የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ሀዋሳ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወሳኝ ድል አሳክተዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ10ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ መደረግ ጀምረው ሀዋሳ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ተጋጣሚዎቻቸውን ሲረቱ አርባምንጭ ከተማ ከይርጋጨፌ ቡና ጋር ያለ ጎል አጠናቀዋል።

በሀዋሳ እየተደረገ የሚገኘው የ2015 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 10ኛ ሳምንት የጨዋታ ቀኑ ላይ የደረሰ ሲሆን በሦስት መርሀግብር ቀጥሎ ተደርጓል። ረፋድ 4 ሰዓት ጠንካራ ፉክክርን ያስመለከተን የቦሌ ክፍለ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ ቀዳሚው ጨዋታ ነበር። የቦሌ ክፍለ ከተማ የኳስ ቁጥጥርም ሆነ የግብ ሙከራዎች ጎልተው በታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ በአንፃሩ ሀዋሳ ከተማዎች በብዙ ረገድ ደካሞች ሆነው የታዩበት ነበር ማለት ይቻላል።

\"\"

የጨዋታውን የኃይል ሚዛን ወደ ራሳቸው በማድረግ ከመስመር እና ከመሀል ሜዳ በሚፈጠሩ ዕድሎች ተሻጋሪ ኳሶች ላይ አተኩረው መንቀሳቀስን የቀጠሉት ቦሌዎች 10ኛው ደቂቃ ላይ መሪ መሆን ችለዋል። ከግራ መስመር የተጣለላትን ኳስ የሀዋሳ ተከላካዮችን ስህተትን ተጠቅማ ንግስት በቀለ ቦሌን መሪ አድርጋለች። ሀዋሳ ከተማዎች በአጋማሹ ወደ ጨዋታ በፍጥነት ለመመለስ ጥረት ለማድረግ ሲታትሩ ቢታዩም የቦሌን የተከላካይ ክፍል አልፎ ግብ ለማስቆጠር ባለ መቻላቸው አጋማሹ 1-0 ሊገባደድ ችሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው ሲመለስ አሰልጣኝ መልካሙ ታፈሰ ሦስት ተጫዋቾችን አከታትለው በማስገባት አርባ አምስቱን በሚገባ በመቆጣጠር በተጋጣሚያቸው ላይ በተቃራኒው ብልጫን ሲወስዱ ገና በጊዜ መከላከልን መርጠው ለመጫወት የሞከሩት ቦሌዎች በአንፃሩ ደካማ የጨዋታ መንገድን መከተላቸው የኋላ ኋላ ዋጋ አስከፍሏቸዋል። ሀዋሳዎች የበላይነታቸውን ቀጥለው 57ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ጨዋታ የሚመልሳቸውን ጎል አግኝተዋል። ሲሳይ ገብረዋህድ በግራ የቦሌ የግብ ክልል የተገኘን ቅጣት ምት ወደ ጎል ስታሻማ መንደሪን ክንዲሁን በግንባር ገጭታ በማስቆጠር ሀዋሳን አቻ አድርጋለች። ጨዋታውን አሸንፎ ለመውጣት ይበልጥ ጥቃት መሰንዘርን ያስቀጠሉት ሀዋሳዎች ተቀይራ በገባችው ነፃነት መና ጎል ከተመሪነት ወደ መሪነት ተሸጋግረዋል። ለሀዋሳ ሁለተኛ ጎል ከመረብ ያገናኘችው አጥቂዋ ነፃነት ጎል ካስቆጠረች በኋላ የላይኛውን መለያ በማውለቅ ደስታዋን የገለፀችበት መንገድ በርካቶችን ፈገግ ያሰኘ ሲሆን ጨዋታውም በሀዋሳ 2-1 አሸናፊነት ተደምድሟል።

የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ አርባምንጭ ከተማን ከ ይርጋጨፌ ቡና ያገናኘ ሆኗል። ሙሉውን የጨዋታ አጋማሽ ብዙም ለተመልካች ሳቢ ያልነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በአጋማሾቹ የተለየ ልዩነትን ሳንመለከት ያለ ጎል ተጠናቋል።

\"\"

ተጠባቂ የነበረው የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና መቻል ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በጊዜ ያገኟት ብቸኛ ጎል ሦስት ነጥብ አስገኝታላቸዋለች። በመጀመሪያው አጋማሽ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በመስመር በኩል በሚደረጉ ተሻጋሪ ኳሶች መቻሎች በበኩላቸው ከመሀል ሜዳ መነሻቸውን ከሚያደርጉ እና ወደ አጥቂ ክፍሉ ከሚደረጉ ቅብብሎች በማድረስ ጥቃትን ለመሰንዘር ቢጥሩም በተሻለ ተሳትፎአቸው ጎልቶ ይታይ የነበረው የአሰልጣኝ መሠረት ማኔ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ነበር። በሁለቱ ኮሪደሮች በኩል የመቻልን የመከላከል ድክመት በአግባቡ ለመጠቀም የቻሉት ኤሌክትሪኮች ከቀኝ በኩል መነሻን ያደረገች ተሻጋሪ ኳስን 17ኛ ደቂቃ ላይ አይናለም አሳምነው የመቻል ተከላካዮች እና ግብ ጠባቂዋ እምወድሽ ይርጋሸዋን ስህተት ተጠቅማ በድንቅ አጨራረስ ቡድኗን መሪ አድርጋለች።

በሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ መቻሎች ወደ ጨዋታ ለመመለስ የጣሩበት ቢሆንም በጥብቅ መከላከል በመልሶ ማጥቃት በመጫወት ግባቸውን ሳያስደፍሩ የዘለቁት ኤሌክትሪኮች ተሳክቶላቸው 1-0 ጨዋታውን አሸንፈው ወጥተዋል።