የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ተጠባቂው ጨዋታ በኢትዮ ኤሌክትሪክ አሸናፊነት ተጠናቋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ12ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ በሁለት መርሐ-ግብሮች ሲጀመር በተጠባቂው ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በመጨረሻ ደቂቃ ጎሎች ሀዋሳን 2ለ0 ሲረታ አርባምንጭ ከተማም ወሳኝ ድልን አስመዝግቧል።

የመጀመሪያው ዙር ጨዋታዎች ሊጠናቀቁ የአንድ ሳምንት ዕድሜ ብቻ የቀረው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በሁለት መርሐ-ግብሮች የ12ኛ ሳምንት ጀምሯል። ቀደም ብሎ ረፋዱን የጀመረው የአርባምንጭ ከተማ እና አዳማ ከተማ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠሩ ሶስት ጎሎች እንስት አዞዎቹን ባለ ድል አድርጓቸዋል። በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በእንቅስቃሴ እና በጎል ሙከራዎች አርባምንጮች የተሻለ የበላይነት የነበራቸው ሲሆን አዳማ ከተማዎች በአንፃሩ አመዛኙን ደቂቃዎች መሀል ሜዳ ላይ በቁጥር በዝተው በሚደረጉ ቅብብሎች ለመጫወት ጥረት ለማድረግ የሞከሩ የነበረ ቢሆንም የኳስ ቁጥጥሩን ወደ ራሳቸው አድርገው የሚንቀሳቀሱት አርባምንጮች ግን የተዋጣላቸው ነበሩ።

ጨዋታው 30ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ አማካዩዋ አይናለም መኮንን በጥሩ ቅልጥፍና የሰጠቻትን ኳስ ሠርካለም ባሳ በቀላሉ ጎል አድርጋ ቡድኑን መሪ አድርጋለች። ተደጋጋሚ ጥቃት መሰንዘራቸውን አጠናክረው የቀጠሉት አርባምንጮች ከአምስት ደቂቃ በኋላ የአይናለም መኮንን ድንቅ የማቀበል አቅም ታይቶበት ቤቴልሄም ታምሩ በመጨረሻም ነፃ አቋቋም ላይ ለተገኘችው ሠርካለም ሰጥታት አጥቂዋ በድጋሚ ለቡድኗ እና ለራሷ ሁለተኛ ኳስ ከመረብ አዋህዳለች። አጋማሹ ሊገባደድ አንድ ደቂቃ ሲቀረው ደግሞ ይህቺው ሠርካለም ባሳ የአርባምንጭን መሪነት ወደ 3ለ0 ስታደርግ ለራሷም ሀትሪክ መስራት ችላለች።

ከዕረፍት ጨዋታው ተመልሶ ሲቀጥል አርባምንጭ ከተማዎች በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ላይ ያሳዩ የነበሩትን የአጨዋወት መልክ ሳይለውጡ ሲቀርቡ በአንፃሩ በመጀመሪያው አጋማሽ ከነበረባቸው ድክመት በሚገባ ራሳቸውን አርመው የተመለሱት አዳማ ከተማዎች ወደ ጨዋታ ለመመለስ ብርቱ ትግል ውስጥ ቢሰነብቱም በቀዳሚው አርባ አምስት ሠርካለም ባሳ ባሳረፈችባቸው ሦስት ጎሎች በአርባምንጭ ከተማ 3ለ0 ተሸንፈው ወጥተዋል።

\"\"

ተጠባቂ የነበረው እና በደረጃ ሰንጠረዡ በጎል ክፍያ ተበላልጠው ሁለተኛ እና ሦስተኛ ላይ ተቀምጠው የሚገኙትን ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ሀዋሳ ከተማን ያገናኘው የከሰዓት ጨዋታ በመደበኛው ደቂቃ መጠናቀቂያ እና ጭማሪ ላይ በተቆጠሩ ሁለት ድንቅ ጎሎች ኢትዮ ኤሌክትሪክን ባለ ድል በማድረግ ፍፃሜን አግኝቷል።

ሀዋሳ ከተማዎች የጨዋታውን የኃይል ሚዛን ወደ ራሳቸው በማድረግ በተጋጣሚያቸው ላይ ብልጫን የማሳየትን አጋጣሚ አግኝተው የነበረ ቢሆንም የኢትዮ ኤሌክትሪክን ጥብቅ የመከላከል አደረጃጀት በቀላሉ አልፎ ኳስ እና መረብን ለማገናኘት ከብዷቸው ተስተውሏል። ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በበኩላቸው የሀዋሳን የጨዋታ ብልጫ በተረጋጋ የመከላከል እና በፈጣን መልሶ ማጥቃት አጨዋወት ለመስበር የጣሩ ቢሆንም አጋማሹ ግን ጎልን ሳያስመለክተን ተገባዷል።

በሁለተኛው አጋማሽ የቀጠለው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከመጀመሪያው አርባ አምስት የሀዋሳ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በአንፃራዊነት ተመጣጣኝ ፉክክርን ያስመለከተን ቢሆንም በመጨረሻዎቹ ሀያ ደቂቃዎች ጫናን የፈጠሩት ኤሌክትሪኮች ስኬታማ ሲሆኑ ተስተውሏል። ሀዋሳ ከተማዎች ተደጋጋሚ ዕድሎችን ፈጥረው መሪ ሊሆኑ የሚችሉባቸውን በርከት ያሉ አጋጣሚዎችን ፈጥረው መታየት ቢችሉም ኳስ እና መረብን ለማገናኘት በእጅጉ መዳከማቸው የኋላ ኋላ ዋጋ ያስከፈላቸው ይመስላል። 68ኛው ደቂቃ ላይ በተደጋጋሚ ከዳኛ ጋር ሰጣ ገባ ውስጥ ስትገባ የነበረችው የሀዋሳዋ አጥቂ ቱሪስት ለማ መስከረም ካንኮን በክርን መማታቷን ተከትሎ በዕለቱ ዳኛ ማርታ መለሰ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዳለች።

አንድ ተጫዋች የጎደለባቸው ሀዋሳዎች ተጋጣሚያቸው የአጥቂ ቁጥርን ከፍ በማድረግ በመጨረሻ ደቂቃ በተጠቀመበት መንገድ ጎሎች አስተናግደው ተሸንፈዋል። 90ኛው ደቂቃ ላይ ህይወት ደንጊሶ መሀል ሜዳ ላይ የተገኘን የቅጣት ምት ወደ ግብ ክልል ስታሻማ ሰላማዊት ጎሳዬ በጥሩ የግንባር አገጫጭ ኳሱን ከመረብ አገናኝታ ቡድኗን መሪ አድርጋለች። መደበኛው የጨዋታ ደቂቃ ተጠናቆ በጭማሪው 90+2 ደቂቃ ላይ ደግሞ በመልሶ ማጥቃት ምንትዋብ ዮሐንስ ወደ ሳጥን ይዛ ገብታ ነፃ ቦታ ላይ ለተገኘችው ትንቢት ሳሙኤል ስትሰጣት አጥቂዋ ሁለተኛ ጎል በማድረግ ጨዋታው በኢትዮ ኤሌክትሪክ 2ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

\"\"

የ12ኛ ሳምንት ቀሪ ጨዋታዎች


ሐሙስ

አዲስ አበባ ከተማ ከ ይርጋጨፌ ቡና 4፡00
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ መቻል 10፡00

ዓርብ

ንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ 4፡00
ልደታ ክፍለ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ 10፡00