

“የዝውውር ሂደቱ ጥሩ ነው። እኔ እንደምፈልገው ነው የሆነልኝ ፤ እኔ የምፈልጋቸውን ተጫዋቾች ነው ክለቡ ያመጣልኝ ስለዚህ ጥሩ ነው።” የሚል ሀሳባቸውን የሰጡን አሠልጣኝ ዮርዳኖስ አባይ ከዓምናው የቡድኑ ስብስብ መጠነኛ የተጫዋች ለውጦችን አድርገዋል። ከዓምናው ስብስብም ከ14 በላይ ተጫዋቾችን በመቀነስ በዝውውር መስኮቱ የግብ ዘቡ ዳንኤል ተሾመን፣ ተከላካዮቹን እያሱ ለገሰ፣ አሳንቴ ጋድፍሬድ እና አሰጋኸኝ ጼጥሮስ፣ አማካዮቹ ዮሴፍ ዮሐንስ፣ ኤሊያስ አህመድ፣ ያሬድ ታደሰ፣ ጫላ በንቲ እንዲሁም አጥቂዎቹ ቢኒያም ጌታቸው እና ሙሲጊ ቻርለስ ወደ ቡድኑ አምጥተዋል። ከአስሩ አዲስ ተጫዋቾች ውስጥ አብዛኞቹ ከወገብ በታች የሚጫወቱ መሆኑ ደግሞ ቡድኑ ዓምና የነበረበትን ጨዋታን የመቆጣጠር እና ግቦችን የማስተናገድ ችግር ለመቅረፍ ያለመ ይመስላል። በተለይ የሊጉ አራተኛ ብዙ ግቦችን ያስተናገደውን የኋላ መስመር ለማሻሻል የተኬደው ርቀት ምናልባት በዘንድሮ የውድድር ዓመት መሻሻል ሊያስገኝ ይችላል። በዋናነት ደግሞ የቆሙ ኳሶችን ችግር በቁመታሙ አሳንቴ ጎድፍሬድ የመሬት ላይ የአንድ ለአንድ ግንኙነት ድክመቶችን ደግሞ በእያሱ ለገሰ ለመቅረፍ የሚያስችለው ግዢ አድርገዋል። ከመሐል ተከላካዮች ባለፈም በአዲስ አበባ ከተማ በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ረገድ ጥሩ አበርክቶ ያለው አሰጋኸኝ ጼጥሮስን ጨምሮ ከተከላካዮች ፊት የሚሰለፈው አማካዩ ዮሴፍ ዮሐንስ ለቡድኑ ጥንካሬ እንደሚሰጡ ይገመታል።

በማጥቃቱም ረገድ ዓምና በጨዋታ በአማካይ አንድ ግብ እንኳን ማስቆጠር ተስኖት የነበረው ቡድኑ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ቢይዝም የሳጥን ውስጥ ጨራሽ ተጫዋች ግን የሊጉ ጅማሮ መቃረቢያ ድረስ አላገኘም ነበር። እርግጥ በአዲስ አበባ ከተማ ያሳለፈው ቢኒያም ቡድኑን ቢቀላቀልም ተጫዋቹ ያለበት የአጨራረስ ችግር በቶሎ ቡድኑ እንዲታከም አያደርገውም። በአማራ ባንክ ጣና ዋንጫ ውድድር ላይ ከተሳተፈው ሞደርን ጋዳፊ የተዘዋወረው ሙሲጊ ቻርለስ ምናልባት ሊጉን እና ሀገሩን የመላመድ ችግር የማይገጥመው ከሆነ ዋነኛ አማራጭ መሆኑ የማይቀር ነው። አሠልጣኙ “የመጡት ተጫዋቾች በደንብ ነው የተዋሃዱት ፤ ምንም የከበዳቸው ነገር የለም።” እንዳሉት ከሆነ ጥሩ እድገት በቡድኑ ዋነኛ ክፍተት ላይ የሚፈጠር ይሆናል።

