ሪፖርት | ባህር ዳር ከተማ ከመሪው ጋር ያለውን ልዩነት አጥብቧል

የጣና ሞገዶቹ ወልቂጤ ከተማን 4-0 በማሸነፍ በደረጃ ሰንጠረዡ በግብ ክፍያ በልጠው ሁለተኛ ላይ የተቀመጡበትን ውጤት አስመዝግበዋል።

\"\"

የጨዋታው የመጀመሪያዎቹ 15 ያህል ደቂቃዎች ከእንቅስቃሴዎች ውጪ ሁለቱ ቡድኖች መሀል ሜዳ ላይ አመዛኙን ጊዜያቸውን ማሳለፋቸው ሙከራዎችን በጊዜ እንዳናይ ዕክል ሆኖብን ተስተውሏል። ባህር ዳር ከተማዎች በቅብብል ወደ ፊት በመሄድ ከዛም ከመስመር በሚሻገሩ ኳሶች ግቦችን ለማግኘት ወልቂጤዎች በበኩላቸው ከኋላ ክፍላቸው ኳስን በመመስረት አልያም ከባህርዳር የሚቋረጡ ኳሶችን ሲያገኙ ፈጠን ባለ ሽግግር ሲጫወቱ ብንመለከትም የጠሩ ዕድሎችን ለመመልከት ግን ደቂቃዎችን ማጋመስ ግድ ብሎናል። ባህር ዳርን ጫና ውስጥ ለመክተት የሚመስል እንቅስቃሴ ያደረጉት ወልቂጤዎች 18ኛው ደቂቃ ላይ በፈጣን መልሶ ማጥቃት የኋላሸት ሰለሞን ወደ ሳጥን እየገፋ ገብቶ ለጌታነህ ሰጥቶት አጥቂው መልሶ ለየኋላሸት አቀብሎት ተጫዋቹ ወደ ጎል አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው ታፔ አልዛየር ሲመልስ አቤል ነጋሽ በድጋሚ ወደ ጎል ሲመታት አይቮሪያኑ ግብ ጠባቂ በሚገርም ብቃት አሁንም ኳሷን አውጥቷል።

\"\"

ወደ ወልቂጤ የግብ ክልል ከጅምሩ መድረስ ቢችሉም ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ለማድረግ ተቸግረው የነበሩት ባህር ዳሮች 27ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር በኩል ፉዓድ ፈረጃ ከቅጣት ምት ወደ ጎል መቶ ጀማል በእግሩ ሲመልሳት ከጎሉ ትይዩ የነበረው ሀብታሙ በቀላሉ አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ ጀማል ባዳነበት አጋጣሚ በይበልጥ መንቃት ጀምረዋል። ከአራት ደቂቃዎች መልስም ከመስመር እና ከቆመ ኳስ ጎልን ለማግኘት የታተሩት የጣና ሞገደኞቹ ከቅጣት ምት ፍራኦል መንግሥቱ አሻምቶ ያሬድ ባየህ በግንባር ገጭቶ ባስቆጠራት ግብ ቀዳሚ ሆነዋል።

\"\"

ጎልን ማግኘታቸው ይበልጥ ያነቃቸው ባህር ዳሮች 43ኛው ደቂቃ ላይ ከሀብታሙ ታደሰ ያገኘውን ኳስ በግምት ከ30 ሜትር ርቀት አለልኝ አዘነ አክርሮ በመምታት የጀማል ጣሰው የአቋቋም ስህተት ታክሎበት ሁለተኛ ግብን ከመረብ አገናኝቶ ጨዋታው 2-0 ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።

ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ ባህርዳር ከተማዎች ጨዋታውን ወደ ራሳቸው በማድረግ በኳስ ቁጥጥርም ሆነ በሙከራ ረገድ ፍፁም ብልጫን ወስደዋል። የተጫዋች ለውጥን ካደረጉ በኋላ በተወሰነ ረገድ የአጋማሹ አጀማመራቸው ወልቂጤዎች ሻል ያለ መልክ ነበረው። ለዚህም በጌታነህ ከበደ እና አቤል ነጋሽ ያደረጉት ተከታይ ሙከራዎች ማሳያ ቢሆኑም የመከላከል ድክመታቸው በቅብብል በመስመር በኩል የሰላ ጥቃት ለሚሰነዝሩት ባህርዳሮች በእጅጉ ምቹነት የፈጠረላቸው ሆኗል። 65ኛው ደቂቃ ከእጅ ውርወራ መሳይ አገኘው በቀኝ በኩል የሰጠውን አብስራ ተስፋዬ በሁለት ንክኪ ወደ ጎል ሲያሻማ ሀብታሙ ታደሰ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር የቀድሞው ቡድኑ ላይ ሦስተኛውን ግብ ከመረብ አዋህዷል። የመከላከል አደረጃጀታቸው ደካማ የነበረው ወልቂጤዎች ከሁለት ደቂቃ ቆይታ መልስም ጎል አስተናግደዋል።

በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ሳጥን ውስጥ የደረሰችን ኳስ መሳይ አገኘው ወደ ውስጥ ሲያሻግር ፉዓድ ፈረጃ አራተኛ ጎል አድርጓታል።

\"\"

ከደቂቃዎች በኋላ አደም አባስ ሌላ አጋጣሚን አግኝቶ በጀማል ጣሰው ከሽፎበታል። የመጨረሻውን አስር ደቂቃዎች ወደ ቀኝ የሜዳው ክፍል በየኋላሸት ሰለሞን አማካኝነት ይበልጡኑ ጥቃቶችን ወልቂጤዎች መሰንዘር ቢችሉም የታፔ አልዛየርን መረብ መድፈር ባለ መቻላቸው ጨዋታው 4-0 የባህርዳር ድል አድራጊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ከደመወዝ ጥያቄ ጋር በተገናኘ የሁለት ቀናት ልምምድን ብቻ ሰርተው የቀረቡት ወልቂጤ ከተማ አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ቡድናቸው የዛሬው አለመሆኑን ጠቅሰው ከልምምድ ጋር በተያያዘ በቂ ዝግጅትን ሳያደርጉ በመቅረታቸው በሰሩት መጠን ውጤት እንዳገኙ ጨዋታውም የወረደ እንደነበር ነገር ግን በተቻለ መጠን ተጫዋቾቻቸው ያላቸውን አድርገው እንደወጡ በሚቀጥለውም ለማሻሻል እንደሚሰሩ ገልፀዋል።

\"\"

የባህር ዳር አቻቸው ደግአረገ ይግዛው በበኩላቸው በመጀመሪያው አስራ አምስት ኦና ሀያ ደቂቃ ከተጋጣሚያቸው ጠንካራ ፉክክር እንዳስተናገዱ ጠቁመው በሒደት ግን የተሻለ ነገር በተለይ ከመጀመሪያው በሁለተኛው አጋማሽ ምቾት ተሰምቷቸው በመጫወታቸው ውጤት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

\"\"