መረጃዎች | 90ኛ የጨዋታ ቀን

በአዳማ ከተማ ነገ የሚደረጉትን የመጨረሻ የ22ኛ ሳምንት የሦስተኛ ቀን ጨዋታዎች በተመለከተ ተከታዮቹ ቅድመ-መረጃዎች ተሰባስበዋል።

መቻል ከድሬዳዋ ከተማ

በአንድ ነጥብ እና በአንድ ደረጃ ተበላልጠው 11ኛ እና 10ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት መቻል እና ድሬዳዋ ከተማ ከወራጅነት ስጋት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመሸሽ ነገ 9 ሰዓት እርስ በእርስ ከባድ ፍልሚያ ያደርጋሉ።

መቻል ከወራጅ ቀጠናው አምስት ነጥብ ርቀት ላይ ተቀምጧል። ባሳለፍነው ሳምንት በወላይታ ድቻ የገጠመው ሽንፈትም በወረጅ ቀጠናው ካሉት ቡድኖች ውጪ በርካታ ሽንፈት (9) በማስተናገድ ከአዳማ ከተማ ጋር ቀዳሚውን ቦታ እንዲይዝ አድርጎታል። ቡድኑ በዋንጫ ፉክክር ውስጥ የሚገኘው ኢትዮጵያ መድንን ከረታ በኋላ ይህንን ሽንፈት ማስተናገዱ በነገው ጨዋታ በድጋሚ የማንሰራራት ሀሳብ ይዞ ጨዋታውን እንዲጀምር ያደርገዋል። በእርግጥ መቻል በአመዛኙ ጠባብ ሽንፈቶችን እያስመዘገበ መገኘቱ በየጨዋታዎቹ በቁጭት ስሜት ከሜዳ እንዲወጣ የሚያደርገው ነው። ለዚህም ቡድኑ ዕድሎችን ወደ ግብ የመቀየር አቅሙ በእጅጉ መሻሻል እንደሚኖርበት መናገር ይቻላል።
\"\"
ከአዲሱ አሠልጣኝ ቅጥር በኋላ የድል እና የሽንፈት ውጤቶችን አፈራርቆ ያስመዘገበው ድሬዳዋ ከተማ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት የነበረበትን የመጨረሻ ሳምንታት የጭንቅ ወቅት ዘንድሮ ላለመድገም እየሞከረ ይመስላል። በተለይ በቅርብ ሳምንታት ከባዶቹን ሀዲያ እና ሀዋሳ ማሸነፉ በብዙዎች ተስፋ እንዲጣልበት ቢያደርግም በባህር ዳር እና በኢትዮጵያ ቡና የደረሱበት ሽንፈቶች መጠራጠሮቹን አምጥተዋል። ከምንም በላይ ደግሞ በሀዋሳው ጨዋታ የተሻሻለው የተከላካይ መስመሩ በቡናው ጨዋታ ዳግም መሸንቆሩ ቡድኑን ችግር ውስጥ የከተተ ይመስላል። የሆነው ሆኖ የነገ ተጋጣሚው መቻልም በብዙ መስፈርቶች ችግር ያለበት ስብስብ በመሆኑ የጎላ ፈተና ላይገጥመው ይችላል።

መቻል ግሩን ሀጎስ፣ ዳግም ተፈራ እና ፍፁም ዓለሙን በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጪ አድርጓል። ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ ያሬድ ታደሠ እና ቢኒያም ጌታቸው አሁንም ከጉዳታቸው ባለማገገማቸው የማይጠቀም ሲሆን ተከላካዩ አሳንቴ ጎድፍሬድ ግን ልምምድ በመጀመሩ የመሰለፉ ዕድል የሰፋ እንደሆነ ተሰምቷል።

በሊጉ ከዚህ ቀደም አስራ ዘጠኝ ጊዜያት የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች መቻሎች በዘጠኝ አጋጣሚ ማሸነፍ ሲችሉ በአንፃሩ ድሬዳዎች ደግሞ ሦስት ጨዋታዎች እንዲሁም የተቀሩት ሰባት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው።

የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው በመሐል ዳኝነት ሶርሳ ዱጉማ እና ሙሉነህ በዳዳ ረዳቶች ዮናስ ካሳሁን ደግሞ አራተኛ ዳኛ ሆነው በጋራ ይመሩታል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከኢትዮጵያ መድን

