መረጃዎች | 68ኛ የጨዋታ ቀን

በ17ኛ ሣምንት የሁለተኛ ቀን መርሐግብር የሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንዲህ አሰናድተናል።

መቻል ከ አዳማ ከተማ

የዕለቱ ቀዳሚ መርሐ-ግብር በአራት ደረጃዎች እና በሁለት ነጥቦች ተበላልጠው 5ኛ እና 10ኛ ደረጃ የተቀመጡት መቻል እና አዳማ ከተማን ሲያገናኝ ከወሳኝ ድል የተመለሱት ሁለቱም ቡድኖች እያሳዩት ያለውን መነቃቃት ለማስቀጥል ውጤቱ እጅግ ከማስፈለጉ አንጻር ከፍተኛ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ውድድሩን ሲጀምሩ ከተጠበቁት በተቃራኒው የውጤት ማሽቆልቆል ውስጥ ገብተው የነበሩት መቻሎች ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ግን በእጅጉ እየተሻሻሉ መጥተዋል። ከመጀመሪያዎቹ 10 ጨዋታዎች በሁለቱ ብቻ ድል ሲቀናቸው ካለፉት አምስት ጨዋታዎች ግን ሦስቱን መርታት ችለዋል። ከውጤታቸው ባሻገር ካስቆጠሯቸው 17 ግቦች 11 የሚሆኑት (64.7 %) የተቆጠሩትም በእነዚህ አምስት ጨዋታዎች መሆኑ የቡድኑን መሻሻል በግልጽ ያስረዳሉ ( ከለገጣፎ ጋር ሊደረግ ታስቦ ፎርፌ የተሰጠበት ጨዋታ የቡድኑን እንቅስቃሴ ለመግለጽ ስለማይረዳን ከቁጥራዊ መረጃዎች ላይ አለማካተታችንን ልብ ይሏል)።

መቻሎች በ16ኛው ሣምንት ሀዲያ ሆሳዕናን 2-1 ሲረቱ በ15 ደቂቃዎች ውስጥ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥሩ ቀሪዎቹን ደቂቃዎች በዝናብ ምክንያት ምቹ ባልሆነው ሜዳ ታክቲካሊ ዲሲፕሊንድ በመሆን የመረጡት ጥንቃቄ የተሞላበት ጨዋታ በነገው ዕለትም ይጠበቃል።

\"\"

ባህርዳር ላይ ካሳዩት እንቅስቃሴ አንጻር ከሚመርጡት አጨዋወት ጋር ሜዳው ምቹ ባልሆነላቸው የድሬዳዋ ሜዳ አራት ተከታታይ ሽንፈቶች አስተናግደው የነበሩት አዳማዎች  በመጨረሻ ካደረጓቸው ሰባት ጨዋታዎች ግን በአራቱ ድል ሲቀናቸው አንዱን ብቻ ተሸንፈዋል። በተለይም ወጣቱ አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ በሥነምግባር እና በወጣቶች የመጫወት ዕድል ላይ ያላቸው የውሳኔ አፈጻጸም ውጤታማ እያደረጋቸው ይገኛል። ዮሴፍ ታረቀኝ! ከሰሞኑ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ባስቆጠራቸው ሦስት ግቦች እና በሚያሳየው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ የብዙዎችን ትኩረት የሳበው ከአዳማ ተስፋ ቡድን የተገኘው አጥቂ ለብሔራዊ ቡድን የተደረገለትን ጥሪ ተከትሎም በከፍተኛ መነሳሳት በነገው ጨዋታም ለመቻሎች ፈተና ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

በመቻል በኩል ልምምድ ላይ ጉዳት ያጋጠመው ግብጠባቂው ዳግም ተፈራ ጨዋታው የሚያመልጠው ሲሆን አዳማ ከተማዎች በስነምግባር ችግር ከስብስቡ የተነጠሉትን ሦስት ተጫዋቾች ጨምሮ ጉዳት ያስተናገደውን አማኑኤል ጎበናን በነገው ጨዋታ አይጠቀሙም።

የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ በአዳማ 2-0 አሸናፊነት መጠናቀቁ ሲታወስ በአጠቃላይ ከዚህ ቀደም በሊጉ ለሰላሳ(30) ያህል ጊዜያት በተገናኙባቸው ጨዋታዎች አሥራ ሦስቱ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ መቻል ለስምንት አዳማ ደግሞ ለዘጠኝ ጊዜያት ድል አድርገዋል።

