ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛው አደጋ ደርሶበታል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የተመደበበትን ጨዋታ አጠናቆ በመመለስ ላይ የነበረው አርቢትር የመኪና አደጋ አጋጥሞታል።

\"\"

በከፍተኛ ሊግ የምድብ ሀ ውድድር በአሰላ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል። በዛሬው ዕለትም የ19ኛ ሳምንት ሦስት ጨዋታዎች ተካሂደው ተጠናቀዋል። በጠዋቱ የመጀመርያ ጨዋታ ወሎ ኮምቦልቻን ከቤንች ማጂ ቡና ያገናኘውን መርሐግብር ከሌሎች የውድድር ዳኞች ጋር በመሆን በረዳት ዳኝነት ያጫወተው ኢንተርናሽናል ዳኛ አበራ አብረድው የመኪና አደጋ አጋጥሞታል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ከቤተሰቦቹ ጋር በዓልን ለማክበር ከአሰላ መናህርያ ወደ ሻሸመኔ መጓዝ የጀመረው አበራ 15 ኪሎ ሜትር ከተጓዘ በኋላ በአሰላ ከተማ ዙርያ በምትገኘው ቢላሎ በምትባል ገጠራማ አካባቢ የመኪና መገልበጥ አደጋ ደርሷል። በውስጡ የነበሩ ለጊዜው ማንነታቸው የማይታወቁ አስር ተሳፋሪዎች ህይወታቸው አልፏል። የቀሩት ወደ አሰላ ሪፈራል ሆስፒታል በህክምና ላይ እንደሚገኙ የቀይ መስቀል አባላት ገልፀዋል።

ኢንተርናሽናል ዳኛ አበራ አብርደው እጁ አካባቢ መጠነኛ አደጋ እንደደረሰበት እና ህክምናውን በተገቢው መንገድ በመከታተል በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኝ በአሰላ የሚገኘውን ውድድር በላይነት እየመሩ የሚገኙት አቶ ሰለሞን ነግረውናል።

\"\"