ሪፖርት| የጣና ሞገዶቹ የዋንጫ ተፎካካሪነታቸውን ያስቀጠሉበት ድል አስመዘገቡ

በ19ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን የመጀመርያ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማን የገጠመው ባህር ዳር ከተማ ነጥቡን ከመሪው ያስተካከለበትን ድል አስመዝግቧል።

ባህር ዳሮች ባለፈው ሳምንት ፋሲል ከነማን ካሸነፈው ስብስብ ፍፁም ጥላሁን በአደም አባስ ተክተው ሲገቡ ብርቱካናማዎቹም ያሬድ ታደሰን በአቤል አሰበ ለውጠው ጨዋታውን ጀምረዋል።

\"\"

በእንቅስቃሴ ደረጃ ተመጣጣኝ ፉክክር የታየበት እና ባህርዳር ከተማዎች በርካታ የግብ ዕድሎች በፈጠሩበት  ጨዋታ ባህርዳር ከተማዎች በዋንጫ ፉክክሩ ምን ያህል ጉዞ መጓዝ እንደሚችሉ ያሳዩበት ነበር።

በአጋማሹ ጥራት ያላቸው የግብ ዕድሎች የፈጠሩት ባህርዳሮች ጫና በፈጠሩባቸው ደቂቃዎች በርካታ ሙከራዎች አድርገዋል። ከነዚህም ያብስራ ተስፋዬ ተከላካዮች አልፎ መቶት ዓብዱለጢፍ መሓመድ የመለሰው ኳስ እና ፈቱዲን ጀማል ከመዐዝን ያደረገው ሙከራ ይጠቀሳሉ።

በመጀመርያዎቹ  ደቂቃዎች ሦስት የግብ ዕድሎች የፈጠሩት የጣና ሞገዶቹ በአስራ አምስተኛው ደቂቃ ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ በሀብታሙ ታደሰ አማካኝነት ግብ አስቆጥረዋል። አጥቂው ከፍራኦል መንግሥቱ በግሩም መንገድ የተሻገረለትን ኳስ በመጠቀምም ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።

ባህርዳሮች ከግቧ በኃላም በፉዐድ አማካኝነት ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ቢችሉም ፍሬው እንደምንም አውጥቷታል።

ከእንቅሳሴ ባለፈ በርካታ ግብ ዕድሎች መፍጠር ያልቻሉት ብርቱካናማዎቹ የፈጠሯቸው ሁለት ዕድሎች ግን እጅግ ለግብ የቀረቡ ነበሩ። በተለይም ዓብዱለጢፍ ከመስመር አሻግሮት ቢንያም በግንባሩ ገጭቶ ታፔ በምያስደን ብቃት ያወጣት ኳስ እጅግ ለግብ የቀረበች ነበረች።

የመጀመርያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩትም ያብስራ ፣ ዱሬሳ እና ሀብታሙ በጥሩ መናበብ የፈጠሩት ዕድል ሀብታሙ ታደሰ ወደ ግብነት ቀይሮ የጣና ሞገዶች መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ ቅያሬዎች አድርገው የተመለሱት ብርቱካናማዎቹ ቅያሬያቸው ለውጥ አምጥቶ ግብም ማስቆጠር ችለዋል። በአርባ ሰባተኛው ደቂቃም ተቀይሮ የገባው እንየው ያሻማው ኳስ ቢንያም ወደ ግብነት ቀይሮ የግብ ልዩነቱ ማጥበብ ችሏል። አጥቂው ከግቧ በኃላም ቡድኑ አቻ ለማድረግ ተቃርቦ ነበር።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኃላ መቀዛቀዝ የታየባቸው ባህርዳሮች ምንም እንኳ በእንቅስቃሴ ደረጃ ቢቀዛቀዙም ሙከራ ከማድረግ ግን አልቦዘኑም። ዱሬሳ ሹቢሳ በሁለት አጋጣሚዎች የሞከራቸው ሙከራዎችም ይጠቀሳሉ። በተለይም ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ፍሬው እንደ ምንም ያወጣት ኳስ ለግብ የቀረበች ነበረች።

በስልሳ አራተኛው ደቂቃ ብሩክ ቃልቦሬ በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። በሰማንያ አንደኛው ደቂቃ ደግሞ በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ሳያደርግ የዋለው እና ሁለት ያለቀላቸው ዕድሎች ያባከነው ዱሬሳ ሹቢሳ ግብ አስቆጥሮ ልዩነቱን ማስፋት ችሏል። ግቧም ሲዲቤ አሻምቷት በግንባር የተቆጠረች ነች።

ከግቧ በኃላም ቢንያም ጌታቸው የባህርዳር ተከላካዮች የፈጠሩት ስህተት ተጠቅሞ ያደረጋት ሙከራ ወደ ግብነት መቀየር አልቻለም ፤ አራት ግቦች የተቆጠሩበት ጨዋታ በባህርዳር አሸናፊነት መጠናቀቁ ተከትሎ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ የነበራቸው የሦስት ነጥብ ልዩነት ወደ ግብ ልዩነት አጥብበዋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ የአሰልጣኞች አስተያየቶች ደግአረግ ይግዛው \”የድሬዳዋ አጨዋወት ለመቆጣጠር ጥረት አድርገናል ፤ በቡድናችን በኩልም በሥስቱ አጥቂዎች ለማጥቃት አስበን ነበር የገባነው እሱም ተሳክቶልናል። ስለ ዋንጫ ለማውራት ግዜው አደለም\” ብለው ዋናው እቅዳቸው እያንዳንዱን ጨዋታዎች ማሸነፍ መሆኑ አውስተዋል።

\"\"

በድሬዳዋ ከተማ የመጀመርያ ጨዋታቸው የመሩት አሰልጣኝ አስራት አባተ በበኩላቸው \”ጨዋታው ከጠንካራ ቡድን ጋር ስለሆነ ጠንካራ ነበር። ግቦቹ በተከላካዮቻችን የአቋቋም ችግር የተቆጠሩ ናቸው። በመከላከል ላይ መስተካከል ያለባቸው ነገሮች አሉ ፤ ችግሮቹን ለማረምም ሞክረናል። ዕድሎች በመጠቀም ረገድም ክፍተቶች አሉ።\” ብለዋል። አሰልጣኙ ስለቀጣይ ጨዋታዎች ተጠይቀው \”ከፍተኛ ፉክክር አለ  በቀጣይ ያሉትን ጨዋታዎችን ለማሸነፍ መጣር አለብን\” ብለዋል።