ሪፖርት | ሰራተኞቹ ወደ ድል ተመልሰዋል

የስምንተኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ በወልቂጤ ከተማ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ለገጣፎ ለገዳዲ በሀድያ ሆሳዕና ከተረታበት ጨዋታ ወንደሰን ገረመው ፣ አቤል አየለ እና ያብቃል ፈረጃን በሚኪያስ ዶጆ፣ በረከት ተሰማ እና ጋብርኤል አሕመድ በተከታት ወደ ሜዳ ሲገባ በአንፃሩ ወልቂጤ ከተማዎች ከፈረሰኞቹ ጋር አቻ ከወጡበት ስብስባቸው ጀማል ጣሰው እና ፋሲል አበባየሁን በፋሪስ ዓለሙ እና ተመስገን በጅሮወንድ በመያዝ ለፍልሚያው ገብተዋል።

ገና ከጨዋታውን ጅማሬ አንስተው በሁሉም የሜዳ ክፍል በተገቢው መንገድ ብልጫ ወስደው መጫወት የጀመሩት ወልቂጤዎች በአስረኛው ደቂቃ ነበር የመጀመርያ ጎላቸውን ያገኙት። የለገጣፎው ተከላካይ መዝገቡ ቶላ ጌታነህ ከበደን በእጅ ጎትቶ በማስቀረቱ ተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ጌታነህ ወደ ጎልነት በመቀየር ቡድኑን ቀዳሚ ጎል አስገኝቷል።

ብልጫ ወስደው ማጥዋታቸውን የቀጠሉት ወልቂጤዎች በመልሶ ማጥቃት ሁለተኛ ጎላቸውን በ21ኛው ደቂቃ አግኝተዋል። በፍጥነት ከራሳቸው የሜዳ ክፍል በረጅሙ ኳስ ያስጀመርቱን ጌታነህ ከበደ በጥሩ መንገድ ለኋላሸት ሰለሞን አቀብሎት መሬት ለመሬት በግራ ግሩ አክርሮ በመምታት የቡድኑን ሁለተኛ ጎል አሰገኝቷል።

ለገጣፎዎች ኳሱን ተቆጣጥረው መጫወት ቢችሉም ሦስተኛ የሜዳው ክፍል ሲደርሱ በቀላሉ በወልቂጤ ተከላካዮች እየተነጠቁ የሚመለሰው ኳስ በራሳቸው ላይ አደጋ ሲፈጥርባቸው ተስተውሏል። በዚህም ሂደት በ31ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት አንድ የለገጣፎ ተከላካይን ሦስት የወልቂጤ አጥቂዎች አግኝተው በስተመጨረሻም ጌታነህ ከበደ እግር ስር ደርሶ አስቆጠረው ሲባል ግብ ጠባቂው ሚኪያሰ ያዳነበት ሦስተኛ ጎል መሆን የሚችል ነበር። ወልቂጤዎች በየኋላሸት ሰለሞን አማካኝነት ሌላ ጎል የቀረበ ሙከራ ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። የመጀመርያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ድረስ በለገጣፎዎች በኩል ግልፅ የማግባት አጋጣሚ ሳይፈጠር ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ተነቃቅተው የተመለሱት ለገጣፎዎች ወደ ጨዋታው መግባት የሚያስችላቸውን እንቅስቃሴ ከጎል ሙከራ ጋር ማድረግ ችለው ነበር። በ52ኛው ደቂቃም ኪሩቤል ወንድሙ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን በተከላካዮች ተደርቦ ሲመለስ አግኝቶ ወደ ጎል ቢመታውም ግብ ጠባቂው ፋሪስ የመለሰበት እንዲሁም ብዙም ሳይቆይ ካርሎስ ዳምጠው ከግብ ጠባቂው አናት ላይ አሻግሮት ጎል ተቆጠረ ሲባል የወልቂጤ ተከላካዮች ተረባርበው ያዳኑት ለለገጣፎዎች ግልፅ የጎል ዕድሎች ነበሩ።

ብልጫ የተወሰደባቸው ወልቂጤዎች ጨዋታውን ለመቆጣጠር የሚያስችላቸውን እንቅስቃሴ በማድረግ ቀጥለው በ59ኛው ደቂቃ በየኋላሸት ሰለሞን አማካኝነት ያደረጉት ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል። የጨዋታው እንቅስቃሴ መሐል ሜዳ ላይ ተገድቦ ኳሶች እየተቆራረጡ መጓዝ ቢችልም ተቀዛቅዞ የነበረውን ጨዋታ የወልቂጤዎች ሦስተኛ ጎል ነፍስ ዘርቶበታል። በአቡበከር ሳኒ ከቀኝ መስመር ከተከላካይ ጀርባ የጣለለትን አይምሬው አጥቂ ጌታነህ ከበደ በግሩም ሁኔታ በግንባሩ በመግጨት ለቡድኑ ሦስተኛ ለራሱ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል።

በቀሩት ደቂቃዎች እምብዛም የተለየ ነገር ሳያስመለክተን ጨዋታው በወልቂጤዎች 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።