ቻን | አልጄሪያ ለሞሮኮ ጥያቄ ምላሽ ሰጥታለች

የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን በቻን ውድድር ላይ ለመሳተፍ ያስቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ በተመለከተ የውድድሩ አዘጋጅ ምላሽ ሰጥታለች።

በ18 ብሔራዊ ቡድኖች መካከል የሚደረገው የዘንድሮ የቻን ውድድር ሊጀመር አስር ቀናት ቀርተውታል። ብሔራዊ ቡድኖች ለዚህ ውድድር ዝግጅታቸውን እያደረጉ ባለበት በዚህ ሰዓት በሞሮኮ በኩል የተሰማው ዜና ውድድሩን እንዳያጠለሽ ተሰግቷል። በዚህም በአልጄሪያ እና ሞሮኮ የፖለቲካ ግንኙነት አልጄሪያ ከመስከረም 2021 ጀምሮ በዐየር ክልሏ የሞሮኮ የዐየር የትራንስፖርት አማራጮች እንዳይገቡ መከልከሏ ይታወቃል። ይህንን ተከትሎ ከሞሮኮ ወደ አልጄሪያ በቀጥታ የሚደረጉ በረራዎች የሉም። በዚህ የቻን ውድድር የሚሳተፈው የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን ደግሞ ከሀገሩ ራባት ወደ አልጄሪያ ኮንስታንቲን ልዑካኑን ይዞ በራሱ ዐየር መንገድ የሚጓዝ ልዩ በረራ ካልተፈቀደ በውድድሩ እንደማይሳተፍ ይፋ ማድረጉን ከቀናት በፊት ዘገባ አቅርበን ነበር።

\"\"

የአልጄሪያ መንግስት አሁን እንዳስታወቀው ከሆነ የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድንን ከራባት ወደ ኮንስታንቲን በቀጥታ ይዞ ለሚመጣ አውሮፕላን የዐየር ክልሉን ክፍት እንደማያደርግ ለካፍ ይፋ አድርጓል። ይህንን ተከትሎ ሞሮኮ ያስቀመጠችው ቅድመ ሁኔታ አሉታዊ ምላሽ አግኝቷል።

ይህንን የአልጄሪያ ምላሽ ተከትሎ ሞሮኳዊያን በይፋ ያስተጋቡት ግብረ-መልስ ባይኖርም ከውድድሩ ራሳቸውን ሊያገሉ የሚችሉበት ዕድል ሊኖር እንደሚችል እየተዘገበ ይገኛል።

ሞሮኮዎች ቀድመው እንደገለፁት ያስቀመጡት ቅድመ ሁኔታ ባለመሟላቱ ራሳቸውን ከውድድሩ ሙሉ ለሙሉ ያገላሉ ወይስ ሀሳብ በመቀየር በሌላ ሀገር የበረራ አማራጭ ወደ አልጄሪያ ተጉዘው ውድድራቸውን ያደርጋሉ የሚለው ይጠበቃል።

\"\"

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ታኅሣሥ 29 እና ጥር 1 ከሞሮኮ የቻን ቡድን ጋር ሁለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን ለማድረግ ቀጠሮ መያዙ ይታወቃል።