የሲዳማ ክልል እግርኳስ ፌዴሬሽን ቢሮውን በይፋ አስመርቋል

የሲዳማ ክልል እግር ኳስ ፌድሬሽን በዘንድሮው ዓመት በርካታ ሥራዎችን ለመስራት ማሰቡን ዛሬ በተከናወነ ሥነስርዓት ላይ ገልጿል።

ከተመሠረተ ጥቂት ዓመታትን ያስቆጠረው የሲዳማ ክልል እግርኳስ ፌድሬሽን ከምስረታው ጀምሮ ፌድሬሽኑን ከማጠናከር ጀምሮ ከታዳጊ እስከ አዋቂዎች ድረስ በሁለቱም ፆታ የተለያዩ የውስጥ ውድድሮችን ጨምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን የሚዘጋጁ ውድድሮችን እያስተናገደ ዘልቋል።

ዘንድሮም የተለያዩ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን ጨምሮ የተለያዩ ውድድሮችን ለማዘጋጀት በዝግጅት ላይ የሚገኘው ፌድሬሽኑ በዛሬው ዕለት በክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ትብብር የከፈተውን ቢሮ በይፋ አስመርቋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ አዲሱ ቃሚሶ ፣ የሲዳማ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ፍሬው አሬራ እና የክልሉ ፌድሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ አንበሴ አበበ በተገኙበት ቢሮ የተመረቀ ሲሆን በቀጣይ በሰው ኃይል ፣ በስታዲየም ግንባታ እና የታዳጊ ተጫዋቾች መሠረተ ልማት ላይ ትኩረት አድርገው ለመስራት ዕቅድ መያዙን በሥነስርዐቱ ላይ ተገልጿል።