መረጃዎች | 15ኛ የጨዋታ ቀን

የአራተኛ የጨዋታ ሳምንት ሦስተኛ ቀን ሁለት ጨዋታዎች ነገ ይደረጋሉ። በተከታዩ ፅሁፋችንም በሁለቱ ጨዋታዎች ላይ ያተኮሩ መረጃዎችን አሰናድተናል።

ኢትዮጵያ ቡና ከ ሲዳማ ቡና

የሊጉ የመጀመሪያ ድላቸውን ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ያሳኩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በአዲሱ የውድድር ዘመን ከውጤት ማጣት ጋር በተያያዘ ዋና አሰልጣኝ የቀየሩትን ሲዳማ ቡናዎችን የሚያስተናግዱበት የምሳ ሰዓቱ ጨዋታ ውጤት በተለያየ መንገድ ለሁለቱ ቡድኖች ከሚኖረው ትርጉም አንፃር የሚጠበቅ ነው።

በሊጉ በሦስት የጨዋታ ሳምንት በአማካይ 63% የኳስ ቁጥጥር ድርሻ በመያዝ በሊጉ ከሚወዳደሩ ክለቦች በርቀት ልቀው የተቀመጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች በኳስ ቁጥጥራቸው ተጋጣሚ ላይ እምብዛም አደጋ ሲደቅኑ አናስተውልም። እስካሁን በሊጉ 12 ብቻ ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎችን ያደረገው ቡድን እስከ አሁን ያስቆጠረው የግብ መጠን ሁለት መሆኑ ላስተዋለ እንደ አዲስ እየተሰራ የሚገኘው ቡድኑ የሚፈለገው ደረጃ ላይ ለመድረስ ብዙ እንደሚቀረው የሚያሳይ ነው።

በዚህ ረገድ ግን ቡድኑ በወልቂጤው ጨዋታ ከማሸነፉ ባለፈ ከሰሞኑ ጨዋታዎች በተሻለ በአማካይ እና አጥቂ ተጫዋቾች መካከል የተሻለ የህብረት እንቅስቃሴ ፍንጮችን የተመለከትን ሲሆን ቡድኑ እነዚህን የተጫዋቾች የሜዳ ላይ ግንኙነቶችን ይበልጥ እያጎለበተ መምጣት ይኖርበታል።

አሰልጣኝ ተመስገን ዳና በነገው ጨዋታ መጠነኛ ጉዳት ያስተናገደው አማኑኤል ዮሐንስን ግልጋሎት የማግኘታቸው ነገር አጠራጣሪ ሲሆን ሁለገቡ ገዛኸኝ ደሳላለኝ ግን ከጉዳቱ አገግሞ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ነው።

ከአሰልጣኝ ወንድማገኝ ተሾመ ጋር የተለያዩት ሲዳማ ቡናዎች ከፋሲል ከነማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የሊጉን ክብር የተቀዳጁትን ባለልምዱን አሰልጣኝ ስዩም ከበደን በቦታቸው የተኩ ሲሆን አሰልጣኙም በሊጉ ግርጌ የሚገኘውን ቡድን ዕጣ ፈንታ የመቀየር ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።

ትላንት ምሽት ወደ ባህር ዳር በማምራት አዲሱን ስብስባቸውን የተቀላቀሉት አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ዛሬ የመጀመሪያ ልምምዳቸውን ያሰሩ ሲሆን የነገውንም ጨዋታ ቡድናቸውን ለመገምገም ይጠቀሙበታል ተብሎ ይጠበቃል። ከአሰልጣኝ ሹም ሽር ባለፈ ክለቡ የገጠሙትን የውስጥ ችግሮችን በመገምገም አቶ አቡሽ አሰፋንም እንዲሁ አዲሱ የክለቡ ቡድን መሪ አድርገው መሾማቸው እንዲሁ ተሰምቷል።

በሊጉ ከኢትዮጵያ መድን ጋር በጣምራ 11 ግቦችን በማስተናገድ ደካማው የመከላከል መስመር ባለቤት የሆነው ቡድኑ ከአምናው የቀጠለ በሚመስል መልኩ በመከላከል ረገድ አሁንም ሚዛኑ የተፋለሰ ቡድን እንደሆነ እየተመለከትን እንገኛለን። ከኳስ ውጭ ፍፁም ያልተረጋጋ የሚመስለው ቡድኑ የሚፈፅማቸውን በርከት ያሉ ግለሰባዊ ሆነ መዋቅራዊ ስህተቶቹን ማረም የአሰልጣኝ ስዩም ተቀዳሚ የቤት ስራ እንደሚሆን ይጠበቃል። በሲዳማ ቡናዎች በኩል በነገውም ጨዋታ አንጋፋውን አጥቂ ሳላሀዲን ሰይድን በጉዳት ምክንያት የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ሆኗል።

