የሊጉን ጅማሮ የሚያበስሩ ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ ወቅታዊ መረጃዎች

የ2015 ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ነገ ሲጀመር ከቀትር በኋላ የሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ የቡድን መረጃዎች እንደሚከተለው አጠናክረናል።

ተጠባቂው የሀገራችን ከፍተኛ የሊግ እርከን ውድድር የዘንድሮውን ፍልሚያ ነገ ማከናወን ይጀምራል። እናዳለፉት ሁለት ዓመታት በተመረጡ ከተሞች የሚደረገው ውድድሩ የመጀመሪያ አምስት ሳምንታት ቆይታውን በባህር ዳር ለማድረግ ተሰናድቷል። 7 እና 10 ሰዓትም በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ማሟሻውን የሚያደርግ ይሆናል።

የዓመቱ ውድድር የሚጀመረው ወልቂጤ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ በሚያደርጉት ትንቅንቅ ነው። በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በቅደም ተከተል 8ኛ እና 7ኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁት ሁለቱ ክለቦች በክረምቱ ለየቅል ጊዜያትን አሳልፈዋል። ሠራተኞቹ ከአሠልጣኝ ቅጥር ጀምሮ በርካታ ተጫዋቾችን ወደ ስብስባቸው ሲያመጡ አዞዎቹ በበኩላቸው በተረጋጋ ሁኔታ ብዙ የተጫዋች መውጣት እና መግባት ሳይፈፅሙ የቡድን ግንባታውን አስቀጥለዋል።

በዝውውር መስኮቱ 16 ተጫዋቾችን ያስፈረሙት ወልቂጤዎች ከተማዎች በነገው ጨዋታ የአብዛኞቹን አዳዲስ ተጫዋች ግልጋሎት ያገኛሉ። ምናልባት ግን በአማራ ባንክ ጣና ዋንጫ ላይ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ የተመረጠው ሳሙኤል አስፈሪ እና የቀድሞ የቡድን አጋሩ ቴዎድሮስ ሀሙ መጠነኛ ጉዳት ስላለባቸው የመሰለፋቸው ነገር አጠራጣሪ መሆኑና ነገ ጠዋት እንደሚወሰን ተጠቁሟል።

የሊጉ ሦስተኛው በዝውውር መስኮቱ ጥቂት ተጫዋቾችን ያስፈረመው አርባምንጭ ከተማ በበኩሉ በነገው ጨዋታ አጥቂው በላይ ገዛኸኝ እና ተከላካዮ አንድነት አዳነን በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ አይጠቀምም።

የሊጉን የመክፈቻ እና የሁለቱን ቡድኖች የመጀመሪያ የእርስ በርስ ግንኙነት ጨዋታ ኃይለየሱስ ባዘዘው በዋና ዳኝነት ፣ ተመስገን ሳሙኤል እና አበራ አብርደው በረዳት ዳኝነት እንዲሁም አሸብር ሰቦቃ በአራተኛ ዳኝነት ይመሩታል።

የእርስ በርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በ2014 የውድድር ዓመት የመጀመሪያ ግንኙነቶቻቸውን ያደረጉ ሲሆን በመጀመሪያው ዙር ያለግብ ተለያይተው በሁለተኛው ዙር ወልቂጤ ከተማ 3-0 አሸንፏል።

ወልቂጤ ከተማን የተመለከተ ያዘጋጀነውን የውድድር ዘመን ቅድመ ዳሰሳ ለማንበብ ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ : https://soccerethiopia.net/football/83964

አርባምንጭ ከተማን የተመለከተ ያዘጋጀነውን የውድድር ዘመን ቅድመ ዳሰሳ ለማንበብ ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ : https://soccerethiopia.net/football/83916

በደማቅ የደጋፊዎች ድባብ እንደሚከናወን የሚጠበቀው የውድድሩ አዘጋጅ ከተማ ባህር ዳር እና አዲስ አዳጊው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታ ደግሞ 10 ሰዓት ሲል ጅማሮውን ያደርጋል። የሊጉ ውድድር ሊጀመር ሲል የአሠልጣኝ መተካካት የፈፀመው ባህር ዳር ከተማ የዓምናውን ድንቅ የመክፈቻ ጨዋታ ደግሞ ዓመቱን በድል ለመጀመር ወደ ሜዳ ሲገባ ከአራት ዓመታት በኋላ ዳግም ወደ ሊጉ የተመለሱት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ደግሞ ምልሰታቸውን በፌሽታ ለማሳመር የሚያደርጉት ትንቅንቅ ይጠበቃል።

በ2014 የውድድር ዓመት ይዞ ያጠናቀቀው ደረጃ ቁጥር አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ያመጣው ባህር ዳር ከተማ ሦስት ተጫዋቾችን በነገው ጨዋታ አያገኝም። በዚህም የኋላ መስመር ተጫዋቾቹ ያሬድ ባየ እና ፈቱዲን ጀማል እንዲሁም የመስመር አጥቂው ፍፁም ጥላሁን ባጋጠማቸው ጉዳት ከፍልሚያው ውጪ ናቸው።

በአሳዳጊ አሠልጣኙ ክፍሌ ቦልተና እየተመራ ሊጉን የሚቀርበው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ደግሞ 13 ተጫዋቾችን አስፈርሞ አዲስ የቡድን ግንባታ ውስጥ የገባ ይመስላል። በነገው ጨዋታም አዲሶቹንም ሆነ ነባሮቹን የመጠቀም ዕድሉን ጉዳት እና ቅጣት አላጨናገፈበትም።

ይህን ጨዋታ ባምላክ ተሠማ በመሀል ዳኝነት ሲመራው ይበቃል ደሳለኝ እና ሙስጠፋ መኪ በረዳት ዳኝነት ለሚ ንጉሤ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ይመሩታል፡፡

ባህር ዳር ከተማን የተመለከተ ያዘጋጀነውን የውድድር ዘመን ቅድመ ዳሰሳ ለማንበብ ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ : https://soccerethiopia.net/football/8392

ኢትዮ ኤሌክትሪክን የተመለከተ ያዘጋጀነውን የውድድር ዘመን ቅድመ ዳሰሳ ለማንበብ ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ : https://soccerethiopia.net/football/83902