ድሬዳዋ ከተማ አሠልጣኝ ለመሾም ከጫፍ ደርሷል

ከአሠልጣኝ ዮርዳኖስ ዓባይ ጋር የተለያየው ድሬዳዋ ከተማ አሠልጣኝ ለመሾም ከጫፍ መድረሱን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

የዘንድሮ የውድድር ዓመት ከመጀመሩ በፊት አሠልጣኝ ዮርዳኖስ ዓባይን የቀጠረው ድሬዳዋ ከተማ በ17 ሳምንታት የሊጉ ጉዞ 21 ነጥቦችን በመሰብሰብ በደረጃ ሰንጠረዡ 11ኛ ቦታ ላይ መቀመጡ ይታወቃል። ከወራጅ ቀጠናው በአንድ ነጥብ ብቻ ከፍ ያለው ቡድኑ ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች አንዱን ብቻ ማሸነፉን ተከትሎም ከዮርዳኖስ ዓባይ ጋር ለመለያየት ወስኗል።
\"\"
የክለቡ ኃላፊዎች በቦታው አዲስ አሠልጣኝ ለማምጣት ሦስት አሠልጣኞችን በእጩነት በመያዝ ሲመካከሩ ከቆየ በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምክትል አሠልጣኝ የሆነውን አስራት አባተን ለመሾም የመጨረሻው ደረጃ ላይ እንደደረሱ ድረ-ገፃችን አረጋግጣለች።

ክለቡ ከአሠልጣኝ አስራት ጋር ንግግሮችን አድርጎ ስምምነት ላይ የደረሰ ሲሆን አሠልጣኙ አሁን ግልጋሎት እየሰጠበት ካለው የብሔራዊ ቡድን ኃላፊነት ለመነሳት በትናንትናው ዕለት የመልቀቂያ ደብዳቤ እንዳስገባም ታውቋል። ቀጣሪው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የአሠልጣኙን ጥያቄ በቶሎ የሚመልስ ከሆነም ነገ የወረቀት ስራዎች ተገባደው በይፋ የቡድኑ አሠልጣኝ እንደሚሆን ይጠበቃል።
\"\"
በሁለቱም ፆታዎች ያሰለጠነው አስራት ከ17 እና ከ20 አመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድኖችን በአሠልጣኝነት ለዓለም ዋንጫ ጫፍ አድርሰው ነበር። ያለፉትን 31 ወራት ደግሞ በዋልያዎቹ የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ረዳት ሆነው ሲያገለግሉ ነበር።