ሪፖርት | አዳማ ከተማ ወሳኝ ድል ተቀዳጅቷል

በመቀመጫ ከተማቸው የመጨረሻ ጨዋታቸውን ያደረጉት ድሬዳዋ ከተማዎች በአዳማ ከተማ 2-0 በመሸነፍ ቆይታቸውን አጠናቀዋል።

10፡00 ላይ አዳማ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ ሲገናኙ አዳማዎች በ12ኛው ሣምንት ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ያለግብ በተለያዩበት ጨዋታ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል።

በዚህም ኩዋሜ ባህ ፣ ቢንያም አይተን ፣ መስዑድ መሐመድ እና አድናን ረሻድ በ ሰዒድ ሀብታሙ ፣ ዊልያም ሰለሞን ፣ ፍሬድሪክ ሀንሰን እና አብዲሳ ጀማል ተተክተው ገብተዋል። ብርቱካናማዎቹ በበኩላቸው በወላይታ ድቻ 1-0 ሲሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ብሩክ ቃልቦሬን እና አሣንቴ ጎድፍሬድን አስወጥተው በምትካቸው ኢያሱ ለገሠን እና ሙኸዲን ሙሳን አስገብተው ለጨዋታው ቀርበዋል።

ጨዋታው በጀመረ አንድ ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ቢንያም አይተን የአማረ በቀለን ስህተት ተጠቅሞ የውድድር ዘመኑን ፈጣን ግብ በማስቆጠር አዳማ ከተማን መሪ አድርጓል። 

በመጀመሪያ ደቂቃዎች በተደጋጋሚ የተጋጣሚ የግብ ክልል የደረሱት አዳማዎች 6ኛው ደቂቃ ላይ ፈታኝ ሙከራ ሲያደርጉ በቀኝ መስመር የተገኘውን የማዕዘን ምት መስዑድ መሐመድ ሲያሻማ አዲስ ተስፋዬ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ ሄኖክ ሀሰን ግብ ከመሆን አግዶታል። በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ፉክክር ቢኖርም ድሬዳዋ ከተማዎች ባልተረጋጋው የተከላካይ መስመራቸው 14ኛው ደቂቃ ላይ ሁለተኛ ግብ ሊያስተናግዱ ነበር። አማረ በቀለ በድጋሚ ስህተት ሲሠራ ኳሱን ያገኘው አሜ መሐመድ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ዐብዩ ካሣዬ አስወጥቶበታል።

ከዚህ ሙከራ በኋላ ብርቱካናማዎቹ የተሻለ ወደፊት ተጠግተው ለመጫወት ሲሞክሩ በጥሩ ቅብብል የሚወስዱትን ኳስ መዳረሻውን ቢንያም ጌታቸው ላይ ለማድረግ ቢሞክሩም የግብ ዕድሎችን ከጨዋታ ውጪ በሆነ እንቅስቃሴ ሲያባክኑ ተስተውሏል። በአጋማሹ ፈታኙን ሙከራም 43ኛው ደቂቃ ላይ አድርገዋል። በቀኝ መስመር የተሰጠውን የቅጣት ምት ጋዲሳ መብራቴ አሻምቶት በአዳማ ተከላካዮች ሲመለስ ያገኘው ሱራፌል ጌታቸው ግሩም ሙከራ ቢያደርግ ኳሱ የላዩን የግቡ አግዳሚ ገጭቶ ተመልሶበታል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በተመሳሳይ ሂደት ሲቀጥል 53ኛው ደቂቃ ላይ ዊሊያም ሰለሞን ለመስዑድ መሐመድ በጥሩ ዕይታ አመቻችቶ ሲያቀብል መስዑድ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው መልሶበታል። ይሁንና ኳሱ ሲመለስ ያገኘው አሜ መሐመድ ለዊሊያም ሰለሞን ወደ ኋላ መልሶ ሲያቀብል ግራ መስመር ላይ የነበረው ዕረፍት ላይ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ዊልያም ሰለሞን ከሳጥን ውጪ ድንቅ ግብ አስቆጥሮ የክለቡን መሪነት አጠናክሯል።

 አሰልጣኝ ይታገሡ እንዳለም ዕረፍት ላይ ያደረጉት ቅያሪ በጥቂት ደቂቃዎች ውጤታማ አድርጓቸዋል።

ባልተረጋጋ ሁኔታ የማጥቃት እንቅስቃሴ እያደረጉ የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የተቸገሩት ድሬዎች 58ኛው ደቂቃ ላይ የተሻለ የግብ ማግባት አጋጣሚ ሲያገኙ በሳጥኑ በግራ ክፍል ላይ የነበረው ሙኸዲን ሙሳ ለቢንያም ጌታቸው ከማቀበል አማራጭ ጋር ጥሩ ኳስ ቢያገኝም በደካማ አጨራረስ የግብ ዕድሉን አባክኗል። በቡድናቸው እንቅስቃሴ ደስተኛ ያልሆኑት አሰልጣኝ ዮርዳኖስ ዓባይም ተጫዋቾቹን በመቀያየር የማጥቃት ክፍላቸው ላይ የአደራደር ቅርፅ ለውጥ ለማድረግ ተገደዋል።

አስፈሪ የማጥቃት እንቅስቃሴ የማይታይባቸው ብርቱካናማዎቹ በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለውን ሙከራቸውን 76ኛው ደቂቃ ላይ አድርገዋል። በቀኝ መስመር የተገኘውን የቅጣት ምት ተቀይሮ የገባው አብዱለጢፍ መሐመድ ሲመታ ጀሚል ያቆብ በግንባሩ ገጭቶ አቅጣጫ ሲያስቀይረው ኳሱን ያገኘው ኤልያስ አህመድ ጥሩ ሙከራ ሲያደርግ ኳሱ የግብጠባቂው ኩዋሜ ባህን እጅ ጥሶ ማለፍ ቢችልም የላዩ አግዳሚ መልሶበታል። ከዚህ ሙከራ በኋላም ፈታኝ ሙከራ ሳንመለከትበት አዳማዎች ጨዋታውን ተረጋግተው በመቆጣጠር ተሳክቶላቸው ድሬዳዋ ከተማን 2-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የድሬዳዋ ከተማው አሰልጣኝ ዮርዳኖስ ዓባይ ጨዋታውን በተዘጋጁት ልክ አለማግኘታቸውን ሲናገሩ ተጫዋቾቹ በሥነልቦና ረገድ ዝቅ ብለው መቅረባቸውን እና ጨዋታው ደረጃቸውን እንደማይመጥን ግን ለቀጣይ እንደሚያስተካክሉ ሲናገሩ በተከታታይ ጨዋታዎች ያሳዩት ጨዋታ ደካማ ነበር ሀሳባቸውን ሰጥተዋል። በጨዋታው ድል የቀናቸው የአዳማ ከተማ አሰልጣኝ ይታገሡ እንዳለ በበኩላቸው ቀድመው ግብ ማስቆጠራቸው በሥነልቦና ረገድ እንደረዳቸው ሲናገሩ ከአንድ ጨዋታ በኋላ ያለው ዕረፍት ተጨምሮበት የተጎዱ ተጫዋቾች ማገገም ጋር አዳማ ላይ ተሻሽለው እንደሚቀርቡ ጠቁመዋል።