ፈረሰኞቹ ከተከላካያቸው ጋር በስምምነት ተለያይተዋል

ከ2012 ጀምሮ በቅዱስ ጊዮርጊስ የቆየው ተከላካይ ከክለቡ ጋር በስምምነት መለያየቱ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያውን ዙር ውድድር በትናንትናው ዕለት አገባዶ ለብሔራዊ ቡድን የቻን ዝግጅት እና ውድድር ረዘም ላለ ቀናት መቋረጡ ይታወቃል። ውድድሩ በተቋረጠ ማግስት ደግሞ የአጋማሽ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ዛሬ በይፋ ተከፍቷል። እርግጥ እስካሁን ለአዲስ ክለብ የፈረመ ተጫዋች ባይኖርም አንድ ተጫዋች ግን ቀሪ ውል እያለው ከክለቡ ጋር በስምምነት መለያየቱ ተረጋግጧል።

ከክለቡ ጋር የተለያየው ተጫዋች ደስታ ደሙ ነው። የቀድሞ የወልዋሎ ዓ/ዩ፣ ደደቢት እና ሙገር ተጫዋች 2012 ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስን መቀላቀሉ ይታወሳል። የመሐል እና የመስመር ተከላካይ ሆኖ መጫወት የሚችለው ደስታ ከፈረሰኞቹ ጋር ውል ቢኖረውም በዛሬው ዕለት በስምምነት ውሉን መቅደዱ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።