መረጃዎች | 29ኛ የጨዋታ ቀን

8ኛ የጨዋታ ሳምንት ነገም ቀጥሎ ሲውል በዕለቱ የሚደረጉትን ሁለት ተጠባቂ መርሃግብሮች የተመለከቱ መረጃዎች በተከታዩ ፅሁፍ ቀርበዋል።

አዳማ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ

የዕለቱ የመክፈቻ መርሃግብር ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያልሙትን አዳማ ከተማዎችን የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ተከታታይ ድል ለማሳካት ከሚገቡት ወላይታ ድቻዎች ጋር ያገናኛል።

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የነበራቸው ጨዋታ ማድረግ ያልቻሉት አዳማ ከተማዎች ምንም እንኳን ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ በሰባት ነጥቦች 9ኛ ደረጃ ላይ ቢገኙም በእንቅስቃሴ ረገድ ግን እምብዛም የሚያስከፋ ቡድን አልነበረም። በ3ኛው የጨዋታ ሳምንት ሀዋሳ ከተማን ከረቱ ወዲህ በመጨረሻ ሦስት የሊግ ጨዋታዎች ሁለት ሽንፈት እና አንድ አቻ ያስመዘገቡት አዳማዎች ወደ አሸናፊነት መመለስን በጥብቅ ይሻሉ። አምና የቡድኑ አንደኛው ድክመት የነበረው በጨዋታዎች ጥሩ ቢንቀሳቀሱም በቂ ነጥብ መያዝ ያለመቻላቸው ጉዳይ እንደመሆኑ ቡድኑ እንቅስቃሴውን የሚገልፅ ውጤቶችን ከጨዋታዎች መያዝ ይኖርበታል። ወሳኝ ተጫዋቾች የሆኑትን አጥቂውን ዳዋ ሆቴሳ እና ተከላካዩ ሚሊዮን ሰለሞንን በጉዳት ምክንያት በመጨረሻው ጨዋታ መጠቀም ያልቻለው ቡድኑ በጨዋታው ሁለቱን ተጫዋቾች በማጥቃቱ ሆነ በመከላከሉ ስለማጣቱ ምስክር የሆኑ ዘጠና ደቂቃዎችን አሳልፏል።

በዚህኛው ጨዋታ አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ሚሊዮን ሰለሞን እና አብዲሳ ጀማልን በጉዳት እንዲሁም ግብ ጠባቂውን ሰዒድ ሀብታሙን በግል ጉዳይ የማያገኙ ሲሆን አምበላቸው ዳዋ ሆቴሳ ግን ከነበረበት ጉዳት አገግሞ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ሆኗል።

በ6ኛው የጨዋታ ሳምንት መቻልን 1-0 እስኪረቱ ድረስ በሊጉ ግርጌ የነበሩት ወላይታ ድቻዎች የመጀመሪያ ድላቸውን ማሳካታቸውን ተከትሎ በአምስት ነጥቦች ወደ 13ኛ ደረጃ ፈቀቅ ማለት ችለዋል። በሰባተኛ የጨዋታ ሳምንት ለገጣፎ ለገዳዲ ጋር የነበራቸው ጨዋታ መሰረዙን ተከትሎ በነገው ጨዋታ ከ13 ቀናት እረፍት በኋላ ወደ እንቅስቃሴ የሚመለሰው ቡድን ይህን የማሸነፍ ስሜት ለማስቀጠል እንዳይቸገር ስጋትን ያጭራል።

ከሰሞነኛው የጫና ስሜት በተወሰነ መልኩ አሁን ላይ ተንፈስ ያሉት ድቻዎች ላይ አሁንም በርከት ያሉ ቀሪ የቤት ሥራዎች መኖራቸው ግን ዕሙን ነው። በውድድር ዘመኑ ሁለት ግቦችን ቃልኪዳን ዘላለም ካስቆጠራቸው ፍፁም ቅጣት ምቶች ብቻ ያገኘው እና የሊጉ ደካማው ማጥቃት ባለቤት የሆነው ድቻ ከመጀመሪያ ድላቸው ማግስት ማጥቃታቸውን በሚገባ ስለማሻሻል ትኩረት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም በነገው ጨዋታ በቅጣት ከሚያጡት ግብ ጠባቂያቸው ቢኒያም ገነቱ በተጨማሪ ከዚህ ቀደም ጉዳት ላይ የነበሩት እንድሪስ ሰዒድ ፣ ቢኒያም ፍቅሬ እንዲሁም መጠነኛ መሻሻል ያሳዩትን ፂዮን መርዕድ እና ስንታየሁ መንግሥቱን አገልግሎት አያገኙም።

10 ሰዓት ሲል ጅማሮውን የሚያገኘውን የአዳማ ከተማ እና ወላይታ ድቻን ጨዋታ ሀብታሙ መንግሥቴ በመሀል ዳኝነት ይመሩታል።

ሁለቱ ቡድኖች ከነገው ጨዋታ አስቀድሞ 14 ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን በሁለት ጨዋታ ብቻ ነጥብ ሲጋሩ ወላይታ ድቻ ሰባት ጊዜ አዳማ ከተማ ደግሞ አምስት ጊዜ ድል ቀንቷቸዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ መቻል

