ፈረሰኞቹ ቅጣት ተላልፎባቸዋል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን በበላይነት የሚመራው አካል በ5ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ላይ ታይተዋል ባላቸው የዲሲፕሊን ግድፈቶች ላይ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የባህር ዳር ቆይታውን አገባዶ የፊታችን ዓርብ በድሬዳዋ ከተማ የ6ኛ ሳምንት ጨዋታዎችን ማድረግ እንደሚጀምር ይታወቃል። ከዚያ በፊት በ5ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች ታይተዋል ያላቸውን የዲሲፕሊን ግድፈቶች ሲመረምር የቆየው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር አመራር እና ሥነ-ስርዓት ኮሚቴ የተለያዩ ውሳኔውችን ማስተላለፉ ታውቋል።

በዚህም በተጫዋቾች ደረጃ ከድር ኩሊባሊ(ፋሲል ከነማ) ከስፖርታዊ ጨዋነት ውጭ በመጫወቱ ከጨዋታ ሜዳ የተወገደ ስለመሆኑ ሪፖርት ስለቀረበበት 1 ጨዋታ እንዲታገድና በተጨማሪ የ1500 ብር ገንዘብ ቅጣት እንዲከፍል ሲወሰን በክለቦች ደረጃ መቻል ፣. ድሬደዋ ከተማ፣ ሲዳማ ቡና፣ ፋሲል ከነማ ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወላይታ ድቻ የየክለባቸው አምስት እና ከዛ በላይ ተጫዋቾች በተለያዩ ጥፋቶች ካርድ የተሰጣቸው በመሆኑ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት እያንዳንዳቸው የገንዘብ ቅጣት ብር 5000 /አምስት ሺ/ እንዲከፍል መወሰኑ ተገልጿል።

በተጨማሪም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከፋሲል ከነማ ጋር ባደረገው ጨዋታ የፈረሰኞቹ የክለቡ ደጋፊዎች የዕለቱን ዳኛ አፀያፊ ስድብ ስለመሳደባቸው ሪፖርት ቀርቧል በማለት ደጋፊዎቹ በፈጸሙት ጥፋት ክለቡ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 50000 ብር እንዲከፍል ተወስኗል፡፡