የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ | የ 25ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ

ዛሬ በተጠናቀቀው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 25ኛ ሳምንት ሀዋሳ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ድል ሲቀናቸው የአርባምንጭ ከተማ እና የቦሌ ክ/ከተማ ጨዋታ ያለ ግብ ተጠናቋል።

አዲስ አበባ ከተማ 0-2 ሀዋሳ ከተማ

\"\"

ረፋድ 4 ሰዓት ላይ በተጀመረው ጨዋታ መጠነኛ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ አልፎ አልፎ በሚያደርጉት ጥሩ የማጥቃት እንቅስቃሴ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል የተሻሉ የነበሩት ሀዋሳዎች 5ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ግቡንም ሲሣይ ገ/ዋህድ በቀኝ መስመር ድንቅ በሆነ ክህሎት ተከላካዮችን ጥሳ በማለፍ እና ከግብ ጠባቂዋ ከፍ አድርጋ በመምታት መረቡ ላይ አሳርፋዋለች። 11ኛው ደቂቃ ላይ ረድዔት አስረሳኸኝ በቀኙ የሳጥኑ ጠርዝ ላይ ሆና መሬት ለመሬት በመምታት ያደረገችው ሙከራ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት ሲወጣባት ሌላኛዋ አጥቂ እሙሽ ዳንኤል ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ በጥሩ አጨራረስ ተጨማሪ ግብ አስቆጥራ የቡድኗን መሪነት አጠናክራለች። ጥሩ የኳስ ቁጥጥር የነበራቸው አዲስ አበባዎች የተሻለውን የመጀመሪያ የግብ ዕድል 29ኛው ደቂቃ ላይ ሲፈጥሩ አስራት ዓለሙ በሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ  ግብ ጠባቂዋን በማለፍ ወደ ውስጥ ያሻገረችውን ኳስ ዘግይታ ያገኘችው ቤተልሔም መንተሎ ያደረገችውን ሙከራ ተከላካዮች ተደርበው ሲመልሱባት በአንድ ደቂቃ ልዩነት ራሷ ቤተልሔም መንተሎ የሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ያደረገችውን ሙከራ ግብ ጠባቂዋ መስከረም መንግሥቱ መልሳባታለች።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተቀዛቅዞ ሲቀጥል የመጨረሻ 15 ደቂቃዎች በአንጻራዊነት የተሻሉ ነበሩ። በአጋማሹ የተሻሉ ሁለት የግብ ሙከራዎች በሀዋሳ ከተማ ሲደረጉ በቅድሚያም 79ኛው ደቂቃ ላይ ረድዔት አስረሳኸኝ ከቀኝ መስመር ያሻገረችውን ኳስ ያገኘችው ሣራ ነብሶ ያደረገችውን ሙከራ ተቀይራ የገባችው ግብ ጠባቂዋ ስርጉት ተስፋዬ መልሳባታለች። ከአራት ደቂቃዎች በኋላም ተቀይራ የገባችው ነጻነት መና ከቀኙ የሜዳ ክፍል ላይ አክርራ የመታችው ኳስ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቷል። ይህም የጨዋታው የተሻለ የመጨረሻ ትዕይንት ሆኖ ጨዋታው በሀዋሳ ከተማ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

አርባምንጭ ከተማ 0-0 ቦሌ ክ/ከተማ

8 ሰዓት ላይ በተደረገው ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ለመውሰድ ጥሩ ፉክክር ቢደረግበትም አንድም ለግብ የቀረበ ሙከራ ያልተደረገበት ነበር። በአርባምንጭ በኩል 12ኛው ደቂቃ ላይ ቤተልሔም ታምሩ በግራ መስመር ከተገኘ የማዕዘን ምት ያሻገረችውን ኳስ ያገኘችው ቤተልሔም ግዛቸው በዓየር ላይ እንዳለ በእግሯ ያደረገችው ያልተጠበቀ ሙከራ በአጋማሹ የተሻለው ሙከራ ነው። በማራኪ እንቅስቃሴ መሃል ሜዳው ላይ ብልጫ መውሰድ የቻሉት ቦሌዎች ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ የጠራ የግብ ዕድል ለመፍጠር ተቸግረው አጋማሹን አገባደዋል።

