ሪፖርት | አርባምንጭ እና ቡና በድምሩ 19ኛ የአቻ ውጤት አስመዝግበዋል

በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ ሳቢ ፉክክር ያስተናገደው የአርባምንጭ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ 1-1 ተጠናቋል።

አርባምንጭ ከተማ ከሀዲያ ሆሳዕናው ሽንፈት ባደረጋቸው አራት ለውጦች መላኩ ኤልያስ ፣ አንዷለም አስናቀ ፣ አቡበከር ሻሚል እና አሸናፊ ተገኝን አስጀምሯል። ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ ከሲዳማው ጨዋታ አንፃር ጉዳት የገጠመው ሮቤል ተክለሚካኤልን በራድዋን ናስር ተክቷል።

\"\"

ፈጠን ባለ የማጥቃት ፍላጎት በተጀመረው ጨዋታ ቡድኖቹ ከኃይለሚካኤል አደፍርስ እና ወርቅይታደስ አበበ በተሻገሩ ኳሶች አደጋ ለመፍጠር ከጫፍ ደርሰው ነበር። በጊዜ ጉዳት የገጠመው ጫላ ተሺታን በቃለአብ ፍቅሩ ለመቀየር የተገደዱት ቡናዎች ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ምት በመግባት በጥሩ ቁጥጥር ወደ ግብ መድረስ ጀምረዋል። በተለይም 17ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ በየነ ከአማኑኤል ዮሐንስ ጋር አንድ ሁለት ተቀባብሎ ያገኘው ያለቀለት ዕድል ተጠቃሽ ሲሆን ብሩክ ኢላማውን ሊስት ችሏል።

ጨዋታው ከ20 ደቂቃ ሲያልፍ ግን ኃይል ቀላቅለው ጀምረው የነበሩት አርባምንጮች በተራቸው የበላይነቱን ተረክበዋል። በተለይም በቀኝ መስመር ከፍ ያለ ጫና የፈጠሩ ሲሆን 23ኛው ደቂቃ ላይ በርናንድ ኦቼንግ ከቀኙ የሳጥኑ መግቢያ ላይ ያረገውን ሙከራ ተመስገን ደረሰ ጨርፎት በእዝቄል ሞራኬ ብቃት ዳነ እንጂ ቡድኑ ቀዳሚ ሊሆን ነበር። በቀሪው የአጋማሹ ደቂቃዎችም ያለቀለት ዕድል አይፍጠሩ እንጂ ተጋጣሚያቸው ከራሱ ሜዳ እንዳይወጣ ገፍተው የተጫወቱት አዞዎቹ 43ኛው ደቂቃ ላይ መሪ ሆነዋል። ጎሉ ግብ ጠባቂው እዝቄል ሞራኬ ከኩዌኩ ዱሀ የደረሰውን ኳስ ለማቀበል ሲሞክር በሰራው ስህተት ቅርቡ የነበረው ተመስገን ደረሰ በቀላሉ ያስቆጠረው ነበር።

\"\"

ከዕረፍት መልስ ቡናዎች ተሻሽለው ቀርበዋል። ለተጋጣሚያቸው ሳጥን ቀርበው ቅብብሎችን በመከወን ሙከራዎችን ለማድረግ ተደጋጋሚ ጥረት አድርገዋል። በአንፃሩ አርባምንጬች በጠንካራ መከላከል ኳሶችን እየደረቡ በማውጣት ምላሽ ሰጥተዋል። የቡና ጫና ቀጥሎ 59ኛው ደቂቃ ላይ የብሩክን ተቀይሮ መውጣት ተከትሎ ወደ መሀል አጥቂነት የመጣው መሐመድኑር ናስር አርባምንጮች በተከፈቱበት ቅፅበት ከአማኑኤል ዮሐንስ የደረሰውን ኳስ ግብ ጠባቂ በማለፍ ጭምር ጎል አድርጎታል።

\"\"

ከግቡ በኋላም የቡናዎች የበላይነት በተለይም በመስመር በሚደረጉ ጥቃቶች ቀጥሎ ታይቷል። በተለይም 69ኛው ደቂቃ ላይ መስፍን ታፈሰ ከግራ ሰብሮ በመግባት አክርሮ የመታውን ኳስ መኮንን መርዶኪዮስ ነበር ያዳነው። ሁኔታው ያላማራቸው አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በ10 ደቂዎች ሦስት ተከታታይ ቅያሪዎችን ካደረጉ በኋላ አዞዎቹ በመጠኑ ተነቃቅተው የአጋማሹን ቀዳሚ ከባድ ሙከራ አድርገዋል። በ75ኛው ደቂቃ እንዳልካቸው መስፍን ከሳጥኑ መግቢያ ላይ ያደረገውን ይህን ሙከራ እዝቄል ሞራኬ ለጥቂት አውጥቶታል።

\"\"

የጨዋታው ቀሪ ደቂቃዎች በፍፁም ቅጣት ምት ጥያቄዎች ፣ በጨዋታ ውጪ ውሳኔ በሚቋረጡ ጥቃቶች እና በሁለቱም በኩል የሚሰነዘሩ ፈጣን የማጥቃት ምልልሶች እየታዩበት ተጋግሎ የቀጠለ ነበር። ወደ ፍፃሜው ሲቃረብ የአርባምንጮች ቀጥተኛ ኳሶች ጫናቸው እየጨመረ የመጣ ሲሆን ተቀይሮ ገብቶ ጥሩ የተንቀሳቀሰ የቆየው መሪሁን መስቀለ በጭማሪ ደቂቃ ላይ ያደረሰውን ጥሩ ኳስ አህመድ ሀሴን በግራ አጥብቦ ገብቶ አምክኖት ጨዋታው 1-1 እንዲጠናቀቅ ሆኗል። ውጤቱም ለአርባምንጭ 10ኛ ለቡና ደግሞ 9ኛ የአቻ ውጤት ሆኖ ተመዝግቧል።

\"\"

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በሁለተኛው አጋማሽ ወደ መጨረሻ ላይ ቡድናቸው መሻሻሉን ገልፀው ቡድናቸው ኳስ ሲይዝ ያለው በራስ መተማመን መጨመር እንዳለበት ጠቁመዋል። አሰልጣኝ ዮሴፍ ተስፋዬ በበኩላቸው ቡድናቸው በእንቅስቃሴ እየተሻሻለ መምጣቱን አጨራረስ ላይ ግን እንደሚቀረው አስረድተው ግብ ጠባቂያቸው መውጫ መንገድ እየነበረው ስህተት መስራቱን አንስተው በቀጣይ እንደሚያስተካክሉ ተናግረዋል።