መረጃዎች | 56ኛ የጨዋታ ቀን

በነገው ዕለት የሚደረጉ የ14ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰባስበናል።

ሀዋሳ ከተማ ከ ባህር ዳር ከተማ

በሀይቅ የተከበቡትን ሁለቱን ከተሞች የሚወክሉት ሀዋሳ እና ባህር ዳር የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለቻን ውድድር ከመቋረጡ በፊት 13 ጨዋታዎችን አድርገው በቅደም ተከተል 19 እና 25 ነጥቦችን በመያዝ በደረጃ ሰንጠረዡ ስድስተኛ እና ሦስተኛ ቦታን ይዘው ተቀምጠዋል። በነገው ዕለት ማሸነፍም ለሁለቱም ክለቦች ሁለት ደረጃዎችን ሽቅብ እንዲወጡ ስለሚያደርግ ጨዋታው ጥሩ ፉክክር እንደሚደረግበት ይገመታል።

በአሠልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ የሚመራው ሀዋሳ የድሬዳዋ ቆይታውን በሁለት ድል ቢጀምርም ከዛ በኋላ በአራት ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ ሳይችል ቀርቶ በመጥፎ የውጤት ጉዞ ላይ ነበር። በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ግን ራሱን ቀና በማድረግ አራት ነጥብ በማሳካት ወደነበረበት ጠንካራ ብቃት ቢመለስም ሊጉ ተቋርጧል። በውጤትም በእንቅስቃሴም ረገድ ቡድኑ ጥሩ መንገድ እየያዘ የሊጉ መቋረጡ የሚያመጣበት ተፅዕኖም በነገው ጨዋታ ይታያል።

\"\"

በዘንድሮ የውድድር ዓመት ኮስታራ የዋንጫ ተፎካካሪ ሆኖ የቀረበው ባህር ዳር ከተማ ሊጉን የጀመረበት እና ሲቋረጥ የጨረሰበት መንገድ ትንሽ ዝቅ ያለ ሆነእንጂ የሊጉ መሪ በሆነ ነበር። በጠቀስናቸው ወቅቶች ካደረጋቸው የመጀመሪያ እና የመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው አስራ ስምንት ነጥብ አስሩን ጥሏል። አሁን ሊጉ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ እየተሸጋገረ ስለሆነ በተለይ በአንፃራዊነት በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች የተፈጠረውን የውጤት ዝቅታ ለማስተካከል የሊጉ መቋረጥ ምናልባት ሊጠቅመው ይቻላል።

ሀዋሳ ከተማዎች የመጨረሻውን ጨዋታ ከወላይታ ድቻ ጋር ካደረጉ በኋላ ለተጫዋቾቻቸው የ21 ቀናት የዕረፍት ጊዜ ሰጥተው ነው የውድድር አጋማሽ ዝግጅታቸውን በመቀመጫ ከተማቸው የጀመሩት። በዚህ የዝግጅት ጊዜ ከብላክ ስታርስ ክለብ ጋር የልምምድ ጨዋታ አድርገው ነበር። ባህር ዳር ከተማዎች በበኩላቸው የሊጉን የመጨረሻ ጨዋታ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ከውነው የሁለት ሳምንት ዕረፍት በመውሰድ ከጥር 1 ጀምሮ ዝግጅታቸውን እንደ ሀዋሳ በመቀመጫ ከተማቸው አድርገዋል። ቡድኑ የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን እንደ ልቡ ማግኘት ባይችልም በታችኛው የሊግ ውድድር ከሚሳተፈው አውስኮድ ጋር አድርጎ አሸንፏል። ሁለቱ ክለቦች በውድድር አጋማሹ የዝውውር መስኮት አዲስ ተጫዋች ያላስፈረሙ ሲሆን ባህር ዳር በበኩሉ ከአጥቂው ኦሴ ማውሊ ጋር በዲሲፕሊን ምክንያት ተለያይቷል።

ሀዋሳ ከተማ በነገው ጨዋታ እግሩ ላይ የቀዶ ጥገና ያደረገው ብርሀኑ አሻሞ፣ በብሔራዊ ቡድን ግልጋሎት ወቅት ጉዳት የገጠመው ወንድማገኝ ኃይሉ እና ሌላኛው ጉዳት ላይ የሚገኘውን ግብ ጠባቂው ምንተስኖት ጊምቦን አያሰልፍም። ባህር ዳር ከተማ በተቃራኒው ምንም የጉዳት ዜና የሌለበት ሲሆን ረጅም ጊዜ ከሜዳ ርቀው የነበሩት ፍቅረሚካኤል ዓለሙ እና ፋሲል አስማማው ግን ለጨዋታ ዝግጁ ሆነውለታል።

ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ ስድስት ጊዜ ተገናኝተው ሁለቱን በአቻ ውጤት ሲያጠናቅቁ ሀዋሳ ሦስቴ ባህር ዳር ደግሞ አንድ ጊዜ ድል አድርገዋል። በጨዋታዎቹ ሀዋሳ በጨዋታዎቹ በአማካኝ አንድ አንድ ግብ ያስቆጠረበትን የአማካኝ ንፃሬ ሲይዝ ባህር ዳር በበኩሉ በስድስቱ ጨዋታ በድምሩ አምስት ግብ አስቆጥሯል።

ይህንን ጨዋታ ተካልኝ ለማ በመሀል ዳኝነት ሲመሩት አሸብር ታፈሰ እና ሙሉነህ በዳዳ በረዳት ዳኝነት በአምላክ ተሰማ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ከአንጎላ መልስ ለጨዋታው ተመድበዋል።

ፋሲል ከነማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

በዘጠኝ ነጥብ እና በአምስት ደረጃዎች ተበላልጠው አስረኛ እና አስራ አምስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ፋሲል ከነማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪ ደግሞ የዕለቱን የማሳረጊያ ጨዋታ ምሽት 1 ሰዓት ላይ ያከናውናል።

ዓምና በሊጉ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ፋሲል ከነማ ዘንድሮ በብዙ መስፈርቶች የወረደ ብቃት እያሳየ ይገኛል። ክለቡም በ13 ሳምንታት የሊጉ ጨዋታዎች ከአራት በላይ ድል ማስመዝገብ ተስኖት ከመሪው ቦታ ይልቅ ለወራጅ ቀጠናው የተጠጋበትን ነጥብ እና ደረጃ ይዞ ይገኛል። ይህንን መጥፎ ጉዞ ለማሻሻል ክለቡ አንድ ጨዋታ እየቀረው አሠልጣኝ ኃይሉ ነጋሽን ያሰናበተ ሲሆን በእረፍት ጊዜው ደግሞ አሠልጣኝ አሸናፊ በቀለን በመንበሩ ሾሟል። አሠልጣኝ አሸናፊ በሊጉ ካላቸው የካበተ ልምድ መነሻነት ምናልባት ቡድኑን ወደ አዎንታዊ መንገድ ይመልሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

\"\"

አዲስ አዳጊው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በበኩሉ አብሮት ከከፍተኛ ሊግ የመጣውን ለገጣፎ ለገዳዲን በአራተኛ ሳምንት ካሸነፈ በፊትም ሆነ በኋላ በስሙ ምንም ድል የለውም። ይህ የውጤት መጥፋት ገና በስምንተኛ ሳምንት አሠልጣኝ እንዲቀይር አስገድዶታል። ነገርግን ከአሠልጣኝ ለውጥ በኋላም የታየ ምንም የውጤት መሻሻል የለም። ይህንን ተከትሎ በጥር የዝውውር መስኮት ሰባት አዳዲስ ተጫዋቾችን በማምጣት ስብስቡን ለማጠናከር ጥሯል። ምንም እንኳን አዳዲሶቹ ተጫዋቾች እስከ 15ኛ ሳምንት ደረስ ግልጋሎት ባይሰጡም ለሁለተኛው ዙር አጠቃላይ ውድድር ምናልባይ ጥቅም ሊሰጡ ይችላሉ ተብሎ ይታሰባል።

ፋሲል ከነማዎች ከሊጉ መቋረጥ በኋላ 15 ቀናትን ለተጫዋቾቻቸው የዕረፍት ጊዜ ሰጥተው ከጥር 1 ጀምሮ ጎንደር ላይ ከዛም ወደ መዲናው አዲስ አበባ በመምጣት ልምምዳቸውን ከውነዋል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በበኩሉ ብዙም የእረፍት ጊዜ ሳይፈልግ ከታኅሣሥ 23 ጀምሮ መደበኛ ልምምዱን ሲሰራ ሰነባብቷል።

በነገው ጨዋታ ላይ ፋሲል ከነማ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪውን ፍቃዱ ዓለሙ እና ረጅም ወራትን ከሜዳ የራቀው አማካዩን ሀብታሙ ተከስተ ግልጋሎት አያገኝም። በተቃራኒው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በጉዳት የሚያጣው ተጫዋች አይኖርም። ከላይ እንደገለፅነው ግን በዝውውር መስኮቱ ያስፈረማቸውን ሰባቱንም ተጫዋቾች 16ኛው ሳምንት እስኪደርስ ድረስ መገልገል አይችልባቸውም።

ሁለቱ ቡድኖች ለዚህ ቀደም 5 ጊዜ ተገናኝተው 2 ጊዜ ሲሸናነፉ አንድ ጨዋታ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በጎል ረገድ ኤሌክትሪክ 7 ሲያስቆጥር ፋሲል በበኩሉ 5 አስቆጥሯል።
ጨዋታውን የመሐል ዳኛው ተከተል ተሾመ ከአንጎላው የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ ከተመለሱት ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው እና አዲሱ ረዳት ዳኛ ሸረፈዲን አል ፈኪ እንዲሁም ሌላኛው አዲስ ዳኛ ሔኖክ አበበ ጋር በጋራ ይመሩታል።