ሪፖርት | ወላይታ ድቻ የአዳማ ቆይታውን በተከታታይ ድል ደምድሟል

ወላይታ ድቻ እና ለገጣፎ ለገዳዲን ያገናኘው የ22ኛ ሳምንት ቀዳሚ ጨዋታ በጦና ንቦች ሁለት ለባዶ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ወላይታ ድቻዎች መቻልን ካሸነፈው አሰላለፍ ቢንያም ፍቅሬን በስንታየሁ መንግስቱ ተክተው ሲገቡ በለገጣፎዎች በኩልም ከሀድያ ሆሳዕና አቻ ከተለያየው ስብስብ ሱራፌል ዐወል እና ተስፋዬ ነጋሽ በጋብርኤል አሕመድ እና ያሬድ ሀሰን ተለውጠው ጨዋታውን ጀምረዋል።

\"\"

በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች በሁሉም ረገድ ብልጫ የወሰዱት ወላይታ ድቻዎች ብልጫ በፈጠሩባቸው ደቂቃዎች በርካታ የግብ ዕድሎች መፍጠር ባይችሉም በሁለት አጋጣሚዎች ግን ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። እነዚህም አበባየሁ ከርቀት ያደረገው ሙከራ እና ዘላለም አባተ በአክሮባት ሞክሮት ሚክያስ ያወጣው ሙከራ ለግብ የቀረቡ ነበሩ። በ37ኛው ደቂቃ ግን ተጋጣሚያቸው ብልጫ በወሰደበት ግዜ በስንታየሁ መንግሥቱ አማካኝነት ግሩም ግብ አስቆጥረው መሪ መሆን ችለዋል። አጥቂው ግብ ጠባቂው በረዥሙ የለጋው ኳስ ኤልያስ አታሮ በአግባቡ ባለማራቁ ያገኘው አክርሮ በመምታት ነበር ግሩም ግብ ያስቆጠረው።

በመጀመርያ ደቂቃዎች የተወሰደባቸው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በተወሰነ መልኩ ቀልብሰው ዕድሎች ለመፍጠር ያልተቸገሩት ለገጣፎዎች በይብሳ አማካኝነት ሦስት ጥሩ ሙከራዎች አድርገዋል። በተለይም መሐመድ በጥሩ ሽግግር ወደ ተጋጣሚ የወሰደው ኳስ ኢብሳ አግኝቶ መትቶ የወላይታ ድቻው ግብ ጠባቂ የመለሳት ኳስ እና ከመአዝን የተሻማው ኳስ ተጠቅሞ በግንባር ያደረጋት ሙከራ ለግብ የቀረቡ ነበሩ።

የጦና ንቦቹ ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ በአበባየው አማካኝነት ግብ ለማስቆጠር አምስት ደቂቃዎች ብቻ ነበር የፈጀባቸው። በሀምሳኛው ደቂቃም አናጋው በረዥሙ ያሻማው ኳስ በረከት በግሩም ሁኔታ በግንባር አመቻችቶት በግቡ አፋፍ የነበረው አበባየሁ ወደ ግብነት ቀይሮታል።

የጦና ንቦች ከግቡ በኋላም ጫና ፈጥረው በርካታ ዕድሎች መፍጠር ችለዋል ፤ ዮናታን አሻምቶት በሳጥን ውስጥ የነበሩ በርካታ የወላይታ ድቻ ተጫዋቾች ያልተጠቀሙበት ኳስ ፤ አናጋው ባደግ ከርቀት አክርሮ መቶት ግብ ጠባቂው ወደ ውጭ ያወጣው ሙከራ እና መሳይ ከርቀት ያደረገው ሌላ የረዥም ርቀት ሙከራ ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው።

በሁለተኛው አጋማሽ በሁሉም መለክያዎች
የወረደ እንቅስቃሴ ያደረጉት ለገጣፎዎች ጠጣሩ የወላይታ ድቻ አማካይ ክፍል አልፈው ዕድሎች መፍጠር አልቻሉም። ሆኖም በአማኑኤል አረቦ እና ፍቅሩ አማካኝነት ሙከራ ማድረግ ችለዋል። በተለይም ኢብሳ በግሩም ሁኔታ አመቻችቶት በጥሩ አቋቋም የነበረው አማኑኤል ወደ ግብነት ያልቀየረው ኳስ በለገጣፎ በኩል ወርቃማ ዕድል ነበር።

ከጨዋታው በኋላ አስተያየታቸውን የሰጡት የወላይታ ድቻው ምክትል አሰልጣኝ ጣሰው ታደሰ የተሻለ ነገር አሳይተን አሸንፈን ወጥተናል ፤ ያሰብነው ነገር ከሞላ ጎደል ለመተግበር ሞክረናል \” ብለዋል። የለገጣፎ ለገዳዲ አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደግዮርጊስ በበኩላቸው \”በመጀመርያው አጋማሽ ኳስ አልፎ አልፎ ኳስ በማንሸራሸር ለመከላከል አስበን ነበር የገባነው በሁለተኛ አጋማሽ ግን ቅያሬዎች አድርገን ለመጫወት ሞክረናል ግን በመጀመርያው ንክኪ ነው ግብ የገበብን\” ካሉ በኋላ ከእንደዚህ ዓይነት ጨዋታዎች ነጥብ ካላገኙ አስቸጋሪ እንደሚሆን ገልፀዋል።

\"\"