ጨዋታውን ኤፍሬም ደበሌ በዋና ዳኝነት ፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ይበቃል ደሳለኝ እና አማን ሞላ በረዳት ዳኝነት ሔኖክ አክሊሉ በአራተኛ ዳኝነት እንደሚመሩት ይጠበቃል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

በ 35 ነጥቦች የሊጉ አናት ላይ የተቀመጡት ቅዱስ ጊዮርጊሶችን በ 8 ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኙት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የሚያገናኘው የምሽቱ ፍልሚያ ፈረሰኞች መሪነታቸውን ለማጠናከር ኤሌክትሪኮች ደግሞ ካሉበት የወራጅ ቀጠና ለማንሠራራት ጥሩ ፉክክር ያደርጉበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ባለፈው ሣምንት ተከታያቸው ኢትዮጵያ መድንን ከመመራት ተነስተው ድል ያደረጉት ፈረሰኞች ከፍተኛ ፉክክር ይገጥማቸዋል ተብሎ በተጠበቀው ጨዋታ ያሳኩት ጣፋጭ ድል ለቀጣይም ትልቅ መነሳሳት እንደሚፈጠርላቸው ይገመታል። ውድድሩ ለብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ከመቋረጡ በፊትም የመሪነት ደረጃቸው ላይ ተደላድለው ለመቀመጥ ለጨዋታው ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጡት ይሆናል። ሊጉ ላይ ዝቅተኛውን ግብ(10) ማስተናገዳቸው እንደ ጥሩ ጎን ቢታይም አልፎ አልፎ የራሳቸው የሜዳ ክፍል ላይ በውሳኔ እና በጊዜ አጠባበቅ ስህተት የሚታይባቸውን ድክመት በጊዜ ሊቀርፉት ይገባል።

\"\"

በሜዳ ላይ ከሚያሳዩት ጠንካራ እንቅስቃሴ አንጻር የድል ፅዋን ለመጎንጨት የተራራ ያህል የከበዳቸው ኤሌክትሪኮች በተለይም ባለፈው ሣምንት ባህርዳር ከተማን ሲመሩ ቆይተው ወሳኝ ተጫዋቻቸውን አብነት ደምሴን በሁለት ቢጫ ካጡ በኋላ የተፈጠረባቸውን የተጫዋች ቁጥር ብልጫ መቆጣጠር ባለመቻላቸው ለሽንፈት ተዳርገዋል። የቡድኑ ሚዛን ጠባቂ አብነት ደምሴ በቅጣት ምክንያት ነገም አለመሰለፉ ደግሞ ትልቅ ፈተና እንደሚሆንባቸው ሲጠበቅ ከለገጣፎ ለገዳዲ (38) እና ሲዳማ ቡና(28) ቀጥሎ ሦስተኛው ከፍተኛ የግብ መጠን(26) ያስተናገዱ በመሆናቸው በኢስማኤል ኦሮ-አጎሮ የሚመራውን የፈረሰኞቹን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለመመከት የተለየ የጨዋታ ስልት ይዘው ወደሜዳ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ምኞት ደበበ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል በጉዳት የማይኖሩ ሲሆን ኤሌክትሪኮች በበኩላቸው ከላይ እንደተጠቀሰው አብነት ደምሴን በሁለት ቢጫ ካርድ ፀጋ ደርቤን ደግሞ በጉዳት የሚያጡ ይሆናል።

በመጀመሪያው ዙር በተገናኙበት ጨዋታ ጊዮርጊሶች በፍሪምፖንግ ሜንሱ የመጨረሻ ደቂቃ ግብ ማሸነፋቸው የሚታወስ ሲሆን በአጠቃላይም ሁለቱ ቡድኖች 39 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 27 በማሸነፍ  የበላይነትን ሲይዝ ኤሌክትሪክ 3 አሸንፎ በ9 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ 66 ግቦች ሲያስቆጥር ኤሌክትሪክ በበኩሉ 28 አስቆጥሯል።

የምሽቱን ጨዋታ ሃይማኖት አዳነ ከከፍተኛ ሊጉ በማደግ ለመጀመሪያ ጊዜ የፕሪምየር ሊጉን ጨዋታ ሲመራ ፣ ወጋየሁ አየለ እና  ሻረው ጌታቸው በረዳት ዳኝነት ፣ ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ በአራተኛ ዳኝነት ይመሩታል ተብሎ ይጠበቃል።