አዳዲስ እና ነባር ተጫዋቾችን ነሐሴ 5 እንዲሰባሰቡ የጠራው ክለቡ በማግስቱ የህክምና ምርመራ አከናውኖ ወደ ሀሮማያ እንዲያቀኑ በማድረግ በሀሮማያ ዩኒቨርስቲ ከነሐሴ 8 ጀምሮ መደበኛ ልምምድ ጀምሯል። ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በተከናወነው የአማራ ባንክ ጣና ዋንጫ ውድድር ላይ ከመሳተፉ በፊትም ለ25 ተከታታይ ቀናት በሀሮማያ ዩኒቨርስቲ መቀመጫውን አድርጎ ሲዘጋጅ ከርሟል። “የቅድመ ውድድር ዝግጅት ላይ ግዴታ ተጫዋቾች ወደምትፈልገው ደረጃ ለማድረስ የትንፋሽ ፣ የአካል ብቃት እና የስነልቦና ሥራዎች እንዲሁም በዲሲፕሊን ጭምር ብዙ ነገር ነው ምትሠራባቸው። እዛ ላይ ነው ብዙ ነገር የምትጨርሰው። ስለዚህ የወዳጅነት ጨዋታ ከማድረጋችን በፊት እነዛን ነገሮች በደንብ ሰርተናል።” ካሉ በኋላ ከአሠልጣኝ ቡድኑ በተጨማሪ በዩኒቨርስቲው በተለያዩ ዘርፎች የሚገኙ ባለሙያዎችም እርዳታ እና እገዛ እንዳደረጉላቸው አመላክተዋል።

በብዙ መስፈርቶች ዓምና ችግሮች የነበሩበት ድሬዳዋ ከተማ እነዛን ችግሮች ለመቅረፍ ሁለንተናዊ ሥራዎች እንደሚጠብቁት እሙን ነው። ከላይ የገለፅናቸው ግብ ከማስቆጠር እና ከማስተናገድ ውጪ ጨዋታን የመቆጣጠር ከፍተኛ ክፍተት ያለበት ቢሆንም ከምንም በላይ ደግሞ ለዓመታት የዘለቀው ላለመውረድ የመጫወት የሥነ-ልቦና ችግር ግዙፉ ቁስል ይመስላል። ሁሌ በዓመቱ መጀመሪያም ይህ ችግር እንደሚቀረፍ በወቅቱ የነበሩት አሠልጣኞች ሲናገሩ ቢሰማም በዓመቱ መገባደጃ ላይ ግን የተለመደው ግብ ግብ ሲቀጥል ይታያል። ያሁኑ አሠልጣኙም ዘንድሮ ይህንን ለማሻሻል እንደሚሰሩ ጠቁመው የበፊቱን የክለቡን ውጤት መርሳት እንደሚፈልጉና ሥራዎች ላይ ብቻ ማተኮረ እንደሚሹ ጠቁመዋል። “ከዓምና የደረሰኝ ሪፖርት ይጠቅመኛል ብዬ አላስብም። ምክንያቱም ያለፈውን ነገር መርሳት አለብኝ። ከውጪም ሆኘ አውቀዋለሁ ምን አይነት ነገር ሊፈጠር እንደሚችል እና ምን እንደተፈጠረ እንደነበር። ከውጪ ሆነን ማናችንም ልንረዳው የምንችለው ነገር ስለሆነ ያን ነገር ስለማውቀው ስገባ ምን አይነት ነገር ነው ማድረግ ያለብኝ የሚለውን ነገር ነው ትኩረት ያደረኩት። እነዛን ችግር ተፈጠረ የሚባሉትን ነገሮችን ማንም ሳይነግረኝ በደንብ ነው ላውቃቸው የምችለው ፤ የሚታወቅም ነው። ስለዚህ እነዛ ነገሮች ላይ ተዘጋጅቼበት ነው ኃላፊነት የተሰጠኝ ፤ በደንብ ተዘጋጅቼበት ነው የገባሁት። ብዙ ክለቦች ላይ የሚያጋጥም ነገር ነው። ” ካሉ በኋላ ዋናው ነገር “ቡድኑን አንድ ለማድረግ እና ተጫዋቾችን ለማፋቀር እንዲሁም ትናንት ከትናንት ወዲያ የነበረውን የድሬን ጥሩ ያልሆነ ስም ለመለወጥ በዐምሮም ሆነ በሌላው ነገር ጥሩ ዝግጅት ላይ ነን። ተጫዋቾቼ ደግሞ ጥሩ ናቸው። በዲሲፕሊን እስካሁን ባየሁት ነገር ጥሩ ነው። ስለዚህ እንሠራለን ፤ የሠራ ሰው ደግሞ ጥሩ ነገር የማያመጣበት ምንም ምክንያት የለም። ግን ሥራ ይፈልጋል። ውጤት ለማምጣት እግርኳሱ ስነ-ስርዓት ይፈልጋል። እኔ የመጀመሪያው ዋና ነገሬ ደግሞ በእግርኳሱ ዲሲፕሊን ነው። ዲሲፕሊንድ ያልሆነ ተጫዋችም አሰልጣኝም የትም ውጤታማ ይሆናል ብዬ ስለማላስብ እነዛ ነገሮች አልከበዱኝም። ሠርተንባቸዋል ያው ወደፊት ደግሞ እናየዋለን።” ብለዋል።

