መረጃዎች | 80ኛ የጨዋታ ቀን

የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ20ኛ ሳምንት የመክፈቻ ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰባስበናል።

አርባምንጭ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና

በአምስት ነጥቦች እና አምስት ደረጃዎች ተበላልጠው በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ አስራ ሁለተኛ እና ሰባተኛ ቦታ ላይ የተቀመጡት አርባምንጭ እና ቡና በተመሳሳይ በ18ኛ ሳምንት ካሳኩት ድል ጋር ዳግም ተገናኝቶ ደረጃዎችን ለማሻሻል ጥሩ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

በዘንድሮ የውድድር ዓመት አንድም ጊዜ ቢሆን ተከታታይ ድል አስመዝግቦ የማያውቀው አርባምንጭ ከተማ በውጤትም ሆነ በእንቅስቃሴ ረገድ በወጥነት ወጥ ያልሆነ ቡድን ነው። የቡድኑ አሠልጣኝ መሳይ በየጨዋታው ተጫዋቾችን እየለዋወጡ ጠንካራውን ምርጥ 11 ለመፈለግ ቢሞክሩም እስከ 20ኛ ሳምንት ድረስ ሀሳባቸው አልሰመረም። ከምንም በላይ ደግሞ ከዚህ ቀደም የሚታወቁበት ጠንካራው የመከላከል አደረጃጀት መፈረካከሱ \’በእንቅርት ላይ\’ እንዳሉት ሆኖባቸዋል። ከወገብ በታች ያለው የክለቦች የነጥብ መቀራረብ ያን ያህል ያሉበት ደረጃ አሳሳቢ እንዳይሆንባቸው ቢያደርግም በቶሎ ወደ አስተማማኝ ደረጃ ለመምጣት ጨዋታዎችን በተከታታይ ማሸነፍ ይገባቸዋል።

\"\"

በጊዜያዊ አሠልጣኙ ዮሴፍ ተስፋዬ የሚመራው ኢትዮጵያ ቡና ከአምስት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ ወልቂጤ ከተማን አንድ ለምንም አሸንፎ ከናፈቀው ድል ጋር ዳግም ቢገናኝም ባሳለፍነው ሳምንት ወደ አቻ ውጤት ተመልሷል። ከወጥነት ጋር ተያይዞ ችግሮች ያሉበት ቡድኑ በተለይ ከወገብ በላይ ያለው ስልነት በርካታ ጥያቄዎች አሉበት። በርካታ ወጣት አጥቂዎችን በስብስቡ ቢይዝም ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ተጋጣሚው ላይ በድምሩ ከሁለት ጎል በላይ ማስቆጠር አልቻለም። እርግጥ የነገው ተጋጣሚው ከላይ እንደገለፅነው በሚታወቅበት ጠንካራ የመከላከል አጨዋወቱ ላይ ድክመቶች ቢኖሩበትም ቡና የራሱን ችግር አሻሽሎ በራሱ መንገድ ጨዋታውን ለመወሰን ክፍተቱን ማረም ይገባዋል።

በአርባምንጭ ከተማ በኩል ምንም የጉዳት እና የቅጣት ዜና የለም። ኢትዮጵያ ቡና ግን ከአስራት ቱንጆ ባሻገር ሮቤል ተክለሚካኤል እና አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ ጉዳት ላይ ስላሉበት ግልጋሎታቸውን አያገኝም።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ17 ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን አርባምንጭ ከተማዎች 7 ጨዋታዎች በማሸነፍ የበላይነትን ሲይዙ ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ በ6 ጨዋታዎች ረተዋል። የተቀሩት አራት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።

ጨዋታውን ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ በዋና ዳኝነት ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ሙስጠፋ መኪ እና ሶርሳ ዱጉማ በረዳት ዳኝነት እንዲሁም ኤፍሬም ደበሌ በአራተኛ ዳኝነት ይመሩታል።

ለገጣፎ ለገዳዲ ከባህር ዳር ከተማ

በፕሪምየር ሊጉ ደረጃ ሰንጠረዥ በቅደም ተከተል የወራጅ ቀጠናው እንዲሁም የዋንጫ ፉክክር ውስጥ የሚገኙት ለገጣፎ እና ባህር ዳር ካሉበት ዓላማ ጋር በሚያደርጉት ፍልሚያ ሦስት ነጥብ አግኝተው ወደ ውጥናቸውን የሚያደርጉትን ጉዞ ለማስቀጠል ነገ የሚያደርጉት ጨዋታ ጥሩ የአልሸነፍ ታጋይነት እንደሚደረግበት ይገመታል።

በ19 ሳምንታት የእስካሁን የሊጉ ጉዞ ብዙ ሽንፈቶችን (13) ያስተናገደው ለገጣፎ ለገዳዲ በሁለተኛው ዙር የሊጉ ውድድር በዐይን የሚታይ በቁጥሮች የሚደገፍ አንፃራዊ ለውጥ እያስመለከተ ይገኛል። ምንም እንኳን ቡድኑ በሚፈለገው ደረጃ ውጤቶችን እያገኘ ባይገኝም በሁለተኛው ዙር አራት ጨዋታዎች በመጀመሪያው ዙር አጠቃላይ አስራ አምስት ጨዋታዎች ካስመዘገበው ነጥብ ከግማሽ በላዩን (66.7%) አሳክቷል። እርግጥ በ18ኛው ሳምንት መሻሻሎቹን ገደል የከተተ የ7ለ1 ሽንፈት ቢያስተናግድም ተሟጦ ያላለቀውን የመውረድ ጉዳይ ለመጋፈጥ አሁንም ዕድል ስላለው የነገውን ጨዋታ በቀላሉ ይመለከታል ተብሎ አይጠበቅም።

ኮስታራ የዋንጫ ተፎካካሪ እንደሆነ በየጨዋታ ሳምንቱ እያሳየ የሚገኘው ባህር ዳር ከተማ ለተጋጣሚው ሦስት ነጥብ ካስረከበ ሰባት ጨዋታዎች አልፈዋል። በሁሉም የሜዳ ክፍሎች የተረጋጋ ስብስብ ያለው ባህር ዳር ከኳስ ጋር ጊዜ በማሳለፍም ሆነ ከኳስ ውጪ ባለ ውቅር እንዲሁም በድብልቅ የማጥቃት አጨዋወት የተዋጣለት ነው። ከጊዮርጊስ እና መድን በመቀጠል ብዙ ጎሎችን ተጋጣሚ ላይ ያስቆጠረው ቡድኑ ተከታታይ ድል ባስመዘገበባቸው ባለፉት አራት ጨዋታዎች በድምሩ 12 ግቦችን አስቆጥሮ የበለጠ ማጥቃቱ አስፈሪ እንደሆነ አሳይቷል። በተቃራኒው ያስተናገዳቸው ጎሎች ደግሞ ሦስት ብቻ ናቸው። ይህ ደግሞ በሁለቱም የፍፁም ቅጣት ምት ክልሎች ምን ያህል ስል እንደሆነ ያሳያል።

\"\"

በሀገራችን ትልቁ የሊግ እርከን ውድድር ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች በ5ኛ ሳምንት በተደረገው የምሳ ሰዓት ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ ሁለት ለምንም አሸንፎ ነበር።

አዳነ ወርቁ በመሀል ዳኝነት፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ይበቃል ደሳለኝ እና ሙሉነህ በዳዳ ረዳት እንዲሁም ኢንተርናሽናል ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ በበኩሉ አራተኛ ዳኛ ሆነው ተመድበዋል።