ሪፖርት | የጣና ሞገዶቹ ባለቀ ደቂቃ በተቆጠረባቸው ጎል ነጥብ ተጋርተዋል

በምሽቱ ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ በዱሬሳ ሹቢሳ ጎል ሲመራ ቢቆይም ሲዳማ ቡና በጭማሪ ደቂቃ በአበባየሁ ዮሐንስ ጎል አቻ መሆን ችሏል።

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት አራፊ የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች በ10ኛ ሳምንት በፋሲል ከነማ ከተረቱበት ስብስብ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። በለውጦቹም በሰለሞን ሀብቱ ፣ ጊትጋት ኩት ፣ ቴዎድሮስ ታፈሰ እና ቡልቻ ሹራ ምትክ መሐሪ መና ፣ አንተነህ ተስፋዬ ፣ ሙሉቀን አዲሱ እና አቤኔዘር አስፋው ወደ ሜዳ እንዲገቡ ተደርጓል። ባህር ዳሮች በበኩላቸው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነጥብ ሲጋሩ የተጠቀሙበትን አሰላለፍ ሳይለውጡ ጨዋታውን ቀርበዋል።

ሲዳማ ቡናዎች ጨዋታውን በፈጣን ጥቃት ነበር የጀመሩት። በዚህም ይገዙ ቦጋለ በረጅሙ የተላከን ኳስ ከተከላካዮች ጋር ታግሎ ተቀብሎ በቀጥታ መትቶት ቡድኑን ቀዳሚ ሊያደርግ ቢሞክርም ግብ ጠባቂው ፋሲል በጥሩ ቅልጥፍና አውጥቶበታል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ይኸው አጥቂ የቅጣት ምት ሲሻማ ተጨራርፎ የደረሰውን ኳስ በመጠቀም ሁለተኛ ሙከራ አድርጓል። ባህር ዳሮች በበኩላቸው በ13ኛው ደቂቃ የመጀመሪያ ሙከራቸውን ሰንዝረዋል። በዚህም ዱሬሳ ሹቢሳ በግራ መስመር ከተከላካይ ጋር ታግሎ የመታው ኳስ ለጥቂት የግቡን ቋሚ ታኮ ወደ ውጪ ወጥቶበታል።

ባህር ዳሮች በሁለተኛ ጥቃታቸው ግን ግብ አስቆጥረው መሪ ሆነዋል። በ14ኛው ደቂቃም ከርቀት የተገኘን የቅጣት ምት ሔኖክ ኢሳይያስ በረጅሙ ወደ ሳጥን ሲልከው ግብ ጠባቂው ፍሊፕ ኦቮኖ መቆጣጠር ተስኖት ለቆት በቦታው የነበረው ዱሬሳ አግኝቶት መረብ ላይ አሳርፎታል። 

ባህር ዳሮች በ30ኛው ደቂቃ ፍፁም ጥሩ ኳስ በተከላካዮች መካከል ለሀብታሙ አቀብሎት መሪነታቸውን ከፍ የሚያደርጉበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር።

በግብ ጠባቂያቸው ስህተት ግብ አስተናግደው ወደ መመራት የገቡት ሲዳማ ቡናዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ይገዙን መዕከል ያደረጉ ረጃጅም ኳሶች እና ከሳጥን ውጪ ጥብቅ ኳሶችን መሞከር ያዘወተሩ ቢሆንም በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች የተሻሉ የነበሩትን የባህር ዳር ተከላካዮች ማንበርከክ አልቻሉም። የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜም በባህር ዳር አንድ ለምንም መሪነት ተጠናቋል።

የአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ተጫዋቾች በ49ኛው ደቂቃ ለአቻነት ከጫፍ ደርሰው ነበር። በዚህም ይገዙ ቦጋለ ከቀኝ መስመር ያሻማው ኳስ በመስመር ተከላካዩ ሔኖክ ተጨርፎ አቅጣጫ በመቀየር መረብ ላይ ሊያርፍ ተቃርቦ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል። ፈጣኖቹን የመስመር አጥቂዎች በመጠቀም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር የጣሩት የጣና ሞገዶቹ በ64ኛው ደቂቃ መሪነታቸውም ወደ ሁለት የሚያሳድጉበትን ዕድል የግቡ አግዳሚ መልሶባቸዋል። በዚህም ቻርለስ ሪባኑ ከሳጥን ውጪ በተከላካዮች ተጨርፎ የደረሰውን ኳስ በአንድ ንክኪ አጥብቆ መጥቶት በገለፅነው መልኩ አግዳሚው መልሶበታል።

ከ64ኛው ደቂቃ የሪባኑ ሙከራ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች ፍልሚያ ከግብ ሙከራዎች የራቀ ነበር። በእንቅስቃሴ ረገድ ባህር ዳር በእጁ የገባውን ሦስት ነጥብ አሳልፎ ላለመስጠት ሲጥር ሲዳማ ደግሞ ከጨዋታው አንዳች ነገር ለማግኘት ሲሞክር ተስተውሏል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ በተጨመሩት ደቂቃዎች ሲዳማዎች ሁለት ጊዜ የባህር ዳርን የግብ ክልል ጎብኝተው በሁለተኛው ግብ አግኝተዋል። በዚህም የዕለቱ ዳኛ አምስት ተጨማሪ ደቂቃ ጨምረው ፊሽካቸው በሚጠበቅበት ቅፅበት ሲዳማዎች የቅጣት ምት አግኝተው ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አበባየሁ ዮሐንስ በ98ኛው ደቂቃ ግብ አድርጎት ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።