መረጃዎች | ፋሲል ከነማ ከ ድሬዳዋ ከተማ

የወላይታ ድቻ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ ወደ አዳማ መዘዋወሩን ተከትሎ ነገ በሊጉ የሚደረገውን ብቸኛ ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎችን እንደሚከተለው አሰናድተናል።

11ኛው የጨዋታ ሳምንት ድሬዳዋ ላይ በሚኖረው ቆይታ ነገ ምሽት ፋሲል ከነማን ከድሬዳዋ ከተማ በሚያገናኘው ጨዋታ ይቋጫል። ለሦስት ጨዋታዎች ድል ርቆት የነበረው ፋሲል ከነማ ተከታታይ ጨዋታዎችን ማሸነፍ ቢችልም ወደ ሰንጠረዡ አናት ፉክክር ሊያስፈነጥረው ይችል የነበረውን የወላይታ ድቻ ተስተካካይ ጨዋታ በሽንፈት አልፎ ለነገው ጨዋታ ይደርሳል። በመቀመጫ ከተማው ምንም ሽንፈት ያላገኘው ድሬዳዋ ከተማም እንደ ፋሲል ሁሉ ከሁለት ድሎች በኋላ የመጨረሻ ጨዋታውን አድርጎ የነበረ ሲሆን ከወልቂጤ ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርቷል።

ነገሮች እንዳሰቡት ያልጀመሩለት ፋሲል በሰንጠረዡ አጋማሽ ሆኖ ነው ድሬዳዋን የሚገጥመው። ሙሉ ውጤት ማሳካት እስከ 5ኛ ደረጃ የሚገፋው በመሆኑም ጨዋታው ቀላል ግምት የሚሰጠው አይሆንም። ፋሲል ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ግብ ማስቆጠር ሳይችል በወጣበት የወላይታ ድቻው ጨዋታ ተጋጣሚውን ለማስከፈት ያደረጋቸው ጥረቶች ከረጅም ርቀት ሙከራዎች ውጪ የተለየ ዕድል አልፈጠሩለትም። ይልቁንም ለመልሶ ማጥቃት ክፍት ሆኖ መታየቱ ነገም በድሬዳዋ ፈጣን ጥቃቶች እንዳይቀጣ የሚያሰጋው ይመስላል። ሆኖም በነገው ጨዋታ በሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ እንዳ ድቻው ዓይነት ፈተና ላይገጥመው መቻሉ የቡድኑ ልዩነት ፈጣሪ አማካዮች አንዳች ነገር ለማሳየት ዕድሉን ሊሰጣቸው ይችላል ተብሎ ይገመታል።

በመቀመጫ ከተማቸው ካደረጓቸው ጨዋታዎች 73% የሚሆነውን ነጥብ የሰበሰቡት ድሬዳዋ ከተማዎች ነገ ነጥባቸውን 18 አድርሰው ወደ ፉክክሩ ይበልጥ የመጠጋት ዕድሉ አላቸው። ቡድኑ በብዙው ተቀይሮ በታየባቸው ባለፉት ጨዋታዎች እንደ ድክመት የሚነሳበት የመከላከል አቅሙ ነው። በዚህም በአምስቱም ጨዋታዎች ላይ ግብ የማስተናገዱ ነገር እንደማስረጃ ይቀርብበታል። በመጨረሻው የወልቂጤ ከተማ ጨዋታም ግለሰባዊ ስህተቶች እና የመከላከል ድክመት ሁለት ጊዜ እንዲመራ አድርጎት የነበረ ቢሆንም ምስጋና ቡድኑ ለሚገኝበት ከፍተኛ የተነሳሽነት ደረጃ ይግባና በመጨረሻ ግብ አስቆጥሮ አንድ ነጥብ ማሳካት ችሏል። ይህ የቡድኑ ድክመት ነገም በፋሲል ጨዋታ ከተደገመ እና ግብ ካስተናገደ ግን ዐፄዎቹ ነጥቡን አጥብቀው ከመፈለጋቸው አንፃር ውጤታቸውን በቀላሉ አሳልፈው ላይሰጡ ይችላሉ።

የፋሲል ከነማዎቹ አስቻለው ታመነ እና በዛብህ መለዮ በጉዳት በነገው ጨዋታ የመሰለፋቸው ነገር አጠራጣሪ ሲሆን ሀብታሙ ተከስተ አሁንም ከቡድኑ ጋር አይገኝም። በድሬዳዋ በኩል ደግሞ ያሬድ ታደሰ በጉዳት እንየው ካሳሁን በቅጣት ጨዋታው ያልፋቸዋል።

ፋሲል እና ድሬዳዋ በሊጉ እስካሁን አስር ጊዜ ተገናኝተዋል። ፋሲል ከነማ አራት ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ ሦስት ድሎችን ሲያሳኩ በቀሪዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። በጨዋታዎቹ 21 ጎሎች የተቆጠሩ ሲሆን ፋሲል ከነማ 13 ፤ ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ 8 ጎሎች አስመዝግበዋል።

ጨዋታውን ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ በመሀል ዳኝነት ፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ፋሲካ የኋላሸት እና ፍሬዝጊ ተስፋዬ በረዳት ዳኝነት ፣ ብርሀኑ መኩሪያ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ይመሩታል።