ሪፖርት | ድሬዳዋ ከተማ ወሳኝ ድል ተቀዳጅቷል

ምሽት ላይ በተደረገው የስድስተኛ ሳምንት ሁለተኛ ጨዋታ ብርቱካናማዎቹ ቡናማዎቹን 3-1 በመርታት የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ሦስት ነጥብ ማሳካት ችለዋል።

ምሽት 1፡00 ላይ የስድስተኛ ሳምንት ሁለተኛ ጨዋታ በድሬዳዋ ከተማ እና በኢትዮጵያ ቡና መካከል ሲደረግ ብርቱካናማዎቹ በአምስተኛው ሳምንት ከሀዋሳ ከተማ ጋር አቻ ሲለያዩ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ አማረ በቀለ እና ዮሴፍ ዮሐንስን በጋዲሳ መብራቴ እና ኢያሱ ለገሠ ተክተው ጀምረዋል። ቡናማዎቹ በበኩላቸው በአምስተኛው ሳምንት አርባምንጭ ከተማን 2-0 ከረቱበት አሰላለፍ ጫላ ተሽታን በመስፍን ታፈሰ ቦታ ተክተው ጀምረዋል።

ሁለት የተለያዩ የጨዋታ ሂደቶች በታዩበት የመጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያ 25 ደቂቃዎች ድሬዳዋ ከተማዎች በጋለ የጨዋታ ስሜት የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች እግር ስር ኳስ እንዳይቆይ እና መስርተው ለመውጣት እንዲቸገሩ በማድረግ ተጭነው በመጫወት ጥሩ እንቅስቃሴ ማሳየት ችለው የነበረ ሲሆን 8ኛው ደቂቃ ላይም ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ኤልያስ አህመድ በቀኝ መስመር ወደ ሳጥኑ ይዞ ገብቶ የሞከረው ኳስ ወደፊት ወጥቶ በነበረው ግብ ጠባቂው በረከት አማረ ሲጨናገፍ ለማስቆጠር ምቹ ቦታ ላይ የነበረው ቢንያም ጌታቸው ያደረገውን የግብ ማግባት ሙከራ ጋናዊው የመሀል ተከላካይ ኩዋኩ ዱሃ በድንቅ ሁኔታ በግንባሩ ገጭቶ ማስወጣት ችሏል።

ብርቱካናማዎቹ በያሬድ ታደሰ በቢንያም ጌታቸው እና በሙሴጌ ቻርልስ የተለያዩ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ቢችሉም ውጤታማ አልነበሩም። በጨዋታው እየተረጋጉ የመጡት ቡናማዎቹ በመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻዎቹ 20 ደቂቃዎች በኳስ ቁጥጥሩ በኩል ፍፁም የበላይነቱን መውሰድ ሲችሉ በመሐመድኑር ናስር ፣ ጫላ ተሽታ ፣ አስራት ቱንጆ እና ብሩክ በየነ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ቢሞክሩም ውጤታማ አልነበሩም። በተለይም የመጀመሪያ አጋማሽ ሊጠናቀቅ የባከኑ ደቂቃዎች ሲቀሩ መሐመድኑር ናስር ሳጥን ውስጥ ከጫላ ተሽታ በተቀበለው ኳስ የፈጠረው እና ግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመ ወጥቶ በእግሩ ያጨናገፈው ኳስ በቡናማዎቹ በኩል አስቆጪ አጋጣሚ ነበር።

ከዕረፍት መልስ ከኳስ ውጪ ድንቅ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩት ብርቱካናማዎቹ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው በመጫወት በሚያገኙት ኳስ ቶሎ ወደተጋጣሚ ክልል በመግባት በሚፈጥሯቸው የግብ ዕድሎች እና ከቆሙ ኳሶች በሚያገኟቸው የግብ ማግባት አጋጣሚዎች ለመጠቀም ያሰቡት አጨዋወት ውጤታማ አድርጓቸዋል።

49ኛ ደቂቃ ላይ አሰጋኸኝ ጴጥሮስ በቀኝ መስመር ከረጅም ርቀት ከተገኘ የቅጣት ምት በግሩም ሁኔታ ያሻማውን ኳስ አሳንቴ ጎድፍሬድ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሮ ብርቱካናማዎቹን መሪ ማድረግ ችሏል። ይሄም የጨዋታውን መንፈስ የቀየረ ትልቁ አጋጣሚ ነበር።

በተደጋጋሚ ኳሱን የተቆጣጠሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ሰብረው መግባት እንዳይችሉ ማድረግ የቻሉት ብርቱካናማዎቹ59ኛው ደቂቃ ላይ ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም አሰጋኸኝ ጴጥሮስ በድንቅ ሁኔታ ከረጅም ርቀት አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ አቅጣጫውን በድንቅ ሁኔታ የተረዳው ቢንያም ጌታቸው ማስቆጠር ችሏል።

በአምስት ደቂቃዎች ልዩነት ዮሴፍ ዮሐንስ ከረጅም ርቀት ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ቢንያም ጌታቸው ላይ ከወትሮው በተለየ በጨዋታው ደካማ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው ኩዋኩ ዱሃ ጥፋት በመስራቱ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ዮሴፍ ዮሐንስ አስቆጥሮ የክለቡን መሪነት ወደ 3-0 ከፍ ማድረግ ችሏል።

ቡናማዎቹ ከዕረፍት መልስ የተሻለውን የግብ ሙከራ ያደረጉት 72ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን አብዱልከሪም ወርቁ ያቀበለውን ኳስ ተቀይሮ የገባው አንተነህ ተፈራ የግብ ጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ ከፍ አድርጎ ቢሞክርም ኳሱ ዒላማውን መጠበቅ አልቻለም።

ከዚህ ሙከራ በኋላ ጨዋታው እየተቀዛቀዘ ሲሄድ የጨዋታው የመጨረሻ የባከኑ ደቂቃዎች ላይ ቡናማዎቹ ለባዶ ከመሸነፍ ያዳነች ግብ ማስቆጠር ሲችሉ አንተነህ ተፈራ ከኃይለሚካኤል አደፍርስ በተቀበለው ኳስ አሳንቴ ጎድፍሬድን በአንድ ንክኪ አታልሎ በማለፍ ድንቅ ግብ ማስቆጠር ችሏል። ይሄን የጨዋታው የመጨረሻ ትዕይንት ሆኖ ጨዋታው በድሬዳዋ ከተማ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ተመስገን ዳና በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ እንዳልነበሩ እና የተከላካይ መስመራቸው መዋቅር መበላሸቱ ለሽንፈት እንደዳረጋቸው ጠቅሰው በፍጥነት ወደ ማሸነፍ እንመለሳለን ብለው እንደሚያስቡ ሲናገሩ በጨዋታው ድል የቀናው የድሬዳዋ ከተማው አሠልጣኝ ዮርዳኖስ ዓባይ በበኩላቸው የሚፈልጉትን የጨዋታ መንገድ እንዳዩ እና ደጋፊውም በሰጣቸው ድጋፍ ደስተኛ መሆናቸውን ሲገልጹ በቀጣይ ጨዋታዎችም ይህንን አጨዋወት በማስቀጠል ለሕዝቡ ጥሩ ጨዋታ በማሳየት ነጥቦችን እያገኙ መሄድ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።