ጨዋታን ለማሸነፍ በሁለቱ የፍፁም ቅጣት ምት ክልሎች ሥል እና ጠንካራ መሆን የሚገባ ሲሆን ድሬዳዋ ግን በሁለቱ ክፍሎች የወረደ አፈፃፀም ነበረው። በአንፃራዊነት ከኋላ ያለው ማንጠባጠብ በአንፃራዊነት በተሻሉ ተጫዋቾች ግዢ ለመድፈን መጣሩና በአቋም መፈተሻ እንዲሁም በአማራ ባንክ ጣና ዋንጫ ውድድር በታየው የ5 ተከላካዮች ጥምረት ለመሸፈን መጣሩ ጥሩ መሆኑ ታይቷል። ከኳስ ውጪ የነበረው የቡድኑ የመታተር ልኬትም እጅግ ከፍ ማለቱን በቅድመ ውድድር ጨዋታዎች አስተውለናል። ይህ ደግሞ ተጋጣሚ በቀላሉ ግብ እንዳያስቆጥርበት የሚያደርግ ይሆናል። አማካይ መስመር ላይም ከኳስ ጋርም ሆነ ከኳስ ውጪ ምቾት ያላቸው ተጫዋቾች ስብስቡ ውስጥ ስለሚገኙ እነርሱን የማዋቀር ስራ ብቻ የሚፈለግ ይመስላል። ከሁሉም በላይ ግን ፊት መስመር ላይ ያለው ችግር በውድድር ዓመቱ ቡድኑን እንዳይጎዳው ያሰጋል።

