የጌታነህ ከበደ አነጋጋሪ አስተያየቶች…

\”…ካጠገብ የሚጫወት አሲስት የሚያደርግ ተጫዋች ስለሌለ ያ ነገር በኮከብ ግብ አግቢነት ወደ ፊት እንዳልሄድ ጫና አድርጎብኛል…\”

\”…ልምምድ ሳንሰራ ሁሉ የተጫወትናቸው ጨዋታዎች ነበሩ…\”

\”…አሸንፈንም ቢሆን ማንም ዞር ብሎ የሚያየን የለም…\”

የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ 09:00 ላይ ባስተናገደው ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ 2-0 ሲመራ ቆይቶ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ነጥብ የተጋራበትን ውጤት አስመዝግቧል። ከጨዋታው በኋላ አንድ ግብ አመቻችቶ አንድ ያስቆጠረው የሰራተኞቹ አምበል ጌታነህ ከበደ የሱፐር ስፖርት የጨዋታው ኮከብ በመባል ተመርጦ ለቀረቡለት ጥያቄዎች የሰጣቸው ምላሾች አነጋጋሪ ሆነዋል።

\"\"

ከቴሌቪዥን ጣቢያው ጋር የነበረውን ቆይታ እየመሩ ነጥብ መጣላቸው ስለፈጠረበት ስሜት በመናገር የጀመረው ጌታነህ ከበደ በመቀጠል በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ፉክክሩ ሁለተኛ ደረጃ ላይ አንደመቀመጡ ወደ ኦሮ አጎሮ ስለመድረስ በቀጣይ ምን እንደሚያስብ ጥያቄ ቀርቦለታል። ተጫዋቹ በሰጠው ምላሽ ጉዳዩን የቡድን እና አጠገቡ የሚኖረው ተጫዋች ጥራት እንደሚወስነው ይህም በቂ ኳሶች ባለማግኘቱ ተፅዕኖ እንደፈጠረበት በማንሳት \”በአሲስት ደረጃ እንኳን ቢቆጠር ወይ ቅጣት ምት ወይ ከማዕዘን የግንባር ኳስ ነው እንጂ አሲስት ተደርጎ…ካጠገብ የሚጫወት አሲስት የሚያደርግ ተጫዋች ስለሌለ ያ ነገር በኮከብ ግብ አግቢነት ወደ ፊት እንዳልሄድ ጫና አድርጎብኛል። እንዳየኸው ከሆነ እየተመለስኩ የምጫወተው እኔ ነኝ ፤ የገቡት ጎሎች እንዳለ ብታያቸው እኔ ነኝ ለሌሎች ተጫዋቾች አሲስት እያደረኩ የሚገቡት ፤ ያ ነገር ትንሽ ወደ ኋላ አስቀርቶኛል።\” ሲል ሁኔታውን አስረድቷል።

ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ብዙ ዓመት እንደተጫወተ እና የሚችለውን እንዳደረገ የአሰልጣኝ ለውጥ ቢኖርም እንዳማይመለስ የጠቆመው ጌታነህ በመጨረሻው ጥያቄ የወልቂጤ ከተማ ተጫዋቾች እያለፉበት ስላለው ፈተና አስረድቷል።

\"\"

\”ወልቂጤ ብዙ ፈተናዎች አሉበት ፤ እንደምትሰሙት በተጨዋቾች ደመወዝ አከፋፈል ላይ። አዲስ የገቡት አምስት ወራቸው ነው። እኛ በፊት የነበርነው ወደ ስምንት ወርም ያለው ተጫዋች አለ። ስምንት ወር ደመወዝ ሳይከፈለው መጫወት ራሱ ተጫዋቾችን ማመስገን ይገባል። እየታገሉ ነው የሚጫወቱት ፤ አንዳንዴ እንደውም ልምምድ ሳንሰራ ሁሉ የተጫወትናቸው ጨዋታዎች ነበሩ። በየሦስት ቀኑ ነበር ሊጉ ሲጀምር የነበረው እና ልምምድ ሳንሰራ ተጠራርተን በአሰልጣኛችን ጥሪ ነው የተጫወትነው። ብንሸነፍ ማንም የሚመጣ የለም። ስንሸነፍ ሦስት በተከታታይ ተጫውተናል ፤ ማንም የመጣ የለም። ዞር ብሎ የሚያየን የለም። በራሳችን ነው ፤ \’ራሳችንን እናትርፍ እና ጥሩ ነገር ስናሳይ ሌላ ክለብ ያየችኋል\’ በማለት ነው ተጫዋቾቹ እየተጫወቱ ያሉት። አሸንፈንም ቢሆን ማንም ዞር ብሎ የሚያየን የለም። ያው እኛ ራሳችን እየታገልን ነው። አምስት ወር ማለት ለአንድ ተጫዋች ከቤተሰብ ጋር ከባድ ነው ፤ ግማሹ ሰባት ወር ሆኖታል። እንደገና እንደሌላው ክለብ ቅድመ ክፍያ ቼክ የሚሰጣቸው ልጆች አሉ ፤ ከደመወዛቸው ተቆርጦ የሚሰጣቸው። ያ እንኳን አልተሰጣቸውም ፤ እሱ እንኳን ቢሰጣቸው ማስታገሻ ነበር። ቼክ ይዘው ቁጭ ብለዋል።\”