ቻን | ዋልያዎቹ በአልጄሪያ ሽንፈት አስተናግደዋል

የአይመን ማይሆስ ብቸኛ ግብ አልጄሪያ ኢትዮጵያን 1-0 በመርታት ወደ ተከታዩ ዙር ማለፏን እንድታረጋግጥ አድርጋለች።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሞዛምቢኩ ጨዋታ የተጠቀመበትን አሰላለፍ ሳይቀይር ነበር የምድቡን ሁለተኛ ጨዋታ ከአልጄሪያ ጋር ለማድረግ ወደ ሜዳ የገባው። ቡድኑ ባደረገው ፈጣን አጀማመር ገና በ2ኛው ደቂቃ በከነዓን ማርክነህ አማካይነት ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርጎ ነበር። ሆኖም 6ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ ሲንቀሳቀስ በነበረው የአጥቂ አማካዩ አህመድ ኩንዶሲ የግብ ሙከራ ምላሽ የሰጡት አልጄሪያዎች የእንቅስቃሴ የበላይነቱን ወስደዋል። ሰሜን አፍሪካዊያኑ የዋልያዎቹን ቅብብሎች ከጅምሩ በማፈን እና በቶሎ ወደ ግብ በመድረስ አደጋ ሲጥሉ ታይተዋል። ከዚህ መሀል 12ኛው ደቂቃ ላይ አብዱርሀማን ሜዛይን በግራ መስመር ሰብሮ በመግባት የሞከረው ኳስ ተጠቃሽ ነበር።

\"\"

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በቅብብሎች በነፃነት ከሜዳው ለመውጣት በተፈተነባቸው ቀጣይ ደቂቃዎች ወደ ራሱ የግብ ክልል ቀርቦ ለመንቀሳቀስ ተገዷል። በአንፃሩ በኳስ ቁጥጥሩም የተሻሉ የሆኑት አልጄሪያዎች በበኩላቸው 22ኛው ደቂቃ ላይ በአህመድ ኩንዶሲ ሌላ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። በቀሪዎቹ የአጋማሾቹ ደቂቃዎች ግን የአልጄሪያዊያኑ አስፈሪነት እየቀንሰ ሲሄድ ታይቷል። ዋልያዎቹም አልፎ አልፎም ቢሆን ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ቀርበው የታዩ ሲሆን በሚፈጥሩት ጫና የአልጄሪያዊያንን ስህተቶች ወደ ዕድልነት ለመቀየር ግን አልቻሉም።

\"\"

ከባድ ሙከራዎች ሳይታይበት የቀጠለው ጨዋታው ወደ ዕረፍት ሊያመራ ሲቃረብ ቸርነት ጉግሳ ከመስዑድ መሐመድ የደረሰውን ኳስ በቀኝ መስመር ገብቶ ያደረገው ሙከራ እንዲሁም አብዱርሀማን ታሀርም ከግራ መስመር ያሻገረው እና ኢትዮጵያዊያኑ ያወጡት ኳስ የተሻለ ትኩረት የሚስቡ አደገኛ እንቅስቃሴዎች ሆነው ታይተዋል።

የሁለተኛው አጋማሽ ቀዳሚ 15 ደቂቃዎች የአልጄሪያ ፍፁም የበላይነት የታየበት ነበር። ቡድኑ ወደ አይመን ማይሆስ በሚያመሩ ኳሶች ሦስት አደገኛ አጋጣሚዎችን ሲፈጥር ተጫዋቹ 52ኛው ደቂቃ ላይ ያገኘውን ዕድል በአግባቡ በመጠቀም አልጄሪያን መሪ አድርጓል። 

\"\"

አልጄሪያዎች በሞካቲር ቤልካቲር አማካይነትም ሌላ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርገዋል። ዋልያዎቹ 57ኛው ደቂቃ ላይ ኪቲካ ጀማ እና ይሀን እንዳሻውን በቸርነት ጉግሳ እና መስዑድ መሐመድ ለውጠው ካስገቡ በኋላ የተፈጠረባቸውን ጫና መቀነስ እና ከሜዳቸው መውጣት ጀምረዋል። በተለይም 69ኛው ደቂቃ ላይ ከነዓን ማርክነህ የተከላካዩ ቾሀቢ ከዳድን ስህተት ለመጠቀም የተቃረበበት ቅፅበት ተጠቃሽ ነበር።

ሆኖም አልጄሪያዊያኑ ተጋጣሚያቸው ሙሉ ለሙሉ የበላይነትን እንዳይወስድ ከማድረግ ባለፈ ከኳስ ጋር ከሜዳቸው በመውጣት ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ሙከራዎችን ማድረጋቸው አልቀረም። በተለይም አብዱርሀማን ሜዛይን ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ በፋሲል ገብረሚካኤል ጥረት የዳነ ነበር። 

\"\"

ጨዋታው ወደ ፍፃሜው ሲቃረብም እንዲሁ የአልጄሪያ ፈጣን ጥቃቶች መታየታቸውን የቀጠሉ ሲሆን ዋልያዎቹም በቅብብሎች ላይ ተመስርተው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ የሚያደርጉት ጥረት ሳይሰምር ቀርቷል። ጭማሪ ደቂቃ ላይ ቡድኑ አቻ ሊሆን የሚችልበትን ዕድል ከማዕዘን ምት በተነሳ እና በተጨራረፈ ኳስ ቢያገኝም ከነዓን ማርክነህ ከቅርብ ርቀት ያደረገው ሙከራ በግብ ጠባቂው ተመልሶ ጨዋታው በአስተናጋጇ ሀገር አሸናፊነት ተቋጭቷል።

የ1-0 ሽንፈት ያስተናገደው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሦስተኛ የምድብ ጨዋታውን የፊታችን ቅዳሜ ከሊቢያ ጋር ያከናውናል።

\"\"