የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ሀዋሳ እና አርባምንጭ ድል ቀንቷቸዋል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ7ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ዛሬ ሲቀጥሉ ሀዋሳ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ ጣፋጭ ሦስት ነጥብን ሲያገኙ የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ልደታ ክፍለ ከተማ ጨዋታ ነጥብ በመጋራት ተጠናቋል።

የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ልደታ ክፍለ ከተማ ጨዋታ እጅግ አስደናቂ የሜዳ ላይ ፉክክርን አስመልክቶን በመጨረሻም ነጥብ በመጋራት ፍፃሜውን አግኝቷል። መሀል ሜዳ ላይ ያመዘነ የጨዋታ መንገድን በተመለከትንበት የሁለቱ ቡድኖች መርሀግብር ጎል የተመለከትነው ገና 3ኛው ደቂቃ ላይ ነበር።

ሽታዬ ሲሳይ እና ስላማዊት ጎሳዬ ባደረጉት ግሩም ቅብብል በመጨረሻም የደረሳትን ኳስ ተጠቅማ ምንትዋብ ዮሐንስ የአሰልጣኝ መሠረት ማኔን ቡድን ቀዳሚ አድርጋለች። ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በይበልጥ የማጥቃት ተሳትፎ ላይ በይበልጥ ኃይላቸውን ያደረጉት ልደታ ክፍለ ከተማዎች 11ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ህዳት ካሱ ከግራ አቅጣጫ ወደ ውስጥ ሰብራ በመግባት ጎል አስቆጥራ ቡድኗን አቻ አድርጋለች። የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ ሲመጣ ተጨማሪ ጎልን ለማከል ትጋት ያልተለያቸው ልደታ ክፍለ ከተማዎች 21ኛ ደቂቃ ላይ ህዳት ካሱ ለራሷ እና ለቡድኗ ሁለተኛ ግብን አክላ ተመሪ የነበረውን ቡድን ወደ 2ለ1 መሪነት አሸጋግራለች።

መሀል ሜዳ ላይ በተወሰነ መልኩ በተጋጣሚያቸው ለመበለጥ የተገደዱት ኤሌክትሪኮች በፍጥነት ህይወት ደንጊሶን ከተጠባባቂ ወንበር ላይ ወደ ሜዳ በማስገባት ለማስተካከል የጣሩበት ሂደት ፍሬ አፍርቶ ተቀይራ በገባች በሁለት ደቂቃ ልዩነት ከሳጥን ውጪ ህይወት ግሩም ግብን አስቆጥራ ቡድኗን አቻ አድርጋለች። ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተመልሶ ቀጥሎ ለመሸናነፍ ሁለቱም የመዲናይቱ ክለቦች እጅጉን ጥረት ያደረጉ ቢሆንም በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠሩ ግቦች 2-2 ጨዋታው ተጠናቋል።

8 ሰዓት ላይ አርባምንጭ ከተማን ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያገናኘው ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክርን በሁለቱም በኩል አስመልክቶን በመጨረሻም በአዞዎቹ እንስቶች የበላይነት ተደምድሟል። የአርባምንጭ ከተማ ረጃጅም እንዲሁም ከመስመር የሚነሱ ኳሶችን ባስተዋልንበት እንዲሁም የቅዱስ ጊዮርጊስ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት በተንፀባረቀበት ጨወታ ከእንቅስቃሴ ውጪ ረጅሙን ደቂቃ በሙከራዎች የታጀበ አልነበረም። ይሁን እንጂ 72ኛው ደቂቃ ላይ ልማደኛዋ አጥቂ ቤቴልሄም ታምሩ አርባምንጭ ከተማን ሶስት ነጥብ ያስጨበጠች ብቸኛ ጎልን ከመረብ አሳርፋ ጨዋታው 1-0 በሆነ ውጤት ፍፃሜን አግኝቷል።

የሳምንቱ የማሳረጊያ ጨዋታ በሆነው የሀዋሳ ከተማ እና ይርጋጨፌ ቡና ጨዋታ በሀዋሳዎች 3ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል። የሀዋሳ ከተማ የበላይነት አይሎ ባየንበት በዚህ ጨዋታ በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ በእንቅስቃሴ ረገድ ቡድኑ የበላይ ቢሆንም ወደ ሶስተኛው የተጋጣሚ የግብ ክልል ደርሶ ጥቃት ለመሰንዘር ግን ብዙም ድርሻ አልነበራቸውም ይልቁንስ ይርጋጨፌ ቡናዎች የሚሰሩትን ስህተት ለመጠቀም ጥረት ወደ ማድረጉ ፊታቸውን ያዞሩት የአሰልጣኝ መልካሙ ታፈረው ሀዋሳ ተጫዋቾች 32ኛው ደቂቃ ላይ በዚህ የጨዋታ መንገድ በነፃነት መና አማካኝነት ጎል አግኝተው መሪ ሆነዋል።

ሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ በተጀመረ የሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ሲሳይ ገብረዋህድ ከሳጥን ውጪ እጅግ የሚያስደንቅ ግብ ከመረብ አገናኝታ ሀዋሳዎችን ወደ 2-0 አሸጋግራለች። ከመጀመሪያው አጋማሽ በይበልጥ ተሻሽለው ወደ ሜዳ የገቡት ይርጋጨፌ ቡናዎች ወደ ጨዋታ የሚመልሳቸውን በርከት ያሉ ዕድሎችን የማግኘት አጋጣሚን ቢያገኙም የሀዋሳን ተከላካይ አልፎ ግብ ለማግኘት ግን ተቸግረው ተስተውሏል። በአንፃሩ የሚያገኙትን ዕድል ላለማባከን ጥረት የሚታይባቸው ሀዋሳ ከተማዎች ተቀይራ በገባችው ረድኤት አስረሳኸኝ አማካኝነት ሶስተኛ ጎልን ማግኘት ችለዋል። ሶስት ጎሎች የተቋጠረባቸው ይርጋጨፌዎች በመጨረሻዎቹ የጨዋታው ደቂቃዎች በቅድስት ጌታቸው አማካኝነት የማስተዛዘኛ ግብን ቢያገኙም ጨዋታው ግን በሀዋሳ 3-1 የበላይነት ከድምዳሜ ደርሷል።