ከሄኖክ አየለ እና ማማዱ ሲዲቤ ጋር ከተለያየ በኋላ ተፈጥሯዊ የሳጥን ውስጥ አጥቂ ለማግኘት ሲጥር የነበረው ክለቡ ባሳለፍነው የውድድር ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ ከ530 ደቂቃዎች በላይ ግልጋሎት ያልሰጠውን ቢኒያም ጌታቸው ብቻ ወደ ስብስቡ ቀላቅሎ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ጀምሮ ነበር። አጥቂው ጉልበታም፣ ፈጣን እና ታጋይ ቢሆንም ከፍተኛ የአጨራረስ ችግር እንዳለበት ግን በእነዛ በቋሚነትም ሆነ ተቀይሮ ገብቶ ባገለገለባቸው አጠቃላይ የ16 ጨዋታዎች ተሳትፎ በሚገባ አይተናል። ይህንን ተከትሎ ፊት መስመር ላይ የሚኖረው ስልነት ጥያቄ ውስጥ ቢወድቅም የቡድኑ አሠልጣኝ ዮርዳኖስ ዓባይ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ታሪክ ድንቅ ከተባሉ አጥቂዎች መካከል አንዱ ስለሆነና እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የሊጉ የአንድ ውድድር ዓመት ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ሪከርድን የያዘ ስለነበር የቢኒያምን የአጨራረስ ክህሎት ያሳድጋል የሚል እምነት አለ። ይህንን ማምጣት ትንሽ ዘለግ ያለ ጊዜ የሚወስድ መሆኑን በመገንዘብ እና የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች እና የአማራ ባንክ ጣና ዋንጫ ውድድር ላይ የታየውን ክፍተት በመረዳት ቡድኑ ዳግም ገበያ በመውጣት በዚሁ ውድድር ድንቅ ብቃት ሲያሳይ የነበረውን የሞደርን ጋዳፊው አጥቂ ሙሲጊ ቻርለስን አስፈርሟል። አሠልጣኙም “ለማሸነፍ ጎል ማስቆጠር አለብህ ፤ ሲገባብህ ደግሞ ወደ መሸነፍ እየሄድክ ነው ማለት ነው። ስለዚህ ማስቆጠር አለብህ ለማሸነፍ ከአንድ ለባዶ ተነስተህ ለማሸነፍ ማግባት መቻል አለብህ ፤ ስለዚህ የምታስቆጥረው ደግሞ ወደፊት እየሄድክ ነው ማለት ነው። እና ወደፊት እየሄድክ ደግሞ እንዴት ነው የምታስቆጥረው? ለሚለው ሥራዎች አሉ። እነርሱን በልምምድ ላይ በደንብ እየሰራን ነው።” በማለት ስጋቶቹ ሊጉ ላይ እንዳይፈጠሩ እየተሰራ እንደሆነ ጠቁሟል።

በዋና አሠልጣኝነት መንበር በሀገሪቱ ከፍተኛ የሊግ እርከን ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያሰለጥነው አሠልጣኝ ዮርዳኖስ ከመጀመሪያ ስራው ጋር በተገናኘ ስለሚጠብቀው ሥራ ይህንን ይናገራል። “ውጤት ይመጣልሃል አይመጣልህም የሚለው በሥራህ ነው የሚወሰነው። እኔ ምንም አይጨንቀኝም ምክንያቱም መሸነፍ እና አቻ መውጣት አለ። ጥሩ ያልሆነ ዓመት ታሳልፋለህ ግን እነዛ ነገሮች ሊያጋጥሙት እንደሚችሉ ማወቅ ያስፈልጋል። ማንም አሰልጣኝ ላይ ያጋጥማል። ይሄው ትላልቅ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ላይ እናያለን። ትንሽ መውረድ አለ ፤ ከፍ ማለትም አለ። ግን እነዛ ነገሮች ሁሉ ጥሩ እያሸነፍክ ጥሩ ነገር እየጠበቅክ ለመሄድ ከተጫዋቾቹ ጋር ያለህ ነገርና ሜዳ ላይ የምትሰጣቸው ነገር እያንዳንዱ ነገር ጥንቃቄ ልታደርግባቸው ይገባል። እኔ ደግሞ እያንዳንዱን ነገር የምፈልገው እንዴት መጫወት እንዳለባቸው እና እንዴት ሄደው ጎል ማስቆጠር እንዳለባቸው እያንዳንዱን ነገር በልምምድ ላይ እያሰራው ነው። ስለዚህ ከሠራን የአካል ብቃት እና ትንፋሹ ይመጣል። ዲሲፕሊንድ ከሆኑ ተጫዋቾቹ ደግሞ እንዴት ውጤት አይመጣም? ስለዚህ እዛ ላይ ነው መሥራት የያዝነው።”