ከዕረፍት መልስም ጨዋታው በተመሳሳይ ሂደት ሲቀጥል 81ኛው ደቂቃ ላይ የቦሌዋ ሜላት አሊሙዝ ከሳጥን ውጪ ጥሩ ሙከራ አድርጋ ተቀይራ የገባችው ግብ ጠባቂዋ ትዕግስት አበራ መልሳባታለች። ሆኖም 92ኛው ደቂቃ ላይ የአርባምንጯ ቤተልሔም ታምሩ ከግራ መስመር ያደረገችው ሙከራ የግቡን የቀኝ ቋሚ ገጭቶ ሲመለስ ከጥቂት ንክኪዎች በኋላ ኳሱን ያገኘችው ቤተልሔም ሰማን ያደረገችው ሙከራም የግቡን አግዳሚ ታክኮ ወጥቶባታል። ጨዋታውም ያለ ግብ ተጠናቋል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ 3-0 አዳማ ከተማ

የሳምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር ኤሌክትሪክ እና አዳማን ሲያገናኝ በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ፉክክር ሲደረግበት የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ግን ኤሌክትሪኮች የተሻሉ ነበሩ። 18ኛው ደቂቃ ላይ መሠሉ አበራ ከቅጣት ምት ከሴኮንዶች በኋላ ደግሞ ሽታዬ ሲሣይ ከሳጥን ውጪ ያደረጓቸውን ሙከራዎች ግብ ጠባቂዋ መሠረት ባጫ ስትመልስባቸው በአዳማ ከተማ በኩል 24ኛው ደቂቃ ላይ ሔለን እሸቱ ከቅጣት ምት ያደረገችው ግሩም ሙከራ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ወጥቷል። በሚያገኙት ኳሱ ሁሉ ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን መፍጠር የቀጠሉት ኤሌክትሪኮች 35ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን ለመምራት ተቃርበው ነበር። ይህን ዕድልም ዐይናለም አሳምነው ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝታ ሳትጠቀምበት ቀርታለች። 45ኛው ደቂቃ ላይ ዐይናለም አሳምነው ያቀበለቻትን ኳስ ያገኘችው ትንቢት ሳሙኤል ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ የግብ ዕድሉን ሳትጠቀምበት ስትቀር ጨዋታው ሊጠናቀቅ የዋና ዳኛዋ ፊሽካ ሲጠበቅ ግን ትዕግሥት ያደታ ግብ አስቆጥራ ኤሌክትሪኮች ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል።

\"\"

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተቀዛቅዞ ሲቀጥል እንዳላቸው የኳስ ቁጥጥር የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የተቸገሩት አዳማዎች 49ኛው ደቂቃ ላይ የአጋማሹን የመጀመሪያ ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር። ሔለን እሸቱ ከቀኝ መስመር በተሻገረላት ኳስ በተረከዟ በመምታት በቄንጥ ያደረገችው ሙከራ በግብ ጠባቂዋ እና በግቡ አግዳሚ ተመልሶባታል። ከዚህ ሙከራ በኋላ ጨዋታውን የተቆጣጠሩት ኤሌክትሪኮች 51ኛው ደቂቃ ላይም መሪነታቸውን አጠናክረዋል። ዐይናለም አሳምነው በድጋሚ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝታ ያመከነችውን ኳስ በሴኮንዶች ልዩነት ግራ መስመር ላይ ሆና ያገኘችው ትንቢት ሳሙኤል ግሩም ግብ አድርጋዋለች። በአራት ደቂቃዎች ልዩነት ደግሞ ራሷ ዐይናለም አሳምነው ከብዙ ጥረቶች በኋላ ተሳክቶላት ያደረገችው ሙከራ የግብ ጠባቂዋን እጅ ጥሶ መረቡ ላይ አርፏል። ከዚህ ግብ በኋላም ጨዋታው እጅግ ተቀዛቅዞ በመቀጠል በኢትዮ ኤሌክትሪክ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።