ሪፖርት | ኃይቆቹ ቡናማዎቹን በመርታት የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ሦስት ነጥብ አግኝተዋል

በካፍ ኮፌዴሬሽን ጨዋታ ምክንያት ተገፍቶ ዛሬ የተካሄደው ተጠባቂ ጨዋታ በሀዋሳ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ቡናማዎቹ ከወላይታ ድቻ ጋር ነጥብ ተጋርተው ከወጡበት ስብስባቸው መሐመድኑር ናስርን በጫላ ተሺታ ብቻ ሲለውጡ በአዲስ አዳጊዎቹ ለገጣፎ ለገዳዲዎች ያልተጠበቀ ሽንፈት ያስተናገዱት ኃይቆቹ ደግሞ መሐመድ ሙንታሪ፣ ላውረንስ ላሬቴ፣ ዳንኤል ደርቤ፣ ብርሀኑ አሻሞ እና ኤፍሬም አሻሞን አሳርፈው በምትካቸው አላዛር ማርቆስ ፣ ፀጋአብ ዮሐንስ፣ አብዱልባሲጥ ከማል ፣ ወንድማገኝ ኃይሉ እና ኢዮብ አለማየሁን አስገብተው ጨዋታውን ጀምረዋል።

ከዚህ ጨዋታ የሚገኘው ነጥብ ወሳኝ መሆኑን ተከትሎ ብርቱ ፉክክር ያስመለከቱን ቡድኖቹ ወደ ጎል በመድረስ የመጀመርያውን ግልፅ የማግባት አጋጣሚ ለመፍጠር አራት ደቂቃ የፈጀባቸው ቡናማዎቹ ነበሩ። በዚህም በፈጣን ቅብብል ሳጥን ውሰጥ የደረሱት ኢትዮጵያ ቡናዎች ሮቤል ተክለሚካኤል በጥሩ ዕይታ በጎሉ ፊት ለፊት ለነበረው አብዱልከሪም ወርቁ አቀብሎት አብዱልከሪም ወደ ጎልነት ቀየረው ሲባል ያመከነው አጋጣሚ አስቆጪ ሆኖ አልፏል። ተጨማሪ ጥቃት ለመሰንዘር ብዙም ያልቆዩት ቡናማዎቹ ከመሐል ሜዳ ከተከላካይ ጀርባ ወደ ቀኝ መስመር በረጅሙ ጫላ ተሺታ የተቀበለውን ኳስ ለብሩክ በየነ አሻግሮለት ብሩክ በግንባር በመግጨት ወደ ጎል ቢልክውም ወደ ውጭ የወጣው ሁለተኛውን የጎል ዕድል በስምንተኛው ደቂቃ ያገኙበት ነበር።

ግልፅ የጎል ማግባት አጋጣሚ በየትኛውም የሜዳ ክፍል ለመፍጠር የተቸገሩ የሚመስሉት ሀዋሳዎች በራሳቸው ሜዳ በቁጥር በመብዛት የቡናን የማጥቃት እንቅስቃሴ በማቋረጥ በረጃጅም ኳሶች እና በመልሶ ማጥቃት አደጋ ለመፍጠር ቢያስቡም ያን ያህል የተሳካላቸው አይመስልም ነበር። ነገር ግን በ33ኛው ደቂቃ በጨዋታው ቀዳሚ የሆኑበትን ግብ አግኝተው ቡናን መምራት ጀምረዋል። በተጠቀሰው ደቂቃ ከማዕዘን ምት አዲሱ አቱላ ያሻገረውን ኳስ ሙጂብ ከተከላካዮች ጋር ታግሎ በግንባሩ ሲገጨው በጎሉ ቅርበት የሚገኘው አብዱልባሲጥ ከማል አግኝቶት በመገልበጥ አስደናቂ ጎል አሳዳጊ ክለቡ ላይ አስቆጥሯል። የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከጎሉ በኋላ ውጥረት በተሞላበት እና አልፎ አልፎ በኃይል አጨዋወት እንቅስቃሴው እየተቆራረጠ ቢቀጥልም ኢትዮጵያ ቡናዎች ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ጎል በተለያዩ አቅጣጫዎች ለማግኘት ሙከራ ቢያድርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቶ ዕረፍት ሰዓት ደርሷል።

ሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በመጀመርያው አጋማሽ ከነበረው የሁለቱም ቡድኖች የጨዋታ እንቅስቃሴ ሳይለወጥ ቀጥሎ ቡናማዎቹ ከራሳቸው የሜዳ ክፍል ኳሱን ተቆጣጥረው በመጀመር ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ለመድረስ ቢሞክሩም የሀዋስ የመከላከል አጥር ጥሰው ጎሉን ለማግኘት ሲቸገሩ ታይቷል ፤ አልፎ አልፎም በቆሙ ኳሶች ጎል ለማስቆጠር ሲሞክሩ ቆይተዋል። በጥብቅ መከላከል በሚገኙ ክፍት ሜዳዎች በመልሶ ማጥቃት ጫና ሲያሳድሩ የነበረው ሀዋሳዎች በ53ኛው ደቂቃ ሁለተኛውን ጎል ለማግኘት ተቃርበው ነበር። በዚህም ዓሊ ሱሌይማን ወንድማገኝ ኃይሉ ከሳጥን ውጭ ከግራ ጠርዝ ያሻገረለትን ኳስ በጥሩ ሁኔታ ተቆጣጥሮ ወደ ጎል ቢመታው ግብ ጠባቂው በረከት አማረ እንደምንም አድኖበታል። የኢትዮጵያ ቡናን እንቅስቃሴ እያቀዘቀዙ ወደ ፊት ተጭነው መሄድን የቀጠሉት ሀዋሳዎች በ64ኛው ደቂቃም ከሳጥን ውጭ የተገኘውን ቅጣት ምት አፍሬም አሻሞ አጠንክሮ በመምታት ሌላ ጥቃት እንዲሰነዝሩ ቢያደርግም በድጋሜ በረከት አውጥቶባቸዋል።

ደቂቃዎች እየገፉ ሲሄዱ የአቻነት ጎል ፍለጋ አሰልጣኝ ተመስገን ዳና የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾቻቸውን ቀይሮ በማስገባት እንዲሁም በቁጥር በዝተው የሀዋሳ የሜዳ ክፍል ለመገኘት ቢጥሩም ይህ ነው የሚባል ዕድል ለመፍጠር አልቻሉም። በአንፃሩ የመከላከል አደረጃጀታቸው ስኬታማ የሆነላቸው ሀዋሳዎች ጎላቸውን ሳያስደፍሩ ቆይተዋል።

የመጨረሻው አራት ደቂቃ ጭማሪ የሁለት ጎሎችን ትዕይንት አስመልክቶናል። በቅድሚያም ሀዋሳዎች ጨዋታውን መግደል የቻሉበትን ጎል አስቆጥረዋል። በረጅም ወደ ኢትዮጵያ ቡና የሜዳ ክፍል የላኩትን ኳስ የቡናማዎቹ ተከላካዮች ከራሳቸው የሜዳ ክፍል ማራቅ ባለመቻላቸው ኤፍሬም አሻሞ በግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ተባረክ ሂፋሞ በግንባር በመግጨት ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል። ጨዋታው በዚህ ውጤት ተጠናቀቀ ሲበል ብሩክ በየነ ከአስራት ቱንጆ የተጣለለትን ኳስ በተመሳሳይ በግንባሩ በመግጨት ለኢትዮጵያ ቡና የማስተዛዘኛ አንድ ጎል በማስቆጠር ጨዋታው በሀዋሳ ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

የመጀመርያ ድላቸውን ያስመዘገቡት አሠልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ጨዋታው ጥሩ እንደነበር ጠቅሰው የተጋጣሚያቸውን እንቅስቃሴ ተቆጣጥረው በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ያደረጉት ጥረት ስኬታማ እንዳደረጋቸው ገልፀዋል። ተሸናፊው አሰልጣኝ ተመስገን ዳና በበኩላቸው በእንቅስቃሴ ረገድ ጥሩ ቢሆኑም ተረጋግተው ጎል አለማስቆጠራቸው ለሽንፈታቸው ምክንያት እንደሆነ ነገር ግን በሂደት ቡድናቸው እየተሻሻለ እንደሚመጣ ተናግረዋል።