የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ሀዋሳ እና ኤሌክትሪክ ሊጉን በድል ጀምረዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ2015 የውድድር ዘመን የመጀመሪያው ዙር ዛሬ በሀዋሳ ከተማ በሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ በተደረጉ ሦስት ጨዋታዎች ተጀምሯል፡፡

ረፋድ 3፡00 ሰዓት ሲል የመክፈቻ ጨዋታ የሊጉን ጠንካራ ክለቦች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ሀዋሳ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ ቀዳሚው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ አዲሱ ቃሚሶ እና ወ/ሮ ብዙአየው ጀምበሩ ፣ አቶ ፍሬው አሬራ የሲዳማ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር እና አቶ አንበሴ አበበ የሲዳማ ክልል እግር ኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝዳንት እንዲሁም ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተው ጨዋታውን በይፋ አስጀምረዋል፡፡ ብርቱ የሜዳ ላይ የመሸናነፍ ፉክክር በታየበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫን ያሳየ ቢሆንም በመከላከል አደረጃጀት ረጅሙን ደቂቃ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ሽግግር የተጫወቱት ሀዋሳዎች ያገኙትን አጋጣሚ በቀላሉ ወደ ጎል በመለወጡ እጅጉን ተሽለው ታይተዋል፡፡

በመጀመሪያው አጋማሽ 39ኛው ደቂቃ ላይ መነሻዋን ከመስመር ባደረገች ኳስ ረድዔት እና ቱሪስት በጥሩ ቅብብል ያደረሷትን ወጣቷ አጥቂ እሙሽ ዳንኤል የንግድ ባንክን ተከላካዮችን ስህተት በአግባቡ በመጠቀም ሀዋሳን መሪ አድርጋለች፡፡ በበርካታ ተመልካቾች ታጅቦ የተደረገው ይህ ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአጥቂ ቁጥሩን በማሳደግ ወደ ጨዋታ ለመመለስ ቢጥርም አስደናቂ የኋላ መስመርን ያደራጁት ሀዋሳዎች በጥብቅ መከላከል ጨዋታውን 1-0 በመርታት ውድድሩን በድል ጀምረዋል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የሀዋሳ ጎል አስቆጣሪ እሙሽ ዳንኤል ትዕንግርት የሴቶች ስፖርት ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ጋር በመሆን የሚሸልመውን የጨዋታ ምርጥ ሽልማት ተቀብላለች፡፡

የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ቀን 8 ሰዓት በአዲስ አበባ ከተማ እና አዳማ ከተማ መካከል ይደረግ የነበረ ቢሆንም አዲስ አበባ ከተማን የፎርፌ አሸናፊ ያደረገ ውጤት የተመዘገበበት ነበር፡፡ የአዳማ ከተማ ቡድን ጨዋታውን ለማድረግ ሜዳ ላይ መገኘት ቢችልም ከተጫዋቾች የደመወዝ ክፍያ ጋር በተገናኘ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን የዕግድ ውሳኔ ስለተላለፈበት እና የተጣለበትን ዕገዳም መፈፀም ስላልቻለ የዕለቱ ዳኞች በህጉ መሠረት 30 ደቂቃዎች ከጠበቁ በኋላ ለአዲስ አበባ ከተማ ሦስት ነጥብ ፣ ከሦስት ጎሎች ጋር ሰጥተዋል፡፡

ኢትዮ ኤሌክትሪክን ከቦሌ ክፍለከተማ ያገናኘው ሦስተኛው የቀኑ ጨዋታ የአሰልጣኝ መሠረት ማኔውን ኤሌክትሪክ በግብ አንበሽብሾ መጠናቀቅ ችሏል፡፡ በተደራጀ የመሀል ሜዳ ክፍል ለአጥቂዎች በሚጣሉ ኳሶች በማጥቃት መጫወት የጀመሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ገና በጊዜ ነበር ጎል ያገኙት። 5ኛው ደቂቃ ላይ ትንቢት ሳሙኤል ለሽታዬ ሰጥታት ተጫዋቿ ወደ ጎል አክርራ ስትመታው በቦሌ ተከላካይ ብዙነሽ እሸቱ ተጨርፎ ወደ ጎልነት ተለውጧል፡፡ በጥሩ የማጥቃት ኃይል በተጋጣሚያቸው ላይ የበላይነትን ያስቀጠሉት ኤሌክትሪኮች 31ኛው ደቂቃ ላይ በትንቢት ሳሙኤል ጎል ወደ ሁለት ከፍ ማለት ችለዋል፡፡ መደበኛው የቀዳሚው አርባ አምስት የጨዋታ ክፍለጊዜ ሊገባደድ ጭማሪ ደቂቃ ላይ አንጋፋዋ አጥቂ ሽታዬ ሲሳይ ከሁለት ዓመት በኋላ ጎል በማስቆጠር ቡድኑን ወደ 3-0 አሸጋግራለች፡፡

ከዕረፍት ጨዋታው ተመልሶ ሲቀጥል በተመሳሳይ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ተጨማሪ አጥቂዎችን ወደ ሜዳ በማስገባት የማጥቃት ሚዛኑን ወደ ራሳቸው በመውሰድ ሲያስቀጥሉ ቦሌዎች በበኩላቸው የተገደበ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን በማዘውተራቸው ልዩነቱን ለማጥበብ ከብዷቸው ተስተውሏል፡፡ 53ኛው ደቂቃ ላይ የዓይናለም አሳምነው ድንቅ የማቀበል አቅም የታየበትን ኳስ የቀድሞው የንግድ ባንክ አማካይ ትዕግስት ያደታ አራተኛ ጎል አድርጋዋለች፡፡ 

55ኛው ደቂቃ ላይ ሰብለወንጌል ወዳጄ ከቦሌ አማካዮች የተቋረጠ ኳስን አግኝታ ለትንቢት ሰጥታት አጥቂዋ አምስተኛውን ጎል ለቡድኗ ለራሷ ሁለተኛ ጎል አክላለች፡፡ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ዓይናለም አሳምነው ድንቅ ጎል በማከል ጨዋታው 6-0 በኤሌክትሪክ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የኤሌክትሪኳ ትንቢት ሳሙኤል ትዕንግርት የሴቶች ስፖርት ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ጋር በመሆን የሚሸልመውን የጨዋታ ምርጥ ሽልማት ተቀብላለች፡፡

ጨዋታው ነገም ሲቀጥል ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለከተማ ከ ይርጋጨፌ ቡና 4፡00 ፣ ልደታ ክፍለ ከተማ ከ መቻል 8፡00 ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ድሬዳዋ ከተማ በ10፡00 ይጫወታሉ።