ሪፖርት | ሲዳማ ቡና ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ተመልሷል

ዛሬ በተደረገው ቀዳሚ ጨዋታ ሲዳማ ቡና ለገጣፎ ለገዳዲን 2-0 በመርታት ከወራጅ ቀጠናው ቀና ያለበትን ውጤት አሳክቷል።

\"\"

በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ሲዳማ ቡናዎች ከፍ ያለ ጫና በማሳደር ብልጫውን ወስደዋል። ቡድኑ ተጋጣሚው አመዛኙን ጊዜ በራሱ ሜዳ ላይ እንዲያሳልፍ በማድረግ በተለይም ድንቅ ሆኖ የዋለው ይገዙ ቦጋለን መድረሻቸው ባደረጉ ኳሶች በተደጋጋሚ ወደ ጎል በመድረስ አደገኛ ሙከራዎችን ማድረግ ችሎ ነበር። ይህ ጫና ለገጣፎዎች ወደ ማጥቃት ሂደት እንዳይገቡ አድርጓቸው የቆየ ሲሆን የመጀመሪያ ሙከራቸውን ለማድረግም 15 ደቂቃዎች ወስደውባቸዋል። በዚህም ካርሎስ ዳምጠው ከቅጣት ምት የተነሳን ኳስ በግንባር ሞክሮ መክብብ ደገፉ አድኖበታል።

ከሁለት ደቂቃ በኋላ ደግሞ ጊት ጋትጉት በተመሳሳይ ከቅጣት ምት በተነሳ ኳስ ኢላማውን በጠበቀ የግንባር ሙከራ ምላሽ ሰጥቷል። ይህ እንቅስቃሴ በማዕዘን ምት ቀጥሎ ፍሬው ሰለሞን ያሻገረውን ኳስ ራቅ ብሎ የጠበቀው ይገዙ ቦጋለ በአግባቡ በመቆጣጠር አክርሮ በመምታት ጎል አድርጎታል።
\"\"

ከግቡ በኋላ ለገጣፎ ለገዳዲዎች በቅብብሎች ከሜዳቸው በመውጣት ጫና ለመፍጠር ሲሞክሩ ታይተዋል። ሆኖም ከኋላ የሚተዉት ክፍተት ለአደጋ ሲጥላቸው ሲታይ 22ኛው ደቂቃ ላይ ቡልቻ ሹራ ከመሀል ባሻገረው ኳስ ሲዳማዎች የመልሶ ማጥቃት ዕድል አግኝተው ሳላዲን ሰዒድ ያደረገው ሙከራ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል።

በተመጣጠነ እንቅስቃሴ በቀጠለው ጨዋታ 30ኛው ደቂቃ ላይ ለገጣፎን አቻ ለማድረግ የቀረበ ክስተት ተፈጥሯል። በዚህም ፍቅሩ ዓለማየሁ በቀኙ የሳጥኑ መግቢያ ላይ ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ ሲመለስ ኦኬይ ጁል በድጋሚ ሞክሮ ወደ ውጪ ወጥቶበታል።

\"\"

እንደአጀማመታቸው ሁሉ ወደ አጋማሹ ማብቂያ ላይ ሲዳማዎች አይለው ታይተዋል። 36ኛው ደቂቃ ላይ ሳላዲን ሰዒድ ወደ ግራ ካደላ ቅጣት ምት በቀጥታ ያደረገው ሙከራ በግቡ ቋሚ ተመልሷል። አንጋፋው አጥቂ በድጋሚ 44ኛው ደቂቃ ላይ ከሙሉዓለም መስፍን የደረሰውን ኳስ ይዞ ሳጥን ውስጥ በግሩም ሁኔታ ተከላካዮችን አልፎ ያደረገው ሙከራ ወደ ውጪ ወጥቷል።

ሁለተኛው አጋማሽ መሪዎቹ ሲዳማዎች ጠንቀቅ ብለው የታዩበት ነበር። ቡድኑ እንደመጀመሪያው አጋማሽ በተለይም ከግራ መስመር የሚሰነዝራቸው ጥቃቶች ቀዝቀዝ ብለው በጨዋታ ቁጥጥር ላይ አመዝኖ ታይቷል። በአንፃሩ ለገጣፎዎች ኳስ መስርተው በመውጣት ረዘም ያሉ ኳሶችን ከመሀል ወደ ፊት ለመጣል ሲጥሩ ይታይ ነበር። ሆኖም ጨዋታው የሚቆራረጡ የማጥቃት ጥረቶች ተበራክተውበት ቀጥሎ 75ኛው ደቂቃ ላይ ሁለተኛ ግብ አስተናግዷል።
\"\"

በሲዳማ ቡና በኩል ጥሩ ሆነው የዋሉት ተጨዋቾች በተሳተፉበት እንቅስቃሴ መሀሪ መና ከግራ ወደ ቀኝ ያሻገረውን ኳስ ይገዙ ቦጋለ በቀኝ የሳጥኑ መግቢያ ላይ በውጪ እግሩ በግሩም ሁኔታ ወደ ውስጥ ሲያሻግርለት ሳላዲን ሰዒድ ጎል አድርጎታል። በቀሪ ደቂቃዎች ለገጣፎዎች ይበልጥ ቀጥተኛ ሆነው የግብ ዕድል ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ ሲዳማዎችም በፈጣን ጥቃቶች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ሙከራቸው ቀጥሎ ጨዋታው በተሻለ የፉክክር መንፈስ ወደ ፍፃሜው ተጉዞ የውጤት ለውጥ ሳይታይበት በሲዳማ ቡና 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

\"\"

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የለገጣፎ ለገዳዲው አሰልጣኝ ዘማሪያም ዝውውሮችን ቢፈፅሙም የሊጉ አስተዳዳሪ ተጫዋቾችን በመጀመሪያው ዙር ለመጠቀም አለመፈቀዱ እንደጎዳቸው አበክረው ገልፀዋል። የሲዳማ ቡናው አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ በበኩላቸው ውጤቱ ያስፈልጋቸው እንደነበር እና የሥራቸው ዋጋ መሆኑን ገልፀዋል። በተጨማሪም ቡድኑ ከዚህ የተሻለ ደረጃ ላይ መገኘት እንደሚገባው በማንሳት በጨዋታው መልካም እንቅስቃሴ ያደረገው ይገዙ ቦጋለን አድንቀዋል።