ሪፖርት | ኢትዮጵያ መድን ከ አዳማ ከተማ ነጥብ ተጋርቷል

የ14ኛ ሣምንት የመጀመሪያ ጨዋታ የሆነው የኢትዮጵያ መድን እና የአዳማ ከተማ ጨዋታ 2-2 ተጠናቋል።

10፡00 ላይ የ14ኛ ሣምንት የመጀመሪያ ጨዋታ የሆነው የኢትዮጵያ መድን እና የአዳማ ከተማ ጨዋታ ሲደረግ በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ የጠሩ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል አዳማዎች እጅግ የተሻሉ ነበሩ። ሆኖም ጨዋታውን በተሻለ ስሜት መጀመር የቻሉት ኢትዮጵያ መድኖች በመጀመሪያው ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ሲሞን ፒተር ከኪቲካ ጅማ የተሻገረለትን ኳስ ከሳጥን አጠገብ ወደ ግብ ሞክሮት ግብጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙ ሲመልሰው ኳሱን ነጻ ሆኖ ያገኘው ሀቢብ ከማል በቀላሉ ማስቆጠር ችሏል።

\"\"

አዳማዎች ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በተሻለ የኳስ ቁጥጥር በተለይም ከመስዑድ መሐመድ በሚነሱ ኳሶች ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ሲችሉ 15ኛው ደቂቃ ላይ መስዑድ መሐመድ ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ ላይ ወደግብ ያደረገው ሙከራ የግቡን የቀኝ ቋሚ ገጭቶ ወጥቶበታል። በተረጋጋ የኳስ ቅብብል ፈታኝ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን የቀጠሉት አዳማ ከተማዎች 36ኛው ደቂቃ ላይ አቻ ሆነዋል። ግብጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙ ከራሱ የግብ ክልል ያሻማውን ኳስ ከሁለት ንክኪዎች በኋላ አሜ መሐመድ ከቀኝ መስመር ሲያሻገረው ኳሱን ያገኘው ቦና ዓሊ በሦስት ተከላካዮች መሃል በተረጋጋ አጨራረስ ማስቆጠር ችሏል።

\"\"

ቀስ በቀስ ብልጫ እየተወሰደባቸው የመጡት መድኖች 40ኛው ደቂቃ ላይ ሀቢብ ከማል ከባሲሩ ኦማር በተሻገረለት ኳስ የግብጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ ከፍ አድርጎ ሞክሮት ዒላማውን ሳይጠብቅ ከወጣው ኳስ ውጪ የተሻለ የግብ ዕድል ለመፍጠር እና የአዳማን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለመመከት ሲቸገሩ የአጋማሹ መጠናቀቂያ አምስት ደቂቃዎች ውስጥ በግብ ጠባቂያቸው ድንቅ ብቃት ተጨማሪ ግብ ከማስተናገድ ተርፈዋል። ግብጠባቂው አቡበከር ኑራ በቅድሚያም 40ኛው ደቂቃ ላይ ቦና ዓሊ ከሳጥን ውስጥ በአንድ ደቂቃ ልዩነት ደግሞ አብዲሳ ጀማል ከሜዳው የግራ ክፍል ከሳጥን አጠገብ ያደረጓቸውን ፈታኝ ሙከራዎች ማዳን ሲችል 45ኛው ደቂቃ ላይ በአብዲሳ ጀማል እና በአሜ መሐመድ ከሳጥን ውስጥ የተደረጉ ሙከራዎችም ግብጠባቂውን አልፈው መቆጠር አልቻሉም።

\"\"

እጅግ ማራኪ እና እረፍት የለሽ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን የቀጠሉት የአሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ተጫዋቾች አጋማሹን መርተው ሊወጡ የሚችሉበትን ምቹ አጋጣሚ ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። ሳጥን ውስጥ ከማቀበል አማራጭ ጋር ከግብጠባቂ ጋር የተገናኘው አብዲሳ ጀማል ኃይል ባልነበረው ሙከራ የግብ ዕድሉን አባክኖታል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በመጠኑ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል 50ኛው ደቂቃ ላይ የአዳማው ተከላካይ ሚሊዮን ሰለሞን ሳጥን ውስጥ ሀቢብ ከማል ላይ በሠራው ጥፋት በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ ሲወገድ የተገኘውን የፍጹም ቅጣት ምትም ራሱ ሀቢብ ከማል አስቆጥሮት መድንን በድጋሚ መሪ ማድረግ ችሏል።

\"\"

ያገኟቸውን የግብ ዕድሎች ባለመጠቀማቸው ቁጭት ውስጥ በመግባት በስነልቦና ረገድ እየተዳከሙ የመጡት እና ይባስ ብሎም በተጫዋች ቁጥር ብልጫ የተወሰደባቸው አዳማዎች በአጋማሹ የተሻለውን የመጀመሪያ ሙከራ 63ኛው ደቂቃ ላይ አድርገዋል። መስዑድ መሐመድ ወደኋላ መልሶ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ቦና ዓሊ ከሳጥን አጠገብ ያደረገውን ሙከራ ግብጠባቂው አቡበከር ኑራ መልሶበታል።

ጨዋታውን በማረጋጋት ውጤቱን አስጠብቀው ለመውጣት የፈለጉት የገብረመድኅን ኃይሌ ተጫዋቾች የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ሲገደብ 72ኛው ደቂቃ ላይ ወገኔ ገዛኸኝ ካደረገው ዒላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ውጪ የተሻለ የግብ ዕድል ለመፍጠር ሲቸገሩ ይባስ ብሎም 82ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስተናግደዋል። ተከላካዩ ሀቢብ መሐመድ በግንባሩ ገጭቶ ለግብጠባቂው ያቀበለውን ኳስ አቋርጦ ያገኘው ተቀይሮ የገባው አድናን ረሻድ ማስቆጠር ችሏል።

\"\"

የጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃ ላይም ድራማዊ ክስተት ሊፈጠር ከጫፍ ደርሶ ነበር።በሳጥኑ የቀኝ ከፍል ውስጥ ኳስ ይዞ የገባው የአዳማው ቢንያም ዓይተን ያደረገውን ሙከራ በጨዋታው ኮከብ የነበረው አቡበከር ኑራ መልሶበታል። ጨዋታውም 2-2 ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የኢትዮጵያ መድኑ አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ በመጀመሪያው አጋማሽ ከረጅም ዕረፍት መመለሳቸው የሜዳው አለመመቸት ተጨምሮበት በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ያገኙትን የተጫዋች ቁጥር ብልጫ መውሰድ አመቻላቸው በጨዋታው ጥሩ ቀን እንዳያሳልፉ ምክንያት እንደሆናቸው ሲናገሩ የተጋጣሚያቸውን የአዳማ ከተማ እንቅስቃሴ አድንቀዋል። የአዳማ ከተማው አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ በበኩላቸው ጨዋታውን በመጀመሪያው አጋማሽ መጨረስ ይችሉ እንደነበር ሲናገሩ ተጫዋቾች የመጨረሻው የሜዳ ክፍል ላይ መድረሳቸውን ቢያደንቁም ያገኟቸውን የግብ ዕድሎች ባለመጠቀማቸው ድል እንዳያደርጉ ምክንያት እንደሆናቸው ጠቁመዋል።