ሪፖርት | አዞዎቹ በ12 ደቂቃዎች ውስጥ ባስቆጠሯቸው ጎሎች ለድል በቅተዋል

አርባምንጭ ከተማ ከመመራት ተነስቶ በተቀያሪ ተጫዋቾች ልዩነት ፈጣሪነት ድሬዳዋ ከተማን 3-1 አሸንፏል።

01፡00 ሰዓት ሲል በኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ መሪነት ጨዋታው ጅምሩን አድርጓል። የመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች ረጃጅም ኳሶችን ሲጠቀሙ ሁለቱም ቡድኖች ላይ ያስተዋልን ሲሆን የግብ አጋጣሚዎችን መመልከት የጀመርነውም ገና በጊዜ ነበር።

\"\"

5ኛው ደቂቃ ላይ ሙና በቀለ በረጅሙ የሰጠውን ኳስ አህመድ ሁሴን በሦስት የድሬዳዋ ተከላካዮች መሀል በአግባቡ ተቆጣጥሮ ወደ ግብ ሲመታው ኳሷ አቅጣጫዋን ስታ በላይኛው የግብ ብረት ወጥታለች። በተመሳሳይ የሚሻገሩ ኳሶችን በመጠቀም ፈጠን ያሉ ሽግግሮችን ከተደረገባቸው ሙከራ በኋላ ድሬዎች መሪ የሆኑበትን ግብ 9ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ካዝናቸው አስገብተዋል። ከድሬዳዋ የግብ ክልል በረጅሙ ወደ ግራ የአርባምንጭ ተቃራኒ አቅጣጫ የተጣለን ኳስ አሸናፊ ፊዳ ለመቆጣጠር ሲሞክር ኳስን በእጅ በመንካቱ የተገኘውን የቅጣት ምት ጋዲሳ መብራቴ በግሩም ሁኔታ ከመረብ አሳርፎ ድሬዳዋን መሪ አድርጓል። የመስመር አጥቂው ቡድኑን መሪ ካደረገ ከ8 ደቂቃዎች በኋላ በጉዳት በአብዱለጢፍ መሐመድ ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል።

\"\"

ከመስመር ላይ መነሻቸውን አድርገው ለአህመድ እና ተመስገን ወደ ውስጥ በመጣል ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት አርባምንጭ ከተማዎች 13ኛው ደቂቃ ላይ በዚህ የጨዋታ ሂደት አቡበከር ሻሚል ያደረሰውን የአየር ላይ ኳስ ተመስገን ደረሰ በግንባር ገጭቶ ወጣቱ ግብ ጠባቂ አብዩ ካሳዬ በሚገርም ቅልጥፍና ኳሷን ወደ ውጪ አውጥቷታል። ቀሪዎቹን የጨዋታ ደቂቃዎች በተወሰነ መልኩ ኳስን በራሳቸው እግር ስር በማቆየት የቁጥጥር ድርሻውን የወሰዱት ባለሜዳዎቹ ድሬዳዋ ከተማዎች ሲሆኑ 28ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ዕድልን ፈጥረዋል። እንየው ካሳሁን ከቀኝ ወደ ግብ ክልል አሻግሮ ቻርልስ ሙሴጌ በግንባር ገጭቶ የላይኛው የግቡ የውስጥ ብረት ነክቶ ሲመለስ ግብ ጠባቂው መኮንን መርዶክዮስ በድጋሚ የተመለሰችውን ኳስ በቶሎ ይዟታል። አጋማሹም በድሬዳዋ የ1ለ0 መሪነት ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።

\"\"

ሁለተኛው አጋማሽ የድሬዳዋን መቀዛቀዝ እና የአርባምንጭን የተሻለ የማጥቃት ኃይል ያሳየን ሆኖ ቀጥሏል። ከሚሻገሩ ኳሶች በተጨማሪ መሀል ሜዳ ላይ ኳስን በመቆጣጠር ዕድሎችን ለመፍጠር የአጨዋወት መንገዳቸውን ለወጥ ያደረጉት አዞዎቹ 54ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት እንዳልካቸው ሲያሻማ እንየው ካሳሁን ኳስን ከግብ ክልሉ በአግባቡ ባለ ማፅዳቱ አቡበከር ሻሚል አግኝቷት ከግቡ ትይዩ የደረሰውን አክርሮ ሲመታው ወደ ውጪ በላይኛው የግቡ አግዳሚ ወጥታለች።

\"\"

 የግብ ሙከራ ከተደረገባቸው በኋላ በመልሶ ማጥቃት መልስ ለመስጠት በፍጥነት የተጫወቱት ድሬዳዋዎች በአቤል ከበደ ግልፅ አጋጣሚን ቢያገኙም ኳሷ ወደ ውጪ ወጥታለች። የአጋማሹን አስር ያህል ደቂቃዎች በአርባምንጭ መበለጣቸው የገባችው ድሬዳዋ ከተማዎች አቤል ከበደ እና ሔኖክ ሀሰንን ፣ በቢኒያም ጌታቸው እና ዮሴፍ ዮሐንስ በመተካት የተወሰደባቸውን ብልጫ ለማስተካከል ጥረት ቢያደርጉም ስህተታቸው ግን ሊታረም አልቻለም።

ከመጀመሪያው አጋማሽ በእጅጉ የተሻሻሉት አርባምንጮች ድሬዳዋ ከተማዎች 56ኛው ደቂቃ ላይ በቅቅብል ወቅት የፈጠሩትን ስህተት ተጠቅሞ እንዳልካቸው መስፍን ያገኛትን ኳስ በግምት ከ35 ሜትር ርቀት በቀጥታ አክርሮ ወደ ጎል ሲመታው ግብ ጠባቂው አብዩ ካሳዬ እና የግቡ ቋሚ ብረት ተጋግዘው ኳሷ ወደ ውጪ ልትወጣ ችላለች። ወደ ጨዋታ ቅኝት በደንብ ለመመለስ እና ጎልን አግኝቶ አቻ ለመሆን 69ኛው ደቂቃ ላይ አህመድ ሁሴን እና አቡበከር ሻሚልን ፣ በኤሪክ ካፓይቶ እና መሪሁን መስቀሌ የቀየሩት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ቅያሪያቸው ተሳክቶ ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ግብ አግኝተዋል።

\"\"

በጥሩ የመስመር ቅብብል ሙና በቀለ የደረሰውን ኳስ ከቀኝ ወደ መሀል ሲያሻግር ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው መሪሁን መስቀሌ በአግባቡ በመቆጣጠር ከርቀት አክርሮ በመምታት ኳስ እና መረብን አዋህዶ አዞዎቹን አቻ አድርጓል። አሁንም ትጋታቸውን አርባምንጮች ቀጥለው 78ኛው ደቂቃ መላኩ ኤልያስ በረጅሙ ሲያሻግር ኤሪክ ካፓይቶ የድሬዳዋን ተከላካይ እና ግብ ጠባቂ አብዩ ካሳዬን ስህተት ተጠቅሞ የሰጠውን ተመስገን ደረሰ በግንባር አስቆጥሮታል። ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ከማዕዘን ምት ሱራፌል ሲያሻማ አሸናፊ ፊዳ በግንባሩ ገጭቶ አስቆጥሮ ለአርባምንጭ ሦስተኛ ግብን አክሎ አዞዎቹ ከተመሪነት ወደ መሪነት በማሸጋገር ጨዋታውም 3-1 ተጠናቋል።

\"\"

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች በአስራ ሁለት ደቂቃዎች ውስጥ በተገኙ ሦስት ጎሎች ድል ያስመዘገው አርባምንጭ ከተማ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ከዕረፍት በፊት መበለጣቸውን ጠቅሰው ከዕረፍት በኋላ ግን ባደረጉት ቅያሪ እና መልበሻ ቤት ውጤት ለመቀየር ከተፈለገ አቅማችውን አውጥታችሁ የተቃራኒ ቡድንን ክፍተት ተመልክታችሁ ማጥቃት አለባችው ስለ ተባባልን ተሳክቶልን እግዚአብሔርም ፈቅዶ አሸንፈናል ብለዋል። በቀጣይም ይሄንን እናስቀጥላለን ሲሉ ተደምጠዋል። የድሬዳዋ አቻቸው አሰልጣኝ ዮርዳኖስ አባይ በበኩላቸው መሸነፍ እና ማሸነፍ ያለ ነው ካሉ በኋላ የተሸነፉበት መንገድ እንዳበሳጫቸው እና ከዕረፍት በፊት የነበራቸውን ብልጫ ከዕረፍት በኋላ መረጋጋት ስላልቻሉ አጨዋወታቸውን ባለ መድገማቸው ሊሸነፉ እንደተገደዱ ጠቁመዋል።