ዳዊት ተፈራ ለሳምንታት ከሜዳ ይርቃል

በዘንድሮ የውድድር ዓመት ፈረሰኞቹን የተቀላቀለው ዳዊት ተፈራ ቀጣይ ጨዋታዎች ያመልጡታል።

በአራተኛው ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስ አዳማ ከተማን በረታበት ጨዋታ በልምምድ ወቅት ባጋጠመው ጉዳት ምክንያት ከስብስቡ ውጪ የሆነው ዳዊት ተፈራ ለአንድ ወር ከሜዳ እንደሚርቅ አውቀናል። ከቁጭምጭሚቱ በላይ ጉዳቱ የደረሰበት ሲሆን በወቅቱ ቀለል ያለ እንደሆነ እና ብዙም የከፋ እንዳልነበረ ከአዳማ ጨዋታ በኋላ ወደ ሜዳ እንደሚመለስ በክለቡ በኩል ተስፋ ተጥሎ ነበር።

ሆኖም ዛሬ የኤም አራ አይ ምርመራ በማድረግ ወደ አዲስ አበባ ውጤቱን በመላክ ቢታይም ስብራት እንዳጋጠመው እና ጀሶ እንደሚገባለት የህክምና ባለሙያዎች ምክረ ሀሳብ አቅርበዋል። ይህን ተከትሎ ዳዊት ተፈራ ከህመሙ ለማገገም ጀሶ የሚገባለት ከሆነ በቀጣይ ከፋሲል ከነማ የአምስተኛ ሳምንት ጨዋታ ጨምሮ በድሬዳዋ የሚኖሩ የሁለት ሳምንት ጨዋታዎች እንደሚያመልጡት ይጠበቃል።