የአሠልጣኞች አስተያየት | ወልቂጤ ከተማ 1-2 ኢትዮጵያ መድን

👉”ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ሦስት ነጥብ አላገኘንም ነበርና ዛሬ ሦስት ነጥብ ለማግኘት ነበር ጥረት ያደረግነው” ገብረመድህን ኃይሌ

👉”ተጫዋቾቻችን የቻሉትን ለማድረግ ሞክረዋል ፤ ነገር ግን ከነበረን ነገር አንጻር ትንሽ ወረድ ብሏል” ገብረክርስቶስ ቢራራ

አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ – ኢትዮጵያ መድን

ስለ ጨዋታው…

ትንሽ አስቸጋሪ ነው፡፡ ውጥረት የበዛበት ነበር። ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ሦስት ነጥብ አላገኘንም ነበርና ዛሬ ሦስት ነጥብ ለማግኘት ነበር ጥረት ያደረግነው። ከእዛ አንፃር የእነርሱ ትግል ከበድ ይል ነበር፡፡

ሁለተኛው አጋማሽ በተጋጣሚያቸው ስለተፈጠረባቸው ጫና…

አንድ ለባዶ እየመራን ስለ ወጣን በጥሩ ሰዓት ላይ ነው ጎል ያገባነውና እሱን ከመጠበቅ አንፃር ከነበረብን ውጥረት ካለ ማሸነፍ ከተነሳ የተፈጠረ ነገር ነው እንጂ ሌላ ነገር አይደለም፡፡ እንደውም ጥሩ ነው ከእዛ በኋላ ትንሽ ለመቆጣጠር ተሞክሯል ፔናሊቲ ተገኝቶ እንደገና ሌላ ጫና ነበር፡፡ ምክንያቱም ማግባት ሰለነበረብን ወደ ፊት መጫወት ነበረብን። የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾች ቀይረን ጉልበት ያላቸውን አስገብተን እሱም ተሳክቶልናል፡፡

በመጨረሻ ደቂቃ ቡድኑ ውጤት ይዞ ስለሚወጣበት መንገድ…

ይህንን አይቶ አንብቦ ቅያሬዎችን በትክክል ማሳካት ተገቢ ነው። ይሄም ጥሩ ነው ተካክቶልናል ፤ እንቀጥልበታለን፡፡

ወደ አሸናፊነት መመለስ…

ይህው ተመልሰናል ጥሩ ነው፡፡ አሁን እስካለው ሁኔታ ቡድናችን ጥሩ ነው፡፡ ይሔ ሞራል ስሜት ፍላጎት ይቀጥላል ብዬ አስባለሁ፡፡

አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ – ወልቂጤ ከተማ

ስለ ጨዋታው…

ጨዋታው መጥፎም ጥሩም ነው። መጥፎ የምለው በምንፈልገው መንገድ አለመሄዳችን ነው። ተጫዋቾቻችን የቻሉትን ለማድረግ ሞክረዋል ፤ ነገር ግን ከነበረን ነገር አንጻር ትንሽ ወረድ ብሏል። ግቦቹ የተቆጠሩት በራሳችን ድክመት ነው። ሁለቱም ግብ የእኛ ተከላካዮች ስህተት ነው። ይሄ ደግሞ በእግርኳስ ይከሰታልና ስህተታችንን በየጊዜው ለማረም እንጥራለን።

በተከታታይ ጨዋታዎች ባለቀ ደቂቃ ግብ ስለማስተናገዳቸው እና ከትኩረት ጋር ስለተገናኘ ነገር…

ምንም ሌላ ነገር አይባልም ፤ ይሄ ነው ቅድም ያልኩት የትኩረት ማጣት ችግር እንዳለብን እናውቃለን ፤ እንጂ በመጨረሻ ጨዋታ ተጫዋቾቼ ሌላ ችግር የለባቸውም በእናንተ እንደተጻፈው። እንደተባለው እስማማለሁ ትኩረት ማጣት ብዙ ጊዜ ይከሰታል። 90 ደቂቃ አንድ ተጫዋች ትኩረት ላያደርግ ይችላል በእኛ ሀገር።