በደረጃ ሰንጠረዡ የታችኛው እንዲሁም በተቃራኒ በላይኛው ፉክክር ውስጥ የሚገኙት ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ኢትዮጵያ መድን በየዓላማቸው አንድ አርምጃ ለመጓዝ የሚያደርጉት ፍልሚያ ጥሩ የአልሸነፍባይነት ስሜት ይኖረዋል ተብሎ ይታሰባል።

በወራጅ ቀጠናው ቅርቃር ከተገኘ የሰነባበተው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ለከርሞ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለመቆየት ያለውን እጅግ ጠባብ ዕድል ረፍዶበትም ቢሆን ለመጠቀም ነገ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ይጠበቃል። ከድል ጋር ከተገናኘ አስራ ሰባት የጨዋታ ሳምንታት ያስቆጠረው ቡድኑ በአንፃራዊነት በሁለተኛው የሊጉ ውድድር በእንቅስቃሴ ረገድ የተሻለ ይመስላል። እንቅስቃሴው ግን በውጤት አለመታጀቡ አሁንም ዋጋ እያስከፈለው ይገኛል። እርግጥ ባሳለፍነው ሳምንት ቡድኑ በወልቂጤ 2ለ0 እየተመራ በሁለተኛው አጋማሽ በጥሩ ተነሳሽነት አንድ ነጥብ የተጋራበትን ውጤት አግኝቷል። ምናልባት ይህ አጋማሽ ለነገው ጨዋታም ጥሩ መነቃቃት ካመጣ ለተጋጣሚያቸው ፈተና ሊሆኑ ይችላሉ።
\"\"
አሁንም በዋንጫ ፉክክር ውስጥ የሚገኘው ኢትዮጵያ መድን ያለፉትን ሦስት ጨዋታዎች በድምሩ ሰባት ነጥቦችን የጣለ ሲሆን ከፉክክሩ ላለመራቅ ግን በነገው ጨዋታ ተግቶ እንደሚጫወት ይገመታል። ባሳለፍነው ሳምንት ቀጥተኛ ተፎካካሪው ባህር ዳር ከተማን ገጥሞ የነበረው ቡድኑ ቀድሞ ግብ ቢቆጠርበትም የኋላ ኋላ ጨዋታውን የማሸነፍ ዕድል አግኝቶ የነበረ ቢሆንም ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ይህ ቁጭት ቢፈጥርበትም በቶሎ ወደ አሸናፊነት በመመለስ ነጥባቸውን አርባዎቹ ውስጥ ለማድረስ የነገው ጨዋታ ያስፈልጋቸዋል። የነገውን ጨዋታ ጨምሮ ተከታታይ ሦስት ጨዋታዎችን የወራጅ ቀጠናው ስጋት ያለባቸውን ክለቦች መግጠማቸው ፍልሚያውን ሊያከብደው ቢችልም ካሉበት ደረጃ አንፃር ብዙ ይቸገራሉ ተብሎ አይጠበቅም።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጉዳት ላይ የነበረውን የግብ ዘብ ካክፖ ቼሪፍዳይን በነገው ጨዋታ እንደሚያገኝ ተጠቁሟል። ኢትዮጵያ መድን በበኩሉ አሁንም አብዱልከሪም መሐመድን በጉዳት ከጨዋታው ውጪ አድርጓል።

ሁለቱ ቡድኖች 25 ጊዜ ተገናኝተው ኤሌክትሪክ 16 ጨዋታ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን ኢትዮጵያ መድን በአንደኛው ዙር ያስመዘገበውን የ2-0 ድል ጨምሮ 6 ጨዋታዎችን አሸንፏል። በቀሪዎቹ 3 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ለወትሮውም በጎል የታጀበ የእርስ በርስ ግንኙነት ታሪክ ያላቸው ሁለቱ ቡድኖች ባደረጓቸው ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ብቻ ያለ ጎል ሲያጠናቅቁ ኤሌክትሪክ 41 ፣ መድን 23 ጎሎችን አስቆጥረዋል።

ጨዋታውን ኤፍሬም ደበሌ በዋና ዳኝነት ዳንኤል ጥበቡ እና አስቻለው ወርቁ በረዳት እንዲሁም አዳነ ወርቁ በአራተኛ ዳኝነት ይመሩታል።