ሁለቱ ቡናዎች ከዚህ ቀደም በሃያ አራት አጋጣሚዎች ተገናኝተው ሲዳማ ቡናዎች ስምንቱን ጨዋታ ሲያሸንፉ ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ ሰባቱን ያሸነፉ ሲሆን የተቀሩት አስር ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ በመጋራት የተጠናቀቁ ናቸው።

ይህን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ኤፍሬም ደበሌ የመምራቱን ኃላፊነት ሲረከብ ፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ፋሲካ የኋላሸት እና አዲስ አዳጊው ዳኛ ኤፍሬም ሀይለማርያም ረዳቶች ፣ ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ ደግሞ አራተኛ ዳኛ በመሆን ተመድበዋል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ለገጣፎ ለገዳዲ

በሊጉ ፍፁም ተቃራኒ የሆነ ታሪክ ያላቸውን እና በዘንድሮው የውድድር ዘመን ለሊጉ እንግዳ የሆኑትን ሁለቱን ቡድኖች የሚያገናኘው የ10 ሰዓቱ ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር ሊያስመለክተን እንደሚችል ይገመታል።

በሊጉ 15ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች እስካሁን ባደረጓቸው ሦስት ጨዋታዎች አንድ ነጥብን ብቻ ያሳኩ ሲሆን ከፈታኝ ሦስት መርሃግብሮች በኃላ በንፅፅር ተቀራራቢ የጥራት ደረጃ ላይ ከሚገኘው ለገጣፎ ለገዳዲ ጋር ከሚያደርጉት ጨዋታ ሙሉ ሦስት ነጥብ ለማሳካት ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃሉ። እንደ ቡድን በክፍት ጨዋታዎች እድል በመፍጠር ረገድ ደካማ የሆነው ቡድኑ እስካሁን በሊጉ አራት ብቻ ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎችን በማድረግ 16ኛ ደረጃ ላይ ሲገኙ በመከላከሉም እንዲሁ ቡድኑ ስህተቶች የማይለዩት ሆኗል በርካታ ለግብ ሆነ ለአደገኛ ሙከራዎች መነሻ የሆኑ ስህተቶችን እየፈፀሙ የሚገኙት ኤሌክትሪኮች በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ ተሻሽለው መቅረብ ይኖርባቸዋል።

ለመጀመሪያ ጊዜ በሊጉ እየተሳተፉ የሚጉኙት እና በተለየ የቡድን ግንባታ መንገድን በመከተል መልካም አጀማመር እያደረጉ የሚገኙት ለገጣፎ ለገዳዲዎች በሦስተኛ የጨዋታ ሳምንት በኢትዮጵያ መድን የመጀመሪያ የሊግ ሽንፈታቸውን ቢያስተናግዱም አሁንም በአራት ነጥቦች የሊጉ ወገብ አካባቢ ይገኛሉ። ካርሎስ ዳምጠው ላይ ጥገኛ የሚመስለው ቡድኑ በተወሰነ መልኩ ተለዋዋጭ መሆን ይጠበቅበታል። ተጋጣሚ ቡድኖች የለገጣፎን ረጃጅም ኳሶች መቆጣጠር የሚችሉ ከሆነ ቡድኑ በተወሰነ መልኩ አማራጭ ሀሳቦች እንደሌሉት በተለይ በመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች ያስተዋልን ሲሆን ከዚህ ባለፈ ግን ቡድኑ እንደ አዲስ አዳጊነቱ ጥሩ የሚባል ጉዞ ላይ ይገኛል።

በኢትዮ ኤሌክትሪኮች በኩል በወላይታ ድቻው ጨዋታ ጉዳት አስተናግዶ የነበረው ጌቱ ኃይለማሪያም ያገገመ ሲሆን በቀሪ ስብስቡ ውስጥም ሌላ የጉዳት ዜና አለመኖሩ ሲታወቅ በለገጣፎ ለገዳዲዎች በኩል ደግሞ የመሀል ተከላካዩ ዮናስ በርታ ብቸኛው በነገው ጨዋታ በጉዳት የማይኖረው ተጫዋች ነው።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያገናኘውን የነገው 10 ሰዓት ጨዋታ እንዲሁ በውድድር ዘመኑ ለመጀመሪያ ጊዜ በመሀል ዳኝነት እንዲመሩ የተመረጡት ቢኒያም ወርቅአገኘሁ የሚመሩት ጨዋታ ሲሆን ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው እና ለዓለም ዋሲሁን በረዳትነት ኢንተርናሽናል ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ ደግሞ አራተኛ ዳኛ ሆነው ይመሩታል፡፡