ሙሉ ሦስት ነጥብ ካሳኩ ሦስት ጨዋታዎችን ያስቆጠሩትን ቅዱስ ጊዮርጊስ እና መቻልን የሚያገናኘው የምሽቱ ጨዋታ ድል ለሁለቱ ቡድኖች ከሚኖረው ጠቀሜታ አንፃር ብርቱ የሜዳ ላይ ፉክክርን ያስመለክተናል ተብሎ ይጠበቃል።

በ4ኛ የጨዋታ ሳምንት አዳማ ከተማን 2-1 ከረቱ ወዲህ ቅዱስ ጊዮርጊስ ባደረጓቸው ተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ያስመዘገቧቸው ውጤቶች ሆነ በሜዳ ላይ ያሳዩት እንቅስቃሴ ደጋፊዎችን ደስተኛ የሚያደርግ አልነበረም። ከሦስቱ ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው ዘጠኝ ነጥቦች ሁለቱን ብቻ ያሳክኩት ጊዮርጊሶች ወደ 8ኛ የጨዋታ ሳምንት ሲያመሩ ከሊጉ ጅማሮ አንስቶ ላለፉት ሳምንታት ተቆጣጥረው የነበሩትን የሰንጠረዡን አናት አስረክበው በ14 ነጥቦች 2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

በብዙ መመዘኛዎች በሊጉ ጅማሮ ካስመለከቱን አስደናቂ ብቃት አንፃር እጅግ ደካማ ጊዜን እያሳለፉ የሚገኙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ያለወትሮው በቀላሉ ለግለሰባዊም ሆነ ለመዋቅራዊ ስህተቶች እየተጋለጠ የሚገኘውን የመከላከል መስመራቸውን ማስተካከል የሚገባቸው ሲሆን ከዚህ ባለፈም ቡድኑ ጨዋታዎችን ለመቆጣጠር እየተቸገረ መሆኑ ውጤት ለመያዝ እንዲቸገሩ እያስገደዳቸው ያለ ይመስላል። በመሆኑም ቡድኑ ወደ ቀደመ ብቃቱ ለመመለስ በተለይ በሁለቱ መመዘኛዎች የተሻለ ጊዜን ማሳለፍ ይጠበቅባቸዋል።

ከፍ ባለ ጫና ውስጥ የሚገኙት መቻሎች የመጨረሻ ድላቸውን ካስመዘገቡ ሦስት ጨዋታዎች ተቆጥረዋል። በመጨረሻ ባደረጓቸው ሦስት ጨዋታዎች ከተከታታይ ሁለት ሽንፈቶች ማግስት በ7ኛ የጨዋታ ሳምንት ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርተዋል። በጥቅሉ ካደረጓቸው የሰባት ጨዋታ ብዛት ዕኩል ሰባት ነጥቦችን ብቻ የሰበሰበው ቡድኑ አሁን ላይ በ11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

የጥራት ደረጃቸው በላቁ ግለሰቦች ነገር ግን እንደ ቡድን ፍፁም ለመዋሀድ የተቸገረው የአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ስብስብ አሁን ሜዳ ላይ በተጠበቀው ልክ ለመገኘት ተቸግሯል። በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ለያዘው ስብስብ የሚመጥን ነገር እያሳየ የማይገኘው ቡድኑ ሁለተኛ የማሸነፍ ግምትን ይዘው ከሚጀምሩበት የነገው መርሃግብር ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዘው መውጣት ከቻሉ የራስ መተማመን ደረጃው ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ለሚገኘው ስብስብ ብዙ ነገሮችን ሊቀይር ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።

ለነገው ጨዋታ በፈረሰኞቹ ቤት የተሰማ አዲስ የጉዳት ዜና ባይኖርም ጉዳት ላይ የነበሩት ዳዊት ተፈራ ፣ ሻሂዱ ሙስጠፋ እና ተመስገን ዮሐንስ አሁንም ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆኑ በመቻሎች በኩል ደግሞ ከአጥቂው ተሾመ በላቸው ውጭ የተቀረው ስብስብ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠናል።

የምሽቱን ተጠባቂ መርሃግብር ቢኒያም ወርቅአገኘሁ በመሀል ዳኝነት እንደሚመሩት ይጠበቃል።

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ረዘም ያለ ታሪክ ያላቸው ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም በሊጉ 31 ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን 17 ጨዋታዎች ነጥብ በመጋራት ሲጠናቀቁ በመሸናነፍ ከተጠናቀቁት 14 ጨዋታዎች ውስጥ ፈረሰኞቹ 12 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነት የያዙ ሲሆን መቻሎች ደግሞ በተቀሩት ሁለት ጨዋታዎች ባለድል መሆን ችለዋል።