ሪፖርት | ሀድያ ሆሳዕና ደረጃውን ያሻሻለበትን ድል አሳክቷል

ሀድያ ሆሳዕና በፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን እና ፀጋዬ ብርሀኑ ጎሎች አርባምንጭ ከተማን 2-0 አሸንፏል።

ሀድያ ሆሳዕና ባለፈው በድሬዳዋ ሲሸነፉ ከተጠቀሙት በአራቱ ላይ ለውጥ አስፈልጎታል። እያሱ ታምሩ ፣ መለሰ ሚሻሞ ፣ ራምኬል ሎክ እና ሪችሞንድ ኦዶንጎን በሔኖክ አርፊጮ ፣ ስቴፈን ኒያርኮ ፣ ፀጋዬ ብርሀኑ እና ዘካሪያስ ፍቅሬን ሲተኩ አርባምንጮች ድል ካደረገው ስብስባቸው መላኩ ኤልያስ እና አላዛር መምሩን በወርቅይታስ አበበ እና አህመድ ሁሴን ለውጠዋል።

\"\"

በሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በርከት ባሉ ረጃጅም ኳሶች ታጅበው የተጓዙበትን መንገድ በመጀመሪያዎቹ አስራ አምስት ያህል ደቂቃዎች ታዝበናል። ሀድያ ሆሳዕናዎች በሁለቱ ኮሪደሮች በኩል በሚሻገሩ እና የመስመር አጥቂዎቻቸው ዕገዛን ተጠቅመው ግብን ለማግኘት ፍለጋ ላይ የተሰማሩበትን ፣ አርባምንጭ ከተማዎች በበኩላቸው ተመሳሳይ ይዘት ያለውን ተሻጋሪ ኳስ አህመድን በይበልጥ የተጠቀሙበትን አጨዋወት አስተውለናል። 5ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ ወደ ውስጥ ብርሀኑ በቀለ የላከለትን ኳስ ባዬ ገዛኸኝ ከግቡ ጋር በቀላሉ አገናኘው ተብሎ ሲጠበቅ ግብ ጠባቂው መኮንን መርዶክዮስ በጥሩ ቅልጥፍና የመጀመሪያ የጨዋታው ሙከራን አምክኗታል። ለማጥቃት ወደ ሀድያ የሜዳ ክፍል ለመግባት አይቸገሩ እንጂ የጥራት ጉድለት ችግር የተስተዋለባቸው አርባምንጮች አህመድ ባገኘው የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚ ሔኖክ አርፊጮ ደርሶ ባመከናት የምታስቆጭ ዕድልን አግኝተው ነበር።

ከረጃጅም ኳሶቻቸው በተወሰነ መልኩ መለስ ካሉ በኋላ በጥልቀት ለመጫወት መንቀሳቀስ የጀመሩት አርባምንጮች 16ኛው ደቂቃ ወርቅይታደስ ለማሻማት ወደ ውስጥ የላካት ኳስ አቅጣጫ ቀይራ ፔፕ በያዛት እና ኤሪክ ካፓይቶ በጥሩ ቅብብል ያገኛትን ሳጥን ውስጥ ገብቶ አክርሮ መቶ ፔፕ በግሩም ሁኔታ ባወጣበት ኳስ ተጋጣሚያቸውን ቀስ በቀስ መፈተን ቢጀምሩም የኋላ ኋላ ወደ ጨዋታ ቅኝት በገቡት ሀድያ ሆሳዕናዎች ብልጫ ተወስዶባቸዋል። በመስመር አጨዋወት መሪ የሚሆኑበትን ዕድል ለማግኘት በዘካርያስ እና ብርሀኑ አማካኝነት ሙከራን አከታትለው አድርገው በመጨረሻም ጎል አስቆጥረዋል። 33ኛው ደቂቃ ብርሀኑ በቀለ በግራ የአርባምንጭ የግብ ክልል ወደ ውስጥ ሰብሮ ገብቶ ወደ ጎል መቶ በግብ ጠባቂው መኮንን ስትመለስ በድጋሚ አግኝቶ ጥሩ አቋቋም ላይ ለነበረው ፍቅረየሱስ ሰጥቶት አማካዩ ከመረብ ጋር ደባልቋት ሀድያን መሪ አድርጎ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ጨዋታው ከዕረፍት ተመልሶ ሲቀጥል በእጅጉ ተሻሽለው ወደ ሜዳ የተመለሱት አርባምንጭ ከተማዎች ነበሩ።  ኳስን በአንድ ለአንድ እና ወደ መስመር ደርሰው ወደ ሳጥን በሚጣሉ ኳሶች ወደ አቻነት ለመምጣት ሻል ባለ ተነሳሽነት ለመጫወት የሞከሩ ሲሆን ሀድያ ሆሳዕናዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተለሳለሰ አቀራረብ ይቋረጡ የነበሩ ኳሶችን ግን በመልሶ ማጥቃት ባዬ እና ብርሀኑ በቀለን ማዕከል ባደረገ መንገድ ለመንቀሳቀስ ጥረቶችን አድርገዋል። በሙከራዎች  ረገድ ያልደመቀው እንዲሁም እምብዛም በነበረው አጋማሽ 66ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ የጨዋታ ፍሰት ወርቅይታደስ ከቀኝ የላካትን ኳስ ተመስገን ደረሰ በግንባር ገጭቶ በሚገርም ብቃት ፔፕ ሰይዶ አውጥቶበታል። ኳስን በእግራቸው በሚይዙበት ወቅት ፈጣን የሽግግር ምንጮችን ሲጠቀሙ አደገኛ አካሄድን የሚከተሉት ሀድያዎች 74ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ሪችሞንድ ኦዶንጎ ያቋረጠውን ኳስ ተመስገን ብርሀኑ ወደ ሳጥን ገብቶ በጥሩ ዕይታ ያደረሰውን ፀጋዬ ብርሀኑ ሁለተኛ ጎል አድርጓታል።

በኳስ ቁጥጥሩ ተሽለው የነበረ ቢሆንም ጎልን በድጋሚ ካስተናገዱ በኋላ እየወረዱ የመጡት አርባምንጮች ከተማዎች የተጫዋች ለውጥን ጭምር በማድረግ ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው  ጨዋታው በሀድያ ሆሳዕና 2ለ0 አሸናፊነት ተቋጭቷል

የአርባምንጭ ከተማው አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በመጀመሪያው አጋማሽ ተጋጣሚያቸው የተሻለ እንደሆነ ከገለፁ በኋላ በሁለተኛው አጋማሽ ግን በተወሰነ መልኩ እንደሚሻሉ ጨዋታውን እንደተቆጣጠሩ ቢገልፁም በእግር ኳስ የሚያጋጥሙ ክፍተቶች ተፈጥረው እንደተሰነፉ በንግግራቸው አካተዋል። የሀድያ ሆሳዕናው አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ በበኩላቸው ጥሩ ጨዋታ እና ለእኛ ደስ የሚል ነበር ካሉ በኋላ ያገኘናቸውን በአግባቡ ተጠቅመን አሸንፈናል ተሳክቶልናልም ያሉ ሲሆን በሁለተኛው አጋማሽ ተጋጣሚያቸው የተሻለ ቢሆንም በመልሶ ማጥቃት ከፍተው በሚመጡበት ሰዓት ተጫውተው እንደነበር በዚህም ማሸነፍ መቻላቸውን ጠቁመዋል።

\"\"