ሪፖርት | ኢትዮጵያ መድን የድሬዳዋ ቆይታውን በድል አጠናቋል

የሀቢብ ከማል የፍፁም ቅጣት ምት ጎል ኢትዮጵያ መድን ኢትዮጵያ ቡናን 1-0 እንዲረታ አድርጋለች።

ኢትዮጵያ ቡና ከሀዲያ ሆሳዕናው ሽንፈት መልስ በግብ ጠባቂነት በረከት አማረን በእዝቄል ሞራኬ እንዲሁም በአጥቂ መስመር ላይ አንተነህ ተፈራን በመስፍን ታፈሰ በመተካት ጨዋታውን ሲጀምር ኢትዮጵያ መድን ከፋሲል ከነማ ነጥብ ከተጋራበት ጨዋታ ባደረገው ብቸኛ ለውጥ አማካይ ክፍል ላይ አሚር ሙደሲር ሀብታሙ ሸዋለምን ለውጦ ጨዋታውን ጀምሯል።

ጥሩ ፉክክር የተስተዋለበት ጨዋታው የኢትዮጵያ ቡና የኳስ ቁጥጥር የበላይነት እየታየበት ሲጀምር ጥሩ አደረጃጀት የነበራቸው ኢትዮጵያ መድኖችም ወደ ግራ አድልተው በተለይም ለኪቲካ ጀማ የሚልኳቸው ቀጥተኛ ኳሶች አደገኝነት ከጅምሩ ይታይ ነበር። ቡድኑ ቀዳሚውን ኢላማውን የጠበቀ መከራ ሲያደርግ 9ኛው ደቂቃ ላይ ከአብዱልከሪም ወርቁ ያስጣሉትን ኳስ ሀቢብ ከማል ከሳጥን ውጪ ሞክሮ ግብ ጠባቂው እዝቄል ሞራኬ አድኖበታል።

ኢትዮጵያ ቡናዎች በቅብብል የመድንን የኳስ ውጪ አቋቋም ለማለፍ ንክኪዎችን እያደረጉ ወደ ሳጥን ቢቀርቡም የአማካይ ክፍል ፍልሚያውን ማሸነፍ ቀላል አልሆነላቸውም። የቡና ቀዳሚ አደገኛ ሙከራም የተገኘው ከቆመ ኳስ ነበር። 20ኛው ደቂቃ ላይ ከመሀል ሜዳ በረጅሙ የተላከውን የቅጣት ምት ኳስ መሐመድኑር ናስር ወደ ውጪ ከመውጣት ሲያበርድለት መስፍን ታፈሰ ከቅርብ ርቀት ላይ ሞክሮ ለጥቂት ወጥቶበታል። ከዚህ ሙከራ በኋላም የቡና የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ከፍ ብሎ የቀጠለ ቢሆንም በመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች ግን የመድኖች የበላይነት ጎልቷል።

34ኛው ደቂቃ ላይ ባሲሩ ዑመር ያደረሰውን ሰንጣቂ ኳስ ኪቲካ ጀማ በግራ መስመር በመግባት በጥሩ ሁኔታ ተቆጣጥሮ ራምኬል ጀምስን ቢያልፍም ሙከራው ወደ ላይ ተነስቷል። ሆኖም አፍታም ሳይቆይ በቀኝ መስመር ተከላካይነት ጨዋታውን የጀመረው ጫላ ተሺታ ኪቲካ ጀማ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ሀቢብ ከማል 38ኛ ላይ ጎል አድርጎታል።

መድኖች በቀሩት ደቂቃዎችም የቡናን የቀኝ ወገን አጥቅተው መጫወትን ምርጫቸው አድርገዋል። 44ኛው ደቂቃ ላይ ኪቲካ ጀማ ከሳጥኑ መግቢያ በዚሁ አቅጣጫ እየነዳ ሳጥን ውስጥ ያደረሰውን ኳስ ወልደአማነኤል ጌቱን በማለፍ አክርሮ መትቶ በእዝቄል ቅልጥፍና ዳነበት እንጂ መድኖች መሪነታቸውን ለማስፋት ተቃርበው ነበር።

ከዕረፍት መልስ መሀመድኑር ከግራ አቅጣጫ አክርሮ በሞከረው እና አቡበከር ኑራ ባወጣው ኳስ ማጥቃት የጀመሩት ቡናዎች የተሻለ ብልጫ ኖሯቸው ሲታዩ የአቻነት ግብ ለማግኘት የተቃረቡባቸው ቅፅበቶች ነበሩ። ከእነዚህ መሀል 57ኛው ደቂቃ ላይ የመድኖችን ስህተት ተከትሎ ሳጥን ውስጥ የደረሱት ቡናዎች በመስፍን ታፈሰ ያደረጉትን ሙከራ አብዱልከሪም መሐመድ እና አቡበከር ኑራ ተጋግዘው አውጥተውታል። መስፍን ከአንድ ደቂቃ በኋላም በግንባር ያደረገው ሌላ ሙከራም ለጥቂት ወጥቶበታል።

የመጀመሪያው አጋማሽ የማጥቃት ኃይላቸው ቢቀዛቀዝም ሙሉ ለሙሉ መከላከልን ያልመረጡት መድኖች በቀጣይ ደቂቃዎች በተሻለ ሁኔታ የተጋጣሚያቸውን ጥቃት ማፈን ችለዋል። ቀጣዩ ሙከራ የተደረገባቸውም ዘግየት ብሎ 75ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን መሐመድኑር ከግራ መስመር በቀጥታ የመታው ቅጣት ምት በግቡ ቋሚ ተመልሷል። ጨዋታው በተመጣጠነ ፉክክር እስከመጨረሻው ዘልቆ ኢትዮጵያ ቡና በጭማሪ ደቂቃ አብዱልሀፊስ ቶፊቅ በግራ መስመር ይዞ በገባው ኳስ መሐመድኑር ያደረገው ሙከራ በመድኖች ርብርብ ድኖ ጨዋታው ተጠናቋል። በዚህም ኢትዮጵያ መድን ነጥቡን 26 በማድረስ የአንደኝነት ደረጃውን ይዞ የድሬዳዋ ውድድሩን ጨርሷል።

ከጨዋታው ማብቃት በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች በተነሳሽነት ረገድ ቡድናቸው ተሻሽሎ ማየታቸውን የጠቆሙት ኢትዮጵያ ቡናን ዛሬ የመሩት አሰልጣኝ ዮሴፍ ተስፋዬ በቀጣይ ጨዋታዎች ከጉዳት ከሚመለሱ ተጫዋቾች ጋር ተሻሽለው እንደሚመጡ ተናግረዋል። ሦስት ነጥብ ማሳካታቸውን ተከትሎ ጥሩ ሊባል የሚችል ጨዋታ መሆኑን ያነሱት አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ አሸንፈው ወደ ዕረፍት ማምራታቸው የሥነልቦና ጥቅም እንዳለው ጠቁመው ቡድናቸው 2010 ላይ ከከፍተኛ ሊግ አድጎ ቻምፒዮን ካደረጉት ጅማ አባ ጅፋር ጋር እንደሚመሳሰል አብራርተዋል።