ሪፖርት | ሀዋሳ አዳማን በመርታት ደረጃውን አሻሽሏል

የዕለቱ ቀዳሚ የነበረው የሀዋሳ ከተማ እና አዳማ ከተማ ጨዋታ በሁለቱ አጋማሾች የተቆጠሩ ጎሎች ኃይቆቹን የ2-0 አሸናፊ አድርጎ ተጠናቋል።

\"\"

አዳማ ከተማ መቻልን ከረታው ስብስቡ ፍሬድሪክ ሀንሳን በአማኑኤል ጎበና ፣ አቡበከር ወንድሙን በቢኒያም አይተን ሲለውጡ ሀዋሳዎች ድሬዳዋ ላይ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ውድድሩ ከመቋረጡ በፊት አድርገው ስለነበር የዛሬው ጨዋታ የአዳማ ቆይታቸው የመጀመሪያቸው መርሀግብራቸው ሆኗል።

ቀዝቀዝ ባለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴዎች ጅምሩን ያደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የኋልዮሽ ቅብብሎች የበዙበትን አጋማሽ ያሳየን ነበር ማለት ይቻላል። ባለ ሜዳው አዳማ ከተማ ኳስን ከተከላካይ መስመራቸው በመጀመር በሁለቱ መስመሮች በኩል በተለይ ጀሚል ያዕቆብ በተሰለፈበት የቀኝ የሜዳው ክፍል ለመሰንዘር ሀዋሳዎች በበኩላቸው ጥንቃቄ አዘል የጨዋታ መንገድን መርጠው ነገር ግን ኳስን በሚያገኙበት ወቅት በፈጣን መልሶ ማጥቃት ዓሊ እና ኤፍሬምን ተጠቅመው ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረዋል።

 ኤፍሬም አሻሞ ለሙጂብ አቀብሎት አጥቂው ወደ ሳጥን አሻግሮ አብዱልቢሲጥ ለጥቂት በሰይድ ሀብታሙ በተያዘበት ኳስ ሀዋሳ ከተማ የመጀመሪያ ሙከራን ማድረግ ጀምረዋል። የጨዋታ አጠቃቀማቸውን መልሶ ማጥቃት ላይ ትኩረት ያደረጉት ኃይቆቹ ኤፍሬም አሻሞ ከዓሊ ሱለይማን በረጅሙ የደረሰችውን ኳስ ወደ ጎል አክርሮ መትቶ የላይኛው የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ሌላኛው የቡድኑ ሙከራ ሆናለች።

አዳማ ከተማዎች መነሻቸውን በአመዛኙ መሀል ሜዳ ላይ ካደረጉ በኋላ በይበልጥ በኮሪደር በኩል አጋጣሚዎችን ለማግኘት ታትረዋል በዚህም 12ኛው ደቂቃ ላይ ቦና ዓሊ ከግራ የሀዋሳ የግብ አቅጣጫ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ሳጥን ውስጥ ሰብሮ ገብቶ በግራ እግሩ አክርሮ የመታት ኳስ መድሀኔ ብርሀኔ ከግቡ አፋፍ ላይ ያወጣት ኳስ ምናልባትም አዳማን ቀዳሚ ልታደርግ የምትችል ዕድል ነበረች። በሌላ ሙከራቸው ጀሚል ያዕቆብ ከቀኝ ወደ ግራ መሬት ለመሬት የላካትን ኳስ ቢኒያም አይተን መጠቀም ሳይችል ከቀረበት ክስተት መልስ ግን አዳማዎች ጎል አስተናግደዋል። 29ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ኤፍሬም አሻሞ ለዓሊ በፍጥነት ሰጥቶት ኤርትራዊው ተጫዋች ወደ ውስጥ የላካት ኳስ በአብዱልባሲጥ ከማል ተቆጥራ ሀዋሳ መሪ ሆኗል። በይዘቱም ደብዛዛ መልክ የነበረው አጋማሽ ተገባዷል።

ሁለተኛውን አጋማሽን አዳማዎች የተጫዋች ለውጥ በማድረግ ነበር ጨዋታቸውን የጀመሩት አሜ መሐመድ እና መስዑድ መሐመድን በአማኑኤል ጎበና እና አድናን ረሻድ ተክተው ወደ ሜዳ በማስገባት ፈጥን ባለ የሽግግር እንቅስቃሴ ለመጫወት ጥረትን በጀመሩበት ቅፅበት ሁለተኛ ጎልን ሊያስተናግዱ ተገደዋል። 51ኛው ደቂቃ ላይ በግራ የአዳማ ሳጥን ጠርዝ ዳንኤል ደምሱ በመድሀኔ ብርሀኔ ላይ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ የተሰጠውን የቅጣት ምት ዓሊ ሱለይማን አሻምቶ አቤኔዘር ኦቴ በግንባር ገጭቶ ከመረብ አገናኝቷታል። 

ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ መሐል ሜዳውን ዘርዘር ባለ የቅብብል ሒደቶች እና በመስመሮች በኩል ለመጫወት የዳዱት አዳማዎች ግብ ካስተናገዱ ከአንድ ደቂቃ በኋላ ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። ጀሚል ወደ ሳጥን አሻግሮ ዳዊት ታደሰ በእጅ መንካቱን ተከትሎ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ደስታ ዮሐንስ ሲመታው መሐመድ ሙንታሪ ነበር ማምከን የቻለው።

የመስዑድ ወደ ሜዳ መግባት ይበልጥ ያበረታቸው እና የጀሚልን ፍጥነት ለመጠቀም በድግግሞሽ ጥረቶች ያልተለያቸው አዳማ ከተማዎች በመስዑድ ፣ ደስታ እና ዮሴፍ ያለቀላቸውን ዕድሎች አግኝተው ነበር። በተለይ መስዑድ ግብ አስቆጥሮ የተሻረበት እና ዮሴፍ በአግባቡ የተቆጣጠራትን ኳስ ወደ ጎል መትቶ ጥሩ ሆኖ የዋለው መሐመድ ሙንታሪ የያዘበት የቡድኑን ሁነኛ ጥቃቶች ነበሩ። አጋማሹን ያስቆጠሩትን ጎል አስጠብቆ መውጣት ላይ ያተኮረ እንቅስቃሴ ላይ የተጠመዱት ሀዋሳዎች ተሳክቶላቸው ጨዋታውን 2-0 በማሸነፍ በደረጃ ሰንጠረዡ አራተኛ ላይ የተቀመጡበትን ውጤት አስመዝግበዋል።

\"\"


የአዳማ ከተማው አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ሀዋሳን እንደጠበቁት እንዳገኙት እና ከመሐል እና ከተሻጋሪ ኳስ የሚመጡ ኳሶቻቸውን መከላከል እንዳልቻሉ ጠቁመው ለማስከፈት ያደረጉት ጥረት ደካማ በመሆን ውጤት ሳይዙ መቅረታቸውን ገልፀዋል። ሦስት ነጥብን ያገኘው ሀዋሳ ከተማ አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በበኩላቸው በዓሊ ሱለይማን እንቅስቃሴ በደንብ ተጠቅመው እንደቻሉ እና ከዕረፍት በፊት ጥሩ እንደነበሩ ከዕረፍት በኋላ ግን ውጤቱን አስጠብቆ ለመውጣት በማቀዳቸው ድክመት ቢታይባቸውም አሸንፈው መውጣታቸውን ተናግረዋል።