አሠልጣኙ ጨምሮም “ጥሩ አልሸነፍ ባይነት ይዞ ወደሜዳ የሚገባ ቡድን ፤ አንድ ተጫዋች ገብቶ ሜዳ ላይ ቆሞ የማይታይበት እና ሁሉም ታታሪ የሆነበት ቡድን ለመስራት እየጣርን ነው። ውጤት የሚመጣበትን መንገድ ደግሞ በደንብ ሠርተንበታል ተዘጋጅተንበታል። ስለዚህ በዛ መንገድ ተጫወቱ ብለህ ትገባለህ ስለዚህ እልህ ያለው ፍላጎት ያለው ለተመልካች ጥሩ እግርኳስ የሚጫወት ቡድን ፣ በውጤት የታጀበ ቡድን ነው ይዘን የምንቀርበው ብዬ ነው የማስበው።” በማለት በአዲሱ ክለቡ የሚጠበቀውን የጨዋታ መንገድ በአጭሩ አስረድቶናል።

በቡድኑ ውስጥ በዘንድሮ የውድድር ዓመት ተፅዕኖ ይፈጥራሉ ተብለው የሚጠበቁ በርከት ያሉ ተጫዋቾች አሉ። አማካይ መስመር ላይ በክረምቱ የዝውውር መስኮት የፈረሙት ዮሴፍ ዮሐንስ እና ኤሊያስ አህመድ ከጨዋታ ቁጥጥር ጋር ተያይዞ ለቡድኑ እድገት እንደሚያመጡ ሲታሰብ እንደ ብሩክ ቃልቦሬ ካሉ ተጫዋቾች ጋር የሚያደርጉት ፉክክርም ይጠበቃል። በኋላው መስመር ላይ የቁመተ መለሎው አሳንቴ ጎድፍሬድ እና ቀልጣፋው ኢያሱ ለገሰ መምጣትም እንደገለፅነው የኋላ መስመሩ ላይ መሻሻል የሚያመጣ ሲሆን ሁለቱ ተጫዋቾችም ተፅዕኖ ፈጣሪ ሊሆኑ ይችላሉ። ከዚህ ባለፈ የግብ ዘቡ ዳንኤል ተሾመ ከቡድኑ ሁለተኛ አምበል ፍሬው ጌታሁን ጋር የሚያደርገው ፉክክር ትልቅ ግብዐት እንደሚሆን ይታሰባል።

ድሬዳዋ ከተማ የ2015 የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ጨዋታውን የፊታችን ቅዳሜ 10 ሰዓት ከሲዳማ ቡና ጋር የሚያደርግ ይሆናል።

የድሬዳዋ ከተማ የ2015 ስብስብ

ግብ ጠባቂዎች

30  ፍሬው ጌታሁን
33  አብዩ ካሣዬ
27  ዳንኤል ተሾመ
31 ኦብሳ ኤልያስ

ተከላካዮች
13  መሳይ ጳውሎስ
14  አማረ በቀለ
3    ያሲን ጀማል
5   ሚኪያስ ካሣሁን
2   እንየው  ካሣሁን
21 አሰጋኸኝ ጼጥሮስ

45 አሳንቴ ጎድፍሬድ

አማካዮች
9 ኤልያስ አህመድ
10 ያሬድ ታደሰ
8 ሱራፌል ጌታቻው
24 ከድር እዮብ
6 ዮሴፍ ዮሐንስ
16 ብሩክ ቃልቦሬ
4  አቤል አሰበ
47 አብዱልፈታ ዓሊ
23 ወንድወሰን ደረጀ
43 ሄኖክ ሀሰን
40 አድናን መኪ

አጥቂዎች
18 ቢኒያም ጌታቸው
11 ጋዲሳ መብራቴ
19 ሙኸዲን ሙሳ
17 አቤል ከበደ
77 በኃይሉ ተስፋዬ
7 ጫላ ባንቲ
20 መሐመድ አብዱለጢፍ

የአሠልጣኝ ቡድን አባላት
ዋና አሠልጣኝ – ዮርዳኖስ ዓባይ
1ኛ ምክትል አሠልጣኝ – ሽመልስ አበበ
2ኛ ምክትል አሠልጣኝ – ዓለምሰገድ ወልደማርያም
የግብ ጠባቂዎች አሠልጣኝ – መሐመድ ጀማል
የህክምና ባለሙያ – አሥራት ለገሠ
ወጌሻ – ጌታቸው ወልዴ
የቡድን መሪ – ቶፊቅ ሀሰን