መረጃዎች | 77ኛ የጨዋታ ቀን

የጨዋታ ሳምንቱ የሁለተኛ ቀን ሁለት መርሐ-ግብሮችን የተመለከቱ መረጃዎች አሰባስበናል።

ድሬዳዋ ከተማ ከባህር ዳር ከተማ

ከጣፋጭ ድል ማግስት እርስ በእርስ የሚገናኙት ድሬዳዋ እና ባህር ዳር በቅደም ተከተል ከሚገኙበት የወራጅነት ስጋት እና የዋንጫ ፉክክር ዓላማ መነሻነት ጥሩ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በሳምንቱ መጀመሪያ አዲስ አሠልጣኝ የሾሙት ድሬዳዋ ከተማዎች ምንም እንኳን በአሠልጣኙ ሜዳ ላይ ባይመሩም ከአንድ ጨዋታ በኋላ ከድል ጋር የተገናኙበትን ውጤት አግኝተዋል። ሦስት ነጥቡ እና ከመመራት ተነስቶ ድሉን ያሳኩበት መንገድ ደግሞ ለቡድኑ አባላት ትልቅ የራስ መተማመን የሚሰጥ ሲሆን በነገው ጨዋታም ማሸነፉ ያመጣው ትሩፋት ይታያል ተብሎ ይጠበቃል። በተለይ በብዙ ቡድኖች የሚታየው የአዲስ አሰልጣኝ ሹመት መነቃቃትም ምናልባት ካገዛቸው ለባህር ዳር ከተማ ጨዋታውን ሊያከብድበት ይችላል።
\"\"
ከሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሦስት ነጥቦች ብቻ አንሰው ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ባህር ዳር ከተማዎች በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ ይገኛሉ። ሽንፈት ካስተናገደ ስድስት የጨዋታ ሳምንታት ያለፈው ቡድኑም በፈታኙ የፋሲሉ ጨዋታ ያሳካው ሦስት ነጥብ በትክክል ኮስታራ የዋንጫ ተፎካካሪ እንደሆነ ያስመሰከረ ነበር። ከሌላኛው የዋንጫ ተፎካካሪ ኢትዮጵያ መድን ጋር ከሚያደርጉት ወሳኝ ጨዋታ በፊት ደግሞ በታችኛው ፉክክር ውስጥ የሚገኙትን ሁለት ክለቦች በተከታታይ አሸንፈው በተሻለ ቁመና ላይ ተገኝቶ ለፍልሚያው መቅረብን ያስባሉ ተብሎ ይገመታል።

ድሬዳዋ ከተማ ባሳለፍነው ሳምንት ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ሲጫወት ጉዳት ያስተናገዱት አሰጋኸኝ ጴጥሮስ እና ኤሊያስ አህመድ ማገገማቸው ሲታወቅ ሙኸዲን ሙሳ እና ያሬድ ታደሰ ግን ለነገው ጨዋታ እንደማይደርሱ ተገልጿል። በባህር ዳር ከተማ በኩል ግን ምንም የጉዳት እና የቅጣት ዜና የለም።

የሰባት ጨዋታዎች ግንኙነት ያላቸው ቡድኖቹ ሦስት ጊዜ ነጥብ ሲጋሩ በድምሩ አስራ ሁለት ግቦችን ያስቆጠሩ ሲሆን ሦስት ድሎችን ያስመዘገቡት ባህር ዳሮች ሰባት እንዲሁም አንድ ጊዜ ያሸነፉት ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ አምስት ግቦችን አስመዝግበዋል።

በጨዋታው ዳንኤል ግርማይ በመሀል ዳኝነት ኢንተርናሽናል ዳኛ ትግል ግዛው እና ሰብስቤ ጥላሁን ረዳቶች ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ በበኩሉ አራተኛ ዳኛ ሆኖ ተመድቧል።

ሀዲያ ሆሳዕና ከአርባምንጭ ከተማ

በአምስት ደረጃዎች እና ሦስት ነጥቦች ተለያይተው የሚገኙት ሀዲያ እና አርባምንጭ በሊጉ ደረጃ ሰንጠረዥ እድገት ለማምጣት እና ወደ አስተማማኝ ቦታ ለመሸጋገር ብርቱ ትግል እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

በመጀመሪያዎቹ የሊጉ ጨዋታዎች በዋንጫ ፉክክር ውስጥ የነበረው ሀዲያ ሆሳዕና ከሳምንት ሳምንት እየወረደ ይገኛል። ባለፉት ስምንት ጨዋታዎችም አንድ ድል ብቻ በማሳካት ማግኘት ከሚገባው ሀያ አራት ነጥቦች ስድስቱን ብቻ አሳክቷል። ቡድኑ ከውጤት ባለፈም ከነበረበት ጠንካራ ብቃት እየወረደ መምጣቱ ደጋፊዎችን እያሳሰበ የሚገኝ ሲሆን በቶሎ አገግሞ እስከ 5ኛ ደረጃ የሚያሳድገውን ውጤት ለማግኘት ወደ ሜዳ ይገባል ተብሎ ይገመታል። ካልሆነ ግን ከስሩ የሚገኙት ቡድኖች ካሸነፉ በአንዴ ወደ ታችኛው ደረጃ ዝቅ ሊል ስለሚችል ለጨዋታው ትኩረት ሰጥቶ ይገባል።
\"\"
በወጥነት ወጥ ብቃት እና ውጤት ማስመልከት ያልቻለው አርባምንጭ ከተማ ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ሦስት ነጥብ አሳክቷል። በተለይ ቡድኑ ከመመራት ተነስቶ ጣፋጭ ድል መቀዳጀቱ ለነገው ጨዋታ ስንቅ ሊሆነው ይችላል። ይህ ቢሆንም ግን ለወትሮ በመከላከሉ ረገድ ጠጣር የነበረው ስብስቡ ያለፉትን ዘጠኝ ጨዋታዎች ግቡን ማስጠበቅ ሳይችል በድምሩ 15 ግቦችን አስተናግዷል። ይህ የኋላ ችግር ከተስተካከለ ግን የፊት መስመሩ በጥሩ ስለት ላይ ስለሚገኝ ውጤት መያዙ የማይቀር ነው።

ቡድኖቹ በሊጉ ከተገናኙባቸው አምስት ጨዋታዎች አራቱ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ አርባምንጭ ከተማ አንድ ጊዜ ድል አድርጓል። በጨዋታዎቹ ነብሮቹ ስድስት አዞዎቹ ደግሞ ሰባት ግቦችን አስቆጥረዋል።

ተከተል ተሾመ ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት ሲመራው ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ተመስገን ሳሙኤል እና ሀብተወልድ ካሳ በረዳትነት ባህሩ ተካ በአንፃሩ አራተኛ ዳኛ ሆነው ተሳትፎ ያደርጋሉ።