የክለቦች የውድድር ዘመን ቅድመ ዳሰሳ | ቅዱስ ጊዮርጊስ

ከሦስት የውድድር ዘመናት በኋላ ዓምና ዳግም የሊጉን ዘውድ የደፉት ፈረሰኞቹ በተረጋጋ የቡድን ስብስብ ዘንድሮም የተሻሉ ሆነው ስለመቅረብ ያልማሉ ፤ ሶከር ኢትዮጵያም በተከታዩ ዳሰሳ ለአዲሱ የውድድር ዘመን ስላደረጉት ዝግጅት ልታስቃኛችሁ ወዳለች።

በ2014 የውድድር ዘመን በ30 የጨዋታ ሳምንታት በአንዱ ብቻ ሽንፈትን በማስተናገድ በድምሩ 65 ነጥቦች በማሳካት ከሦስት የውድድር ዘመናት ቆይታ በኋላ አስራ አምስተኛ የሊግ ክብራቸውን ያሳኩት ፈረሰኞቹ ለ16ኛ የሊግ ዋንጫቸው የሚፋለሙ ይሆናል። ቡድኑ ከአምናው ድል ማግስት ባሳለፍነው የውድድር ዘመን ከመጀመሪያው የጨዋታ ሳምንት በኋላ ሰርቢያዊው አሰልጣች ዝላትኮ ክሪምፓቲችን ተክቶ በጊዜያዊነት እየመራ ክለቡን ከህልሙ ማገናኘት የቻለውን አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታን በመጪዎቹ ዓመታት ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት እንዲመራ በመሰየም ነበር የጀመሩት።

“ምንም ትልቅ ልዩነት የለውም። በፊትም ምክትል አሰልጣኝ እያለሁ እኔው ነበርኩ ሁሉንም ሥራ የምሠራው ፤ አሁንም እኔ ነኝ የምሠራው። ዋናው ቁምነገሩ ተጫዋቾች ያላቸውን ብቃት ጠብቀው ዓመቱን ሙሉ የሚያጫውት አቅም እና ጠንካራ ህብረት በመፈጥር ስብስቡን አንድ አድርጎ ውጤት ለማምጣት ነው ሁሌም በጊዮርጊስ ቤት የምንሠራው። አሁንም ይህን ነው እያደረግን ያለነው።” ሲል ይናገራል።

በክረምቱ የዝውውር መስኮት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአንፃራዊነት ከሌሎች ክለቦች ጋር ሲተያይ የተረጋጋ የሚባል መስኮትን አሳልፈዋል። በዚህም በተቻለ መጠን ቡድኑን ለስኬት ያበቁ ተጫዋቾችን በማቆየት የተወሰኑ ስብስቡን ሊያሻሽሉ ይችላሉ ተብለው የታመነባቸውን ተጫዋቾች ለመቀላቀል ጥረት አድርገዋል። በፈረሰኞቹ ቤት ምናልባት ስለለቀቁ ተጫዋቾች ካነሳን አምና ጥሩ አበርክቶ የነበራቸው እና ከክለቡ ጋር ስለመቆየታቸው ተነግሮ የነበሩት ከነዓን ማርክነህ እና የዓብስራ ተስፋዬን ስለማጣቱ ነው። ከዚህ ባለፈም ምንም እንኳን በቂ ግልጋሎት ሜዳ ላይ መስጠት ባይችሉም በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ለዘጠኝ ዓመታት ቆይታ ያደረገው ሳልሀዲን በርጌቾን ጨምሮ ቡልቻ ሹራ እና ያሬድ ሀሰንም እንዲሁ ከአምናው ስብስብ የሌሉ ተጫዋቾች ናቸው።

ከክለብ አልፎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተቀዳሚ የግራ መስመር ተከላካይ የሆነው ረመዳን የሱፍ ፈረሰኞቹን የተቀላቀለ ሲሆን ከእሱ በተጨማሪ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሊጉ ከተመለከትናቸው ጥሩ አቅም ካላቸው ፈጣሪ አማካዮች አንዱ የሆነው ዳዊት ተፈራ እና አምና በመከላከያ ከመስመር እየተነሳ የቡድኑ ማጥቃት እንቅስቃሴ አድራጊ ፈጣሪ የነበረው ቢኒያም በላይም እንዲሁ በቢጫ እና ቀዩ መለያ የምንመለከታቸው ተጫዋቾች ናቸው።

አሰልጣኝ ዘሪሁንም አጠቃላይ ቡድኑ በክረምቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያስፈረማቸው ተጫዋቾች በድንገት የመጡ ሳይሆን ዓመቱን ሙሉ ሲከታተሏቸው የነበሩ ስለመሆናቸው ያነሳሉ ፤ “የቅድመ ውድድር ዝግጅት መጨረሻ ላይ አይደለም ይሄንን የወሰነው ፤ ቀደም ብለን ሊጉ ላይ ከመጀመሪያው ጀምሮ ጨዋታዎችን እያየን ማስታወሻ ይዘን ከአስር በላይ ተጫዋቾችን ዝርዝር ይዘን ስንከታተል ነበር። ሁሌ በየጨዋታው ጥሩ የሚጫወቱ ተጫዋቾችን እናያቸዋለን። በግራ መስመር በኩል ክፍተት ነበረብን በዚህ ቦታ ላይ የተሻለ ነገር የነበረውን ረመዳንን አምጥተናል። የመሃል አማካይ ላይ እና ክንፍ ላይ ዳዊት እና ቢያንምን አምጥተናል። ይሄ እኛ ያየነው እና ለቡድናችን ጠንካራ ጎን ይሆናሉ ብለን አይተን እና ተስማምተንበት ነው የመጡት።” በማለት ክለቡ ስለተከተለው የዝውውር ሂደት ሀሳባቸውን ይሰጣሉ።

ቅዱስ ጊዮርጊሶች ተጫዋቾችን ከማስፈረም ባለፈም የወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን ውልም ያራዘሙበት ክረምት ነበር። በመስኮቱ የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት አቤል ያለውን እና የሄኖክ አዱኛን ውል ማራዘም የቻሉ ሲሆን በሊጉ ዋዜማ ደግሞ ወደ ግብፅ ለማምራት ቆርጦ የነበረውን አማኑኤል ገ/ሚካኤል እና አዲስ ግደይንም ግልጋሎት ለተጨማሪ ዓመት ማግኘት ችለዋል።

ሊጉ ከተጠናቀቀ ከ10 ቀናት በኋላ ዳግም ለአዲሱ የውድድር ዘመን ዝግጅት የተሰባሰቡት ፈረሰኞቹ ከሐምሌ 16 አንስቶ መቀመጫቸውን ቢሾፍቱ በሚገኘው የክቡር ይድነቃቸው ተሰማ አካዳሚ በማድረግ ዝግጅታቸውን ከውነዋል። ነገር ግን በዚህ ሂደት ቡድኑ በብሔራዊ ቡድን ግልጋሎት ሳቢያ በርከት ያሉ ቁልፍ ተጫዋቾችን በወጥነት የዝግጅቱ አካል ለማድረግ አለመቻሉ ለቡድኖች የዓመቱን አቋም መስመር ለማስያዝ ወሳኝ የሆነው የቅድመ ውድድር ዝግጅቱ የተቆራረጠ እንዲሆን ያስገደደ ነበር። በውስን ተጫዋቾች አመዛኙን የዝግጅት ጊዜ ያሳለፉት ፈረሰኞቹ ለዝግጅታቸው ይረዳቸው ዘንድ ከታንዛኒያው ሲንባ እና ከሱዳኑ ኤል ሜሪክ ጋር የወዳጅነት ጨዋታዎችን እንዲሁ ማድረግ ችለዋል።

ለሁለት ውድድሮች ራሳቸውን በክረምቱ ሲያዘጋጀለ የቆዩት ፈረሰኞቹ ከዝግጅታቸው መልስ በአዲሱ ዓመት መባቻ “በትልቁ መድረክ” ክለቡ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ አጥብቆ በሚፈልገው የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ አሁንም ሩቁ መጓዝ ሳይችሉ ህልማቸው ገና በቅድመ ማጣሪያው ተገድቦ ቀርቷል። የሱዳኑ አል ሂላል ኡምዱሩማንንም የገጠመው ቡድኑ በመጀመሪያው ጨዋታ ባህር ዳር ላይ 2-1 በተጠናቀቀው ጨዋታ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ባስተናገዱት ግብ ዋጋ ለመክፈል ተገደው ከውድድሩ ተሰናብተዋል።

የክለቡ ዋናው ቡድን በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የመልስ ጨዋታ ለማድረግ ወደ ሱዳን ማምራቱን ተከትሎ በ16ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአዲስ ቡድን ብቅ እንዲሉ ያስገደደ አጋጣሚ ነበር። በአሰልጣኝ ሳምሶን ሙሉጌታ መሪነት ከዕድሜ እርከን ቡድኑ በተገኙ እና ከሱዳኑ ጉዞ በተቀነሱ ተጫዋቾች በተገነባ ስብስብ ውድድሩ ላይ የተካፈሉ ሲሆን ተስፈኞ ፈረሰኞቹም ተስፋ ሰጪ ከነበረ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ጋር በንፅፅር ለዋናው ቡድናቸው የቀረበን ስብስብ ይዘው ከቀረቡ የሊጉ ቡድኖችን ሁሉ ልቀው በውድድሩ አሸናፊ መሆን መቻላቸው የክለቡ ደጋፊዎችን በደስታ ያስፈነጠዘ አጋጣሚ ነበር።

አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የተሻለ እንቅስቃሴ ስላደረጉ ተስፈኛ ተጫዋቾች ሲናገር ፤ “ሁሉም ውድድሩ ላይ የተጫወቱ ተጫዋቾች ሁለት እና ሦስት ዓመት አብረውኝ የሰሩ ልጆች ናቸው። ዓምናም በታችኛው ቡድን ጥሩ እንቅስቃሴ ስላደረጉ ወደዚህ አምጥቻቸው እኔጋ እየሠሩ ነበር።  አቅም ያላቸው ልጆች ናቸው። እነርሱ ራሳቸውን ከፍ እያደረጉ አቅማቸውንም እያሳዩ ነው።” ያለ ሲሆን አክሎም አብዛኞቹ ከሁለት ተጫዋቾች (አቤሴሎም እና ብሩክ) ውጭ በተለያየ ጊዜ ከዋናው ቡድን ጋር ሆነው ልምምድ እየሰሩ የነበሩ መሆናቸውን አንስቶ በሂደት ራሳቸውን በደንብ ማሳደግ ከቻሉም የቅዱስ ጊዮርጊስ “አስቀጣዮች ናቸው” ሲል ይገልፃቸዋል።

እርግጥ በዋናው የቅዱስ ጊዮርጊስ ስብስብ ውስጥ ካሉት አማራጮች አንፃር እነዚህን ወጣቶች በስፋት መጠቀም ከባድ ቢመስልም ባለፉት ሁለት የውድድር ዘመናት በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ካሳዩት ነገር አንፃር ከአምናው በተሻለ የጨዋታ ደቂቃ እንዲያገኙ የሚያስገድድ ብቃት ስለማሳየታቸው ግን ምስክርነትን መስጠት ይቻላል። በተለይ ደግሞ በከተማ ዋንጫው በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ያጠናቀቀው ሀብቶም ገ/እግዚአብሔር ጉዳት ለሚያጠቃው የአጥቂ መስመር አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እየተዘጋጀ ያለ ይመስላል።

የሊግ አሸናፊ ከመሆን በላይ በቀጣዩ የውድድር ዘመን ክብርን ማስጠበቅ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ በብዙ ቡድኖች የተመለከትነው እግርኳሳዊ እውነታ ነው። ነገር ግን አሰልጣኙ ዋናው ይህንን አባባል ፉርሽ ካደረጉ ክለቦች መካከል በሀገራችን እግርኳስ አውድ “የተሻለውን ቅዱስ ጊዮርጊስ ማሳየት” ስለመሆኑ ያነሳሉ።

“ሁሌም ቢሆን የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾችን አስተባብሬ ሁሉን ነገር አድርገን የተሻለውን ቅዱስ ጊዮርጊስ ለማሳየት ነው የምንፈልገው። 2014 ላይ ጥሩ ውጤት አምጥተን ዋንጫውን አንስተናል በ2015ም ደግሞ ዓምና የሠራናቸውን ስህተቶችና ጥሩ ጎኖቻችንን አይተን እና አስተካክለን። የተሻለውን ቅዱስ ጊዮርጊስ ለመሥራት በጠንካራ ዝግጅት እና በጥሩ መንፈስ አዲሱን የውድድር ዘመን ለመጀመር ባህርዳር ከተማ ገብተናል።”

ብዙም ባልተለወጠ ስብስብ ወደ አዲሱ የውድድር ዘመን የሚቀርቡት ፈረሰኞቹ ያለፈውን ዓመት ስኬት መድገም የሚሹ ከሆነ በዋነኝነት የነበራቸውን የቡድን መንፈስ እና አንድነትን ማስቀጠል ቀዳሚው የቤት ስራቸው ነው። ከዚህ ባለፈም ሜዳ ላይ ደግሞ የነበራቸውን የመከላከል ጥንካሬ ማስቀጠል እንዲሁ ዓብይ ጉዳያቸው መሆን ይኖርበታል ፤ በአማካይ በሦስት ጨዋታ አንድ ግብ ያስተናግድ የነበረው እና በ30 ጨዋታዎች 11 ግቦችን ያስተናገደው ጠንካራ የመከላከል መዋቅር ዘንድሮም ቡድኑን ተፎካካሪ ሆኖ የሚቀጥል ከሆነ ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው ይጠበቃል።

ከዚህ ባለፈ ቡድኑ ሻምፒየን ሆነው ባጠናቀቁበት የ2014 የውድድር ዘመን በተለይ በወሳኞቹ የሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች ሆነ በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ እንደተመለከትነው የቅዱስ ጊዮርጊስ የፊት መስመር በተደጋጋሚ የተጫዋቾች ጉዳት ምን ያህል እንደታመሰ አስተውለናል። በመሆኑም በአማራጮች የተሞላ የሚመስለውን ይህን የአጥቂ መስመር ተሰላፊ ተጫዋቾች የጤንነት ሁኔታ ተጠብቆ ረዘም ያሉ ጨዋታዎችን ከጉዳት ነፃ ሆነው እንዲዘልቁ ማድረግ የአጠቃላይ የቡድኑ በተለይም የህክምና ክፍሉ ትልቅ ኃላፊነት መወጣት ይኖርበታል። በማጥቃት ጨዋታ ረገድ በተለይ ፍጥነት መር ለሆነው የቡድኑ ማጥቃት ተጋጣሚዎች በአዲሱ የውድድር ዘመን ይበልጥ ተዘጋጅተው የመምጣታቸው ነገር የሚጠበቅ እንደመሆኑ ከዚህ አንፃር ቡድኑ ይህን ማጥቃት ይበልጥ በአማራጮች የተሞላ ማድረግ ይጠበቅበታል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ የመከላከል ጥንካሬ በስተጀርባ ቁልፍ ሚናን አምና መወጣት የቻለው ጋናዊው ፍሪምፖንግ ሜንሱ ዘንድሮም የቡድኑ ላይ ከፍ ያለ ተፅዕኖ ያሳርፋል ተብሎ ሲጠበቅ የአምና የሊጉ ኮከብ ተጫዋቾች ጋቶች ፓኖም እና ከጉዳት የተመለሰው ቶጎዋዊው እስማኤል ኦሮ-አጎሮ የቡድኑን የውድድር ዘመን ጉዞ ይወስናሉ ተብለው የሚጠበቁ ወሳኝ ተጫዋቾች ናቸው። ከዚህ ባለፈ በነበሩባቸው ክለቦች እጅግ ወሳኝ ሚና ይወጡ የነበሩት እና በአዲሱ የውድድር ዘመን በፈረሰኞቹ መለያ የምንመለከታቸው ተጫዋቾች በምን ያህል ፍጥነት ቡድኑን ተላምደው ቡድኑን ያግዛሉ የሚለው ይጠበቃል።

የዓምና የሊጉን ክብራቸውን ለማስጠበቅ የሚጫወቱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሊጉን አዲስ መጪዎቹን ኢትዮጵያ መድኖችን ቅዳሜ መስከረም 21 ላይ በመግጠም አሀዱ ብለው ይጀምራሉ።

የቅዱስ ጊዮርጊስ የ2015 ስብስብ ዝርዝር

ግብ ጠባቂዎች

30 ቻርልስ ሉክዋጎ
22 ባህሩ ነጋሽ
1 ተመስገን ዮሐንስ

ተከላካዮች

4 ምኞት ደበበ
24 ፍሬምፖንግ ሜንሱ
6 ደስታ ደሙ
3 አማኑኤል ተርፉ
14 ሄኖክ አዱኛ
2 ሱሌይማን ሀሚድ
18 ረመዳን የሱፍ
34 ሻሂዱ ሙስጠፋ

አማካዮች

15 ጋቶች ፖኖም
26 ናትናኤል ዘለቀ
5 ሀይደር ሸረፋ
20 በረከት ወልዴ
16 ዳዊት ተፈራ
7 ቢኒያም በላይ
27 አላዛር ሳሙኤል
31 ፉዓድ ሀቢብ
32 ፉዓድ አብደላ
28 ሚራጅ ሰፋ
29 አወት ኪዳኔ

አጥቂዎች

28 እስማኤል ኦሮ-አጎሮ
10 አቤል ያለው
17 አዲስ ግደይ
11 አማኑኤል ገ/ሚካኤል
12 ቸርነት ጉግሳ
19 ዳግማዊ አርዓያ
9 ተገኑ ተሾመ
33 ሀብቶም ገ/እግዚአብሔር
21 አቤል ዮናስ

የአሰልጣኝ ቡድን አባላት

ዋና አሰልጣኝ – ዘሪሁን ሸንገታ
ረዳት አሰልጣኝ – ደረጀ ተስፋዬ
የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ – ውብሸት ደሳለኝ
ቡድን መሪ – አዳነ ግርማ
ፐርፎርማንስ አናሊስት – አዲስ ወርቁ
የህክምና ባለሙያ – ሙሉቀን ቤካ እና ተስፋማርያም መኩርያ