ሪፖርት | መቻል ሁለተኛውን ዙር በወሳኝ ድል ጀምሯል

127ኛውን የዓደዋ ድል በመዘከር የተጀመረው የሀዲያ ሆሳዕና እና መቻል ጨዋታ ሦስት ግቦች ተቆጥረውበት በመቻል አሸናፊነት ተጠናቋል።

10፡00 ላይ የሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ጨዋታ በሀዲያ ሆሳዕና እና በመቻል መካከል ሲደረግ ነብሮቹ በ 15ኛው ሣምንት በኢትዮጵያ መድን 1ለ0 ሲሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። በዚህም ቃለአብ ውብሸት በሁለት ቢጫ ከሜዳ በተወገደው ፍሬዘር ካሳ ፣ ግርማ በቀለ በ ሳምሶን ጥላሁን ፣ ሰመረ ሐፍታይ በተመስገን ብርሃኑ ተተክተው ጀምረዋል። በ15ኛው ሣምንት ከለገጣፎ የፎርፌ ውጤት ያገኙት መቻሎች በአንጻሩ በ14ኛው ሣምንት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር 3-3 ሲለያዩ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ኢብራሂም ሁሴን ፣ ግሩም ሀጎስ ፣ በረከት ደስታ እና ግርማ ዲሳሳን በዳዊት ማሞ ፣ አሚን ነስሩ ፣ አህመድ ረሺድ እና ሳሙኤል ሳሊሶ ለውጠው በማስገባት ጀምረዋል።

\"\"

127ኛውን የዓድዋ የድል በዓል በማስታወስ እና ባለ ድሎችን በመዘከር ስምንት ያህል ደቂቃዎች ዘግይቶ የጀመረው ጨዋታ ገና በ2ኛው ደቂቃ በሀዲያዎች በኩል ለግብ የቀረበ ሙከራ ተደርጎበታል። ብርሃኑ በቀለ በቀኝ መስመር ከተገኘ የማዕዘን ምት መሬት ለመሬት ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ባዬ ገዛኸኝ ያደረገውን ሙከራ ምንተስኖት አዳነ አስወጥቶበታል።

በነበረው ዝናባማ ሁኔታ የተፈጠረውን የሜዳው መበላሸት ተቋቁመው ድንቅ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የጀመሩት መቻሎች 11ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ግሩም ሀጎስ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው እስራኤል እሸቱ ኳስ በዓየር ላይ እንዳለ ያደረገውን ሙከራ ግብጠባቂው ፔፔ ሰይዶ መልሶበታል። ያንኑ ኳስ ሄኖክ አርፌጮ በረጅሙ መትቶ ለማስወጣት ሲሞክር ግን ከነዓን ማርክነህ ተደርቦ ኳሱን በመመለስ እንዲቆጠር አድርጎታል።

መቻሎች ግብ ካስቆጠሩ በኋላም በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ወደ ተጋጣሚ የግብ ሳጥን ሲደርሱ በአራት ደቂቃዎች ልዩነትም መሪነታቸውን አጠናክረዋል። ግብጠባቂው ዳግም ተፈራ በረጅሙ ያሻማውን እና የሆሳዕናው ተከላካይ ብሩክ ማርቆስ በደንብ ያላራቀውን ኳስ ያገኘው ፍጹም ዓለሙ በግሩም ዕይታ ለበረከት ደስታ ሲያቀብል በረከትም በተረጋጋ አጨራረስ አስቆጥሮታል። መቻሎች የሀዲያን የተከላካይ መስመር አለመረጋጋት በመጠቀም 23ኛው ደቂቃ ላይም በበኃይሉ ግርማ የግቡን የግራ ቋሚ ታክኮ የወጣ ሙከራ ከሳጥን ውጪ ማድረግ ችለው ነበር።

ሆሳዕናዎች ደካማ ሆነው በቀረቡበት የግራ የተከላካይ መስመራቸው የነበረውን አምበሉን ሄኖክ አርፌጮን አስወጥተው ካሌብ በየነን ቀይረው በማስገባት በተሻለ መረጋጋት ተሻሽለው ሲቀጥሉ 37ኛው ደቂቃ ላይም ግብ አስቆጥረዋል። በጥሩ ቅብብል የወሰዱትን ኳስ በመጨረሻም በሳጥኑ የቀኝ ክፍል የነበረው ባዬ ገዛኸኝ ወደ ውስጥ ሲያሻግረው ኳሱን ያገኘው ፀጋዬ ብርሃኑ መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል እጅግ አሳሳቢ በሆነው የመጫወቻ ሜዳ አለመመቸት አቅማቸውን በጨረሱት በሁለቱም ቡድን ተጫዋቾች ቀጣይነት ያለው የኳስ ቅብብል አላስመለከተንም። የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል የተሻሉ የነበሩት መቻሎች ግን 58ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ምቹ አጋጣሚ አግኝተው ነበር። ከነዓን ማርክነህ ከረጅም ርቀት በድንቅ ሁኔታ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው በረከት ደስታ ከማቀበል አማራጭ ጋር ከግብ ጠባቂ ጋር ቢገናኝም እጅግ በወረደ አጨራረስ በኃይል ወደ ውጪ በመላክ ወርቃማውን የግብ ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

በተደጋጋሚ ጊዜ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በቁጥር በዝተው መድረስ የቻሉት መቻሎች 76ኛው ደቂቃ ላይም ሌላ የጠራ የግብ ዕድል ፈጥረው ነበር። ተቀይሮ የገባው ምንይሉ ወንድሙ ወደ ቀኙ የሜዳ ክፍል ካጋደለ ቦታ ላይ ከሳጥን አጠገብ በግሩም ሁኔታ ያሻገረውን ኳስ ዝግጁ ሳይሆን ያገኘው በተመሳሳይ ተቀይሮ የገባው ሳሙኤል ሳሊሶ በሆዱ ገፍቶ ወደ ውጪ አስወጥቶታል።

በጨዋታው እንዳላቸው የኳስ ቁጥጥር የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የተቸገሩት ሀዲያዎች ብርሃኑ በቀለ ከሳጥን ውጪ ካደረገው ፈታኝ ያልሆነ ሙከራ ውጪ በአጋማሹ ተጠቃሽ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል። ጨዋታውም በመቻል የ 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

\"\"

ከጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሀዲያ ሆሳዕናው አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ ጨዋታውን እንደጠበቁት እንዳላገኙት እና የሜዳውን መበላሸት ለሽንፈታቸው እንደ ምክንያት ሲጠቅሱ ተከላካይ ቦታ ላይ ክፍተት እንዳለባቸው ተናግረዋል። አሰልጣኙ አክለውም የመጀመሪያ ዙር ዕቅዳቸው በደረጃ ሠንጠረዡ መኃል ላይ መገኘት እንደነበረ እና ያንንም እንዳሳኩ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል። ድል የቀናቸው የመቻሉ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በበኩላቸው በቡድናቸው ላይ መሻሻል እያዩ እንደሆነ እና ድሉም እንደሚገባቸው ሲናገሩ በሙሉ ደቂቃው የፈጠሩት የግብ ዕድል እንዳስደሰታቸው እና በአቋቋም ስህተት ግብ የሚያስናግዱበትን መንገድም ሊያስካክሉት እንደሚገባ ጠቁመዋል።