መረጃዎች | 49ኛ የጨዋታ ቀን

የ13ኛ የጨዋታ ሳምንት ሦስተኛ ቀን መርሃግብሮችን የተመለከቱ መረጃዎች በተከታዩ መልኩ ቀርበዋል።

አዳማ ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ

ከስጋት ቀጠና መላቀቅን የሚያልሙት አዳማ ከተማዎች ከተማቸው በድል ለመሰናበት ከሚያልሙት ድሬዳዋ ከተማ የሚያገናኘው የዕለቱ ቀዳሚ መርሃግብር ትኩረትን የሚስብ ነው።

በተከታታይ ሽንፈቶች መነሻነት በተወሰነ መልኩ ጫና ውስጥ ገብተው የነበሩት አዳማ ከተማዎች በመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች ባሳኳቸው አራት ነጥቦች በመጠኑም ቢሆን ተንፈስ ያሉ ይመስላል። አሁን ላይ ቡድኑ 11 ነጥቦች 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

መሻሻሎችን እያሳዩ የሚገኙት አዳማ ከተማዎች የውድድር ዘመኑን ሲጀምሩ የነበሯቸውን አዎንታዊ ጎኖቹን ዳግም እያገኙ ይመስላል በተለይም ሀዲያን በገጠሙበት የመጨረሻ ጨዋታ ቡድኑ በብዙ መመዘኛዎች የተሻሻለበትን የጨዋታ ቀን አሳልፏል። በጨዋታው ቡድኑ ምንም እንኳን ድል ባይቀናውም በርከት ያሉ የግብ ዕድሎችን ሲፈጥሩ አስተውለናል ይህም በጨዋታው የታዘብነው አዎንታዊ ጉዳይ ቢሆንም በተለይ በሰንጠረዡ ካሉበት አደገኛ ስፍራ ለመውጣት በመጓጓት በሚመስል መልኩ በአንፃሩ የተመለከትናቸው የአጨራረስ ክፍተቶችን በቀጣይ ግን ማረም ይኖርባቸዋል።

አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ በነገው ጨዋታ ጉዳት ላይ የሚገኘውን ወሳኙን አጥቂያቸው ዳዋ ሆቴሳን ጨምሮ ግብ ጠባቂውን ሰዒድ ሀብታሙ እና የተከላካይ አማካዩ ፍሬድሪክ አንሳህን የማይጠቀሙ ሲሆን ሌሎቹ የቡድኑ ተጫዋቾች ግን ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆናቸው ታውቋል።

በከተማቸው ከአስደናቂ ግስጋሴ ማግስት የመጀመሪያ ሽንፈታቸውን ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ያስተናገዱት ድሬዳዋ ከተማዎች በ18 ነጥቦች በሰንጠረዡ 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

በሊጉ ከስምንት ጨዋታዎች በኋላ በወላይታ ድቻ ሽንፈት ያስተናገዱት ድሬዳዋ ከተማዎች በጨዋታው ብዙ መመዘኛዎች በተለይም የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ ሀሳቦች አጥሯቸው አስተውለናል። በቀጥተኛ አጨዋወት በረጅሙ በሚጣሉ ኳሶች ጥቃትን ለመሰንዘር የሚጥረው ቡድን የተከላካይ መስመራቸውን ቁመት በራሳቸው ወስነው ከሚገቡ ተጋጣሚዎች ጋር እንዴት እንደሚቸገር የወላይታ ድቻው ጨዋታ ፍንጭ ሰጥቶ አልፏል። ይህም ቡድኑ አሁንም ስለአማራጭ የማጥቂያ መንገዶች በደንብ ማሰብ እንዳለበት አስመልክቶናል።

ወደ መቀመጫ ከተማሙ ከተመለሰ ወዲህ አሰደናቂ የሜዳ ላይ ብቃትን ከውጤት ጋር አጅበው ያሳዩት ድሬዳዋ ከተማዎች በመቀመጫ ከተማቸው የሚኖራቸውን የመጨረሻ ጨዋታ በድል ለመቋጨት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

አሰልጣኝ ዮርዳኖስ ዓባይ በነገው ጨዋታ የመስመር አማካዩን አቤል ከበደ እና ዳንኤል ተሾመን በጉዳት ምክንያት የማያገኙ ሲሆን ያሬድ ታደሰ እና አቤል አሰበ ግን ከጉዳት መልስ በነገው ዕለት ግልጋሎት ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከዚህ ቀደም ሁለቱ ቡድኖች በ20 አጋጣሚዎች እርስ በእርስ የተገናኙ ሲሆን አዳማ ከተማዎች 9 ጨዋታዎችን በድል ሲወጡ ድሬዳዋ ከተማዎች በአንፃሩ 6 ጨዋታዎችን ድል ማድረግ ችለዋል ፤ ቀሪዎቹ 5 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።

የዕለቱን ቀዳሚ መርሃግብር ኢንተርናሽናል ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ በመሀል ዳኝነት ፣ ሰብስቤ ጥላዬ እና ዘመኑ ሲሳዬነው በረዳትነት እንዲሁም ኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት እንዲመሩ ተመድበዋል።

ወላይታ ድቻ ከ ሃዋሳ ከተማ

ከፍ ያለ የፉክክር ስሜት እንደሚታይበት የሚገመተው እና በሦስት ነጥቦች ልዩነት በሰንጠረዡ በሦስት ደረጃዎች ተለያይተው የሚገኙትን ወላይታ ድቻ እና ሀዋሳ ከተማን የዕለቱ ሁለተኛ መርሃግብር ያገናኛል።

በባህር ዳር ከተማ ከነበራቸው እጅግ አስከፊ የውድድር ዘመን አጀማመር ማግስት ቀስ በቀስ በድሬዳዋው ውድድር የዓመቱን ጉዟቸውን እያቃኑ የሚገኙት ወላይታ ድቻዎች በ15 ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

በመጨረሻ ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ሁለተኛ የማሸነፍ ግምት አግኝተው በገቡባቸው የፋሲል ከነማ እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታዎች የአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማሪያሙ ቡድን ሳይጠበቁ መሉ ስድስት ነጥቦች ያሳኩ ሲሆን ቡድኑ በአቅሙ የተጋጣሚን ጠንካራ ጎን እያከሸፈ በሽግግር ፣ በቆሙ እንዲሁም በተሻጋሪ ኳሶች የሚፈጥራቸውን ጥቂት የግብ እድሎች በአግባቡ በመጠቀም ነጥቡን እያሻሻለ ይገኛል።

ወላይታ ድቻዎች በነገው ጨዋታ ከመስመር ተከላካያቸው ሳሙኤል ተስፋዬ ውጭ የተቀሩት የቡድኑ አባላት በሙሉ ጤንነት ላይ ይገኛሉ።

ወጥ የሆነ የውድድር ዘመን ጉዞን ለማድረግ የተቸገሩት ሀዋሳ ከተማዎች በመጨረሻ ጨዋታቸው ኢትዮ ኤሌክትሪክን ገጥመው ከአራት ተከታታይ ጨዋታዎች በኃላ ሙሉ ሦስት ነጥብ ማሳካታቸውን ተከትሎ በ18 ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ከሰሞኑ ከፍተኛ የመነሳሳት ችግር ይስተዋልበት የነበረው ቡድኑ ወደ ድል በተመለሱበት የኤሌክትሪኩ ጨዋታ ግን እጅጉን ተሻሽለው ተመልክተናል። በጨዋታው ግብ ጠባቂያቸው መሀመድ ሙንታሪ ፍፁም ድንቅ ብቃቱን ቢያሳይም ሃዋሳዎች ከወትሮው በተሻለ ከኳስ ጋር በዓላማ ሲጫወት አስተውለናል። ከዚህ ባለፈም ቡድኑ የመስመር ተከላካዮቹን ከመከላከል ባለፈ ይበልጥም ወደ ፊት ገፍተው እንዲጫወቱ ነፃነት ሰጥተው የተመለከትን ሲሆን ይህን አዎንታዊነት በምን ያህል መልኩ ያስቀጥሉታል የሚለው ጉዳይ ግን ይጠበቃል።

በሃዋሳ ከተማዎች በኩል መድሀኔ ብርሀኔ እና በቃሉ ገነነ የመሰለፋቸው ነገር ሲያጠራጥር ወሳኙ አጥቂያቸው ሙጂብ ቃሲም ግን ከጉዳት ተመልሷል።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በሊጉ ለ16 ያክል ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ወላይታ ድቻዎች 7 ጊዜ በማሸነፍ የበላይ ሲሆኑ ሃዋሳ ከተማዎች በበኩላቸው 4 ጨዋታዎችን በድል ሲወጡ የተቀሩት 5 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተፈፀሙ ነበሩ።

የምሽቱን ጨዋታ በአራት አዳዲስ ዳኞች የሚመራ ሲሆን ባሪሶ ባላንጎ በታሪኩ ሁለተኛ የሊጉን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ሲመራ ፣ ኤልያስ መኮንን እና ደስታ ጉራቻ በረዳትነት እንዲሁም መለሰ ንጉሴ በአራተኛ ዳኝነት